መጽሐፈ ጦቢት 1
1
1የቶብኤል ልጅ፥ የአናኒኤል ልጅ፥ የአዱኤል ልጅ፥ የጋባኤል ልጅ፥ የሩፋኤል ልጅ፥ የራጉኤል ልጅ፥ የአሲኤል ዘር፥ የኔፍታሊም ወገን የሆነው ጦቢት የቃሉ መፅሐፍ ይህ ነው። 2#2ነገ. 17፥3፤ 18፥9።እሱም በአሦር ንጉሥ በሸልማንሰር ዘመን፥ ከላይኛው ገሊላ ክፍል ከቄዴሽ ኔፍታሊም በስተ ደቡብ፥ ከአሼር ወደ ምዕራብና ከፎጎር በስተ ሰሜን ከምትገኘው ከቲስቤ በምርኮ ተወስዶ የነበረው ነው።
ስደተኛው ጦቢት
3እኔ ጦቢት በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእውነት መንገድና በጽድቅ ሄድሁ፤ ወደ አሦር አገር ወደ ነነዌ ከኔ ጋር ተማርከው ለመጡት ወንድሞቼና ወገኖቼ ብዙ መጽውቻለሁ። 4በአገሬ እስራኤል ምድር በነበርኩበት ጊዜና ገና ወጣት ሳለሁ፥ የአባቶቼ የናፍታሊ ወገኖች በሙሉ የዳዊትን ቤትና ኢየሩሳሌምን ጥለው ሄዱ። ይህች ከተማ ከእስራኤል ነገዶች በሙሉ ተመርጣ፥ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሆነው በቤተ መቅደሱ፥ የእስራኤል ነገዶች መሥዋዕት እንዲያቀርቡባት፥ ለትውልድ ሁሉ ለዘለዓለም ተቀድሳና ታንፃ ነበር። 5#1ነገ. 12፥28፤29።ዘመዶቼና የአባቶቼ የናፍታሊ ወገኖች ሁሉ፥ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በገሊላ ተራራዎች ላይ በዳን ላቆመው ጥጃ መሥዋዕት አቀረቡ። 6#ዘዳ. 16፥16።ለመላው እስራኤል በተሰጠው ለዘለዓለም ጸንቶ በሚኖረው ትእዛዝ መሠረት ለበዓላት ብዙ ጊዜ ብቻዬን ወደ ኢየሩሳሌም እሄድ ነበር። ካመረትሁት ሁሉ የመጀመሪያውን አሥራት ከከብቶቼም በመጀመሪያ የተወለደውን፤ ከበጐቼም በመጀመሪያ የተሸለተውን ጠጉር ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም እሄድና በቤተ መቅደስ 7እነዚህን ለካህናቱ ለአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ እሰጥ ነበር። የወይን፥ የእህል፥ የወይራ፥ የሮማንና ሌሎችም ፍሬዎች አስራት በኢየሩሳሌም ለሚያገለግሉ ሌዋውያን እሰጥ ነበር። መሬት በማይታረስበት በሰባተኛው ዓመት ካልሆነ በቀር በየዓመቱ ሁለተኛውን አሥራት በጥሬ ገንዘብ ለውጬ ወደ ኢየሩሳሌም እሄድና እከፍል ነበር። 8ሶስተኛውን አሥራት ለሙት ልጆች፥ ለመበለቶችና ከእሥራኤል ልጆች ጋር ለሚኖሩ እንግዶች እሰጥ ነበር፤ በየሶስት ዓመቱ እንደ ስጦታ እሰጣቸው ነበር፤ ስንበላም በሙሴ ሕግ ለተደነገገውና ለአያታችን ለአናኒኤል እናት ምክር እንታዘዝ ነበር፥ እኔ አባቴ ሞቶብኝ የሙት ልጅ ነበርሁና። 9ለአቅመ አዳም በደረስሁ ጊዜም ዘመዳችን የሆነችውን ሐናን አገባሁ፤ በእርሷም ጦብያ ብዬ የጠራሁትን ወንድ ልጅ አገኘሁ። 10ግዞት ወደ አሦር በመጣ ጊዜ፥ እኔም ተወሰድሁ ወደ ነነዌም መጣሁ። ወንድሞቼና ወገኖቼ ሁሉ የአረማውያንን ምግብ በሉ፤ 11እኔ ግን የአረማውያንን ምግብ ከመብላት እራሴን ገታሁ። 12ምክንያቱም በሙሉ ልቤ እግዚአብሔርን አስብ ነበር፤ 13ልዑል አምላክ በንጉሡ በሸልማንሰር ዘንድ ሞገስንና ባለሟልነትን ሰጠኝ፥ ንጉሡ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ አቅራቢ ሆንኩኝ። 14እስከሞተበት ጊዜ ድረስ አስፈላጊውን ለመግዛት ወደ ምድያም እመላለስ ነበር። ምድያም በተባለው ቦታ ሳለሁ ለገብርያስ ወንድም ለገባኤል የሚመዝን ብር በአደራነት እንዲያስቀምጥልኝ በከረጢቶች አድርጌ ሰጠሁት። 15ሸልማንሰር በሞተ ጊዜና በቦታውም ልጁ ሰናክሬም በተተካ ጊዜ ግን ወደ ምድያም የሚወስደው መንገድ ተዘጋ፥ እኔም ወደዚያ ለመሄድ አልቻልሁም። 16በሸልማንሰር ጊዜ ለወገኖቼ ብዙ ጊዜ እመጸውት ነበር። 17#ኢዮብ 31፥16-20።ምግቤን ለተራቡ፥ ልብሶችን ደግሞ ለታረዙ እሰጥ ነበር። የወገኖቼ ሬሳ ከነነዌ ቅጥር ውጪ ተጥሎ ባየሁ ጊዜ እቀብር ነበር። 18በሰናክሬም የተገደሉትን ሁሉ ጭምር እቀብር ነበር። ሰናክሬም በተሳደበው ስድብ ምክንያት የሰማይ ንጉሥ ቀጥቶት ከይሁዳ ሸሽቶ በመጣ ጊዜ ተበሳጭቶ ነበርና ብዙ እስራኤላውያንን ገደለ፤ እሱ የገደላቸውን ሰዎች ሬሳ እየሰረቅሁ እቀብር ነበር፤ ሬሳቸውንም ሲፈልገው አያገኘውም ነበር። 19ከነነዌ ሰዎች አንዱ ወደ ንጉሡ ሄዶ የሰዎቹን ሬሳ በምሥጢር የቀበርሁ እኔ መሆኔን ተናገረ፤ ንጉሡ ስለ እኔ ማወቁንና እኔም ለመገደል እየተፈለግሁ መሆኑን ስገነዘብ ፈራሁና ሸሸሁ። 20ያለኝን ንብረት ሁሉ ተይዞ ነበር፤ ሁሉም በግምጃ ቤቱ ተወርሰው ነበር፤ ከሚስቴ ሐናንና ከልጄ ጦብያ በስተቀር ምንም አልቀረም። 21ይህ ከሆነ አርባ ቀን ሳይሞላው ሁለቱ ልጆቹ ንጉሡን ገደሉት፥ ከዛም ወደ አራራት ተራራዎች ሸሹ፤ ልጁ ኤሳራዶን ተተካ። የወንድሜ የአናኤል ልጅ አሂካር የመንግሥት ገንዘብ አስተዳዳሪና የአስተዳደሩ ዋና ሆኖ ተሾመ። 22ከዚህ በኋላ አሂካር አማለደኝና ወደ ነነዌ እንድመለስ ተፈቀደልኝ። በአሦር ንጉሥ በሰናክሬም ጊዜ አሂካር የወይን ጠጅ ቀጂዎች አለቃ፥ የመንግሥት ማኀተም ጠባቂ፥ የገንዘብ ቤቱ አስተዳዳሪና ነበር። ንጉሡ ኤሳራዶንም በዚህ በሥራው ላይ በድጋሚ ሾመው። እርሱም ዘመዴ የወንድሜ ልጅ ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጦቢት 1: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ