መጽሐፈ ምሳሌ 24

24
1በክፉ ሰዎች አትቅና፥
ከእነርሱ ጋርም መሆንን አትመኝ፥
2ልባቸው ግፍን ታስባለችና፥
ከንፈራቸውም ተንኮልን ትናገራለችና።
3ቤት በጥበብ ይሠራል፥
በማስተዋልም ይጸናል፥
4በእውቀት የቤት ክፍሎች
በከበረውና ባማረው ሀብት ሁሉ ይሞላሉ።
5ጠቢብ ሰው ብርቱ ነው፥
አዋቂም ሰው ኃይሉን ያበዛል።
6በመልካም አመራር ጦርነትን ትመራለህ፥
ብዙ ምክር ባለበትም ድል ይገኛል።
7ጥበብ ለሞኝ ሰው ከፍ ብላ የራቀች ናት፥
በከተማውም በር#24፥7 ሕግ ነክ ጉዳዮችና ሌሎች ሐሳቦች ለውይይት በሚቀርቡበት ቦታ። ላይ መናገር አይችልም።
8ክፉ ለማድረግ የሚያውጠነጥን፥
ተንኰለኛ ይባላል።
9የሞኝ እቅድ ኃጢአት መሥራት ነው።
ሰዎች ፌዘኛውን ይጸየፉታል።
10በመከራ ቀን ብትዝል፥
በእርግጥም ጉልበትህ ትንሽ ነው ማለት ነው።
11ወደ ሞት የሚነዱትን ታደግ፥
ለመታረድ የተወሰነባቸውን አድን።
12እነሆ፥ ይህን አላውቀውም ብትል፥
ልቦችን የሚመረምር እርሱ አያስተውልምን?
ነፍስህንም የሚመለከት እርሱ አያውቅምን?
ለሰውስ ሁሉ እንደ ሥራው አይመልስለትምን?
13ልጄ ሆይ፥ መልካም ነውና ማር ብላ፥
ወለላም ለጣምህ ጣፋጭ ነው።
14ጥበብም ለነፍስህ እንዲሁ እንደሚሆን እወቅ፥
ብታገኘውም ፍጻሜህ መልካም ይሆናል፥
ተስፋህም አይጠፋም።
15እንደ ክፉ ሰው በጻድቅ ቤት ላይ አትሸምቅ፥
ማደሪያውንም አታውክ።
16ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃልና፤ ደግሞም ይነሣል፥
ክፉዎችን ግን መጥፎ ነገር ሲገጥማቸው ይወድቃሉ።
17ጠላትህ ቢወድቅ ደስ አይበልህ፥
በመሰናከሉም ልብህ ሐሤት አያድርግ፥
18ጌታ ይህንን አይቶ እንዳያዝንብህ፥
ቁጣውንም ከእርሱ ላይ እንዳያነሣ።
19በክፉ አድራጊዎች የተነሣ አትቈጣ፥
በክፉዎችም አትቅና።
20ለክፉ ሰው የወደፊት ተስፋ የለውምና፥
የክፉዎች መብራት ይጠፋልና።
21ልጄ ሆይ፥ ጌታንና ንጉሥን ፍራ፥
ከዓመፀኞችም ጋር አትደባለቅ።#24፥21 ሰባ ሊቃናት “ለአንዳቸውም አልታዘዝም አትበል” ይላል።
22መከራቸው ድንገት ይነሣልና፥
ከሁለቱ የሚመጣውን ጥፋት ማን ያውቃል?
(የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።)
የነገሩትን የሚሰማ ልጅ ከጥፋት የራቀ ነው፥
የነገሩትን የሚቀበልን ሰው እግዚአብሔር ይቀበለዋል።
ከንጉሥ አንደበት ምንምን ሐሰት ይነገራል አይባልም፥
ከአንደበቱም የሚወጣ ሐሰት የለም።
የንጉሥ ቃል ሾተል ናት፥
ለጥፋት የተሰጠችውን ሰው ሰውነት ታጠፋዋለች እንጂ አንድ አካል ብቻ የምታጠፋ አይደለም።
ሰይፈ መዓቱ ብትሳል ግን
ከወገኑ ጋር ሰውን ታጠፋለች፥
ከአሞሮች ግልገል ወገን የማይበላ እስኪሆን ድረስ
እንደ እሳት ነበልባል ታቃጥላለች።
23እነዚህ ደግሞ የጠቢባን ቃሎች ናቸው።
በፍርድ ላይ ማዳለት መልካም አይደለም።
24ክፉዉን፦ “ጻድቅ ነህ” የሚለውን
ወገኖች ይረግሙታል አሕዛብም ይጠሉታል፥
25የሚዘልፉት ግን ደስታ ይሆንላቸዋል፥
በላያቸውም መልካም በረከት ትመጣላቸዋለች።
26በቀና ነገር የሚመልስ በፍቅር ይሰማል።
27ሥራህን በውጭ አሰናዳ፥
ለራስህ በእርሻ ውስጥ አዘጋጀው፥
ከዚያም በኋላ ቤትህን ሥራ።
28በባልንጀራህ ላይ በከንቱ ምስክር አትሁን፥
በከንፈርህም አታባብለው።
29እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ፥
እንደ ሥራውም እበቀለዋለሁ አትበል።
30በሰነፍ ሰው እርሻ፥
አእምሮ በጐደለውም ሰው ወይን ቦታ አለፍሁ።
31እነሆም፥ ሁሉ እሾህ ሞልቶበታል፥
ፊቱንም ሳማ ሸፍኖታል፥
የድንጋዩም ቅጥር ፈርሶአል።
32ተመለከትሁና አሰብሁ፥
አየሁትና ተግሣጽን ተቀበልሁ።
33 # ምሳ. 6፥10፤11። ትንሽ መተኛት፥ ትንሽ ማንቀላፋት፥
ለማረፍ እጅህን ታጥፋለህ፥
34እንግዲህ ድህነትህ እንደ ወንበዴ፥
ችጋርህም ሰይፍ እንደ ታጠቀ ሰው ይመጣብሃል።
(በግዕዝ መጽሐፈ ተግሣጽ ይባላል)።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ