ወደ ሮሜ ሰዎች 11
11
የእስራኤል ትሩፋን
1 #
ፊልጵ. 3፥5። እንግዲህ ምን ልበል፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ጣላቸውን? በጭራሽ! እኔ ደግሞ ከብንያም ወገን፥ ከአብርሃም ዘር የሆንሁ እስራኤላዊ ነኝና። 2እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን ሕዝቡን አልጣላቸውም። ወይስ ኤልያስ በእግዚአብሔር ፊት ስለ እስራኤል እንዴት እንደተከራከረ መጽሐፍ ምን እንደሚል አታውቁምን? 3#1ነገ. 19፥10፤14።“ጌታ ሆይ! ነቢያትህን ገደሉ፥ መሠዊያዎችህን አፈራረሱ፤ እናም እኔ ብቻ ቀረሁ ነፍሴንም ይፈልጓታል።” 4#1ነገ. 19፥18።ነገር ግን መለኮታዊ መልስ ምን አለው? “ለበዓል ያልሰገዱትን ሰባት ሺህ ሰዎች ለእኔ አስቀርቼአለሁ።” 5እንደዚሁም በአሁን ዘመን ደግሞ በጸጋ ተመርጠው የተረፉ አሉ። 6በጸጋ ከሆነ ግን በሥራ መሆኑ ቀርቶአል፤ ያለዚያ ጸጋ ጸጋ መሆኑ ቀርቶአል።
7እንግዲህ ምንድነው? እስራኤል የሚፈልጉትን አላገኙትም፤ የተመረጡት ግን አገኙት፤ የቀሩትም ደነዘዙ፤ 8#ዘዳ. 29፥4፤ ኢሳ. 29፥10።ይህም
“ዐይኖቻቸው እንዳያዩ፥
ጆሮቻቸውም እንዳይሰሙ፥
እግዚአብሔር ከባድ የእንቅልፍን መንፈስ እስከ ዛሬ ድረስ ሰጣቸው፤” ተብሎ ተጽፎአል።
9 #
መዝ. 69፥22፤23። ዳዊትም፥ ማዕዳቸው ወጥመድና አሽክላ
ማሰናከያም ፍዳም ይሁንባቸው፤
10እንዳያዩ ዐይኖቻቸው ይጨልሙ፤
ጀርባቸውም ሁልጊዜ ይጉበጥ
ብሏል።
የአሕዛብ መዳን
11ተመልሰው መዳን እስከማይችሉ ድረስ ተሰናከሉን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በጭራሽ! ነገር ግን እነርሱን ለማስቀናት፥ በእነርሱ በደል፥ መዳን ለአሕዛብ ሆነ። 12ነገር ግን በደላቸው ለዓለም ባለጠግነት ውድቀታቸውም ለአሕዛብ ባለጠግነት ከሆነ፥ ይልቁንስ መሙላታቸው እንዴት ይሆን?
13አሁን አሕዛብ ለሆናችሁ ለእናንተ እናገራለሁ፤ እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ እንደመሆኔ አገልግሎቴን አከብራለሁ፤ 14ይህም ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ ነው። 15የእነርሱ መጣል ለዓለም እርቅን ካስገኘ፥ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት መነሣት ነው ከማለት በቀር ምን መሆን ይችላል? 16በኩራቱም ቅዱስ ከሆነ ብኮው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው።
17ነገር ግን ከቅርንጫፎቹ አንዳንዱ ቢሰበሩ አንተም የበረሃ ወይራ የሆንህ በመካከላቸው ገብተህ ከእነርሱ ጋር የወይራ ዘይት ከሚወጣው ሥር ተካፋይ ከሆንህ፥ 18በቅርንጫፎች ላይ አትመካ፤ ብትመካባቸው ግን ሥሩ አንተን ይሸከምሃል እንጂ ሥሩን አንተ አትሸከመውም። 19እንግዲህ “እኔ እንድገባ ቅርንጫፎች ተሰበሩ፤” ትል ይሆናል። 20መልካም፤ እነርሱ ከአለማመን የተነሣ ተሰበሩ፤ አንተ ግን ከእምነት የተነሣ ቆመሃል። ፍራ እንጂ የትዕቢትን ነገር አታስብ። 21እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራላቸው ለአንተም አይራራልህምና። 22እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት፤ ጭከናው በወደቁት ላይ ነው፤ በቸርነቱ ግን ጸንተህ ብትኖር የእግዚአብሔር ቸርነት በአንተ ላይ ነው፤ ያለዚያ አንተ ደግሞ ትቆረጣለህ። 23እነዚያም ደግሞ በአለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ በዛፉ ውስጥ ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያገባቸው ይችላልና። 24አንተ በተፈጥሮ የበረሃ ከነበረ የወይራ ዛፍ ተቆርጠህ እንደ አፈጣጠርህ ሳትሆን በመልካም የወይራ ዛፍ ከገባህ፥ ይልቁንስ እነዚያ በተፈጥሮአቸው ቅርንጫፎች የሆኑት በራሳቸው የወይራ ዛፍ እንዴት አይገቡም?
የእስራኤላውያን መታደስ
25ወንድሞች ሆይ! አላዋቂዎች እንድትሆኑ አልፈልግም፤ ይህን ምሥጢር እንድታውቁ እወዳለሁ፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ እስራኤል በከፊል መደንዘዝ ሆነበት፤ 26#ኢሳ. 59፥20፤21።እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ
“አዳኝ ከጽዮን ይወጣል፤
ከያዕቆብም ክፋትን ያስወግዳል።
27 #
ኢሳ. 27፥9። ኃጢአታቸውንም ስወስድላቸው ከእነርሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው።
28በወንጌልስ በኩል በእናንተ ምክንያት ጠላቶች ናቸው፤ በምርጫ በኩል ግን በአባቶች ምክንያት ተወዳጆች ናቸው፤ 29እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጥራቱ አይጸጸትምና። 30እናንተም ቀድሞ ለእግዚአብሔር እንዳልታዘዛችሁ፥ አሁን ግን በማይታዘዙት ምክንያት ምሕረት እንዳገኛችሁ፥ 31እንዲሁም እናንተ ያገኛችሁትን ምሕረት፥ እነርሱ ደግሞ ምሕረትን እንዲያገኙ፥ እነዚህ ደግሞ አሁን አልታዘዙም። 32እግዚአብሔር በሁሉም ላይ ምሕረቱን ለማሳየት ሁሉን በአለመታዘዝ ዘግቶታልና።”
33 #
ኢሳ. 55፥8፤ ጥበ. 17፥1። የእግዚአብሔር ባለጸግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይታወቅ ነው።
34 #
ኢሳ. 40፥13። “የጌታን ልብ የሚያውቅ ማን ነው?”
“ወይስ አማካሪው የሆነ ማን ነው?
35 #
ኢዮብ 41፥11። ወይስ ብድሩን እንዲመልስ
ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው?”
36 #
1ቆሮ. 8፥6። ሁሉም ከእርሱ፥ በእርሱና ለእርሱም ነውና፤ ክብር ለዘለዓለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን።
Currently Selected:
ወደ ሮሜ ሰዎች 11: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ