ወደ ቲቶ 1
1
ሰላምታ
1የእግዚአብሔር ባርያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእግዚአብሔርም የተመረጡት ያላቸውን እምነትና እግዚአብሔርን በመምሰል ላይ የተመሠረተውን የእውነት እውቀት ለማስፋፋት፥ 2ከቶውኑ የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት ቃል በገባው የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ ያደረገ፤ 3ተገቢም በሆነው በራሱ ጊዜ፥ በአዳኛችን በእግዚአብሔር ትእዛዝ፥ ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት አማካይነት ቃሉን ገለጠ፤ 4የጋራ በሆነው እምነት እውነተኛ ልጄ ለሆንከው ለቲቶ፤
ከእግዚአብሔር አብ ከአዳኛችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ሰላም ይሁን።
የቲቶ ሥራ በቀርጤስ ደሴት
5የተቀረውን ሥራ እንድታቃናና በየከተማው እኔ እንዳዘዝሁህ ሽማግሌዎችን እንድትሾም፥ አንተን በዚህ ምክንያት በቀርጤስ ተውሁህ፤ 6ነቀፋ የሌለበትና የአንዲት ሚስት ባል የሆነ፥ በመዳራትም ወይም ባለመታዘዝ የማይከሰሱ አማኝ ልጆች ያሉት ማንም ሰው ቢኖር፥ ሹመው። 7ኤጲስ ቆጶስ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ ነቀፋ የሌለበት ሊሆን ይገባዋል፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ ጠበኛ ያልሆነ፥ ለገንዘብ የማይስገበገብ፥ 8ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚቈጣጠር ይሁን፤ 9እውነተኛውንም ትምህርት ለመምከርና ተቃዋሚዎቹን ለመገሠጽ እንዲችል፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና። 10የማይታዘዙና ከንቱ ነገርን የሚያወሩ የሚያታልሉ በተለይም ከተገረዙት ወገን የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉና፤ 11እነዚህም ማስተማር የማይገባቸውን በማጭበርበር የሚገኘውን ጥቅም እያስተማሩ ቤተሰቦችን በሞላ አውከዋልና፥ እነርሱን ዝም ማሰኘት ይገባል። 12ከእነርሱ አንዱ የሆነው የገዛ ራሳቸው ነቢይ፦ “የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸታሞች፥ ክፉ አውሬዎች፥ ሥራ ፈት ሆዳሞች ናቸው፤” ብሏል። 13ይህ ምስክርነት እውነት ነው። በዚህም ምክንያት እነርሱን አጥብቀህ ገሥጽ፤ ይህን የምታደርገው በእምነት ረገድ እንዲጸኑና 14በአይሁድ ተረቶችና እውነትን በማይቀበሉ በሰዎች ትእዛዛት እንዳይጠመዱ ነው። 15ለንጹሖች ሁሉ ነገር ንጹሕ ነው፤ ለርኩሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ነገር ምንም የለም፤ ነገር ግን አእምሮአቸውም ሆነ ኅሊናቸው ረክሶአል። 16እግዚአብሔርን እንደሚያውቁ በግልጥ ይናገራሉ ዳሩ ግን በሥራቸው ይክዱታል፤ የሚያጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ ብቁ ያልሆኑ ናቸው።
Currently Selected:
ወደ ቲቶ 1: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ