መጽሐፈ ሲራክ 51

51
ቅጥያዎች የምስጋና መዝሙር
1ጌታዬ ንጉሥ ሆይ አመሰግንሃለሁ፤ አዳኜ እግዚአብሔር አወድስሃለሁ፤ ስምህንም ከፍ ከፍ አደርጋለሁ። 2ጠባቂዬ፥ ደጋፊዬም ነበርክና ሥጋዬንም ከጥፋት፥ ከዋሾ ምላስ ወጥመድ፥ ሐሰትን ከሚፈጥሩ ከንፈሮች አድነሃልና፥ በጠላቶቼ ፊት ከጐኔ ቆምህ፤ ደግፈኸኝ አዳንከኝም። 3ወሰን በሌለው ቸርነትህና በስምህም ታላቅነት ታምነህ፥ ሊበሉኝ ካሰፈሰፉት ጥርሶች፥ ካሳለፈኳቸው በርካታ መከራዎች፥ 4ከቦኝ ከነበረው አፋኝ ሙቀት፥ ሌሎች ከለኰሱት እሳት መሀል፥ 5ከጥልቁ ከርስ ሲኦል፥ 6ንጉሡን በክሕደት ከሚያወግዙበት ነጻ አወጣኸኝ። ነፍሴ ወደ ሞት ተቃርባ፥ ሕይወቴም ከሲኦል ደጃፍ ደርሳ ነበር። 7እኔ ተከብቤ ነበር፥ ረዳትም በአጠገቤ አልነበረኝም፥ ረዳት ፈለግሁ፥ ማንም አላገኘሁም። 8ያኔ ጌታ ሆይ፥ ያንተን ምሕረት፥ ከጥንትም ጀምሮ ያደረግኸውን፥ አንተን በትዕግሥት የጠበቁትን እንዴት አንደታደግኻቸው፥ ከጠላቶቻቸውም እጅ እንዴት እንዳዳንኻቸው አስታወስሁ። 9ልመናዬንም ወደ አንተ ሰደድኹ፥ ከሞትም እንድትታደገኝ ለመንሁና፥ 10ጌታዬ፥ የጌታዬንም አባት ተጣራሁ፤ በመከራ ጊዜ፥ ረዳት በማይገኝበት በትዕቢተኛውም ዘመን አትተወኝ፤ ስምህን ያለማቋረጥ አመሰግናለሁ፤ የምስጋና መዝሙርም እዘምርለታለሁ ብዬ ለመንሁህ። 11ልመናዬን ሰማህ፤ ከጥፋት አዳንኸኝ፤ ከክፉ ዘመንም ታደግኸኝ፤ 12ለዚህም አመሰግንሃለሁ፤ እወድስሃለሁ፥ የጌታንም ስም እባርካለሁ።
ስለ ጥበብ ጥም የቀረበ ቅኔ
13ገና በወጣትነቴ፥ ጉዞዬን ከመጀመሬ በፊት፥ በመጀመሪያ የለመንኩት ጥበብን እንዲሰኝ ነበር። 14ከቤተ-እግዚአብሔር ደጃፍ ቆሜ እሷን ለማግኘት እማፀናለሁ፤ እስከ መጨረሻም እርሷን ከመሻት ወደ ኋላ አልልም። 15ከአበበች ጊዜ ጀምሮ፥ ዘለላዋ እስከጐመራ ድረስ፥ የመንፈሴ ደስታ እርሷ ነበረች፤ እግሬ ቀጥተኛ መንገድ ይዞ ተጉዟል፤ ከወጣትነት ዘመኔ ጀምሮ እርሱን እከተል ነበር። 16ጆሮዬን ጥቂት ዘንበል በማድረግ እርሷን ተቀበልኋት፥ ብዙ ትምህርትም ቀሰምሁ፤ 17ዕድሜ ለጥበብ ተሻሻልሁ፤ ጥበብን ለሰጠኝ ክብር ለእርሱ ይሁን! 18እርሷን በሥራ ለማዋል ወሰንሁ። ለደግ ነገር ተጋሁ፤ ከቶውንም አላፈርም። 19ነፍሴ እርሷን ለማግኘት ቃተተች፥ ሕጉንም በመፈጸም ረገድ ቸል ያልኩበት ነገር የለም፤ እጆቼን ወደ ሰማይ ዘረጋሁ፤ ስለ እርሷ የማውቀው ጥቂት በመሆኑ አምርሬ አለቀስሁ። 20ነፍሴን ወደ እርሷ መራሁ፤ በንጽሕናም አገኘኋት፤ ከጅምሩም ልቤን በሷ ላይ ያሳረፈሁ ስለሆነ፥ እርሷ ከቶ ልትተወኝ አይገባም፤ 21እኔነቴ እርሷን በመራቡ በእጄ አስገባኋት። 22ጌታም ለእርሱ የምስጋና መዝሙር የማዜምበት ምላስ ሸለመኝ። 23እናንት ማይማን ወደ እኔ ኑ፥ የእኔም ተማሪዎች ሁኑ፥ 24ነፍሳችሁ ስለ እነዚህ ነገሮች እንዲህ ስትጠማ እንዳጣችኋቸው ስለምን ታማርራላችሁ? 25አፌን ከፈትሁ፥ እንዲህም አልሁ፥ ያለ ገንዘብ ግዟት፥ 26በቀንበሯ ሥር አንገታችሁን አኑሩ፥ ነፍሶቻችሁ ትምህርትን ያግኙ፥ አጠገባችሁ ነች፥ ትደርሱባትማላችሁ። 27እስቲ አስተውሉ፥ ይህን ያህል ሰላም ለማግኘት ምንም እንዳልደከምሁ ታያላችሁ። 28ትምህርቱን በብዙ ብር ግዙ፤ እድሜ ለእርሷ ብዙ ወርቅ ታገኛላችሁ። 29በእግዚአብሔር ምሕረት ነፍሶቻችሁ ተድላን ያግኙ፥ እርሱን ለማመስገን አያስፈራችሁ፥ 30ከቀጠሮ በፊት ሥራችሁን አጠናቁ፥ በተባለውም ሰዓት ከእርሱ ዋጋችሁን ትቀበላላችሁ። የሲራክ ልጅ የኢየሱስ ጥበብ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ