መጽ​ሐፈ ጦቢት 3

3
ጦቢት
1ከዚህ በኋላ በልቤ አዝኜ፥ ተከዝሁ አለቀስሁም፤ ይህን የለቅሶ ጸሎት ጀመርሁ፦ 2“ጌታ ሆይ አንተ እውነተኛ ነህ፥ ስራዎችህም ትክክለኛ ናቸው፥ በመንገዶችህም ሁሉ ጸጋና እውነት ናቸው፥ የዓለምም ፈራጅ አንተ ነህ። 3ስለዚህ ጌታ ሆይ አስበኝ፥ ወደ እኔም ተመልከት፤ በኃጢአአቴ ምክንያት ወይም ሳላውቅ በአጠፋሁት ወይም አባቶቼ በአጠፉት አትቅጣኝ። 4አንተን በድለናል ትእዛዞችህንም አፍርሰናልና፤ ለዝርፊያ፥ ለስደትና ለሞት፥ ተበትነን በምንኖርባቸው አገሮች ሁሉ ተንቀን መተረቻና ማላገጫ እንድንሆን አሳለፈህ ሰጥተኸናል። 5በራሴና በአባቶቼ ኃጢአት ምክንያት እንዲህ በማድረግ ፍርዶችህ ሁሉ እውነት ናቸው፥ ትዕዛዞችህን አልፈጸምንምና፥ በፊትህም በእውነት አልተራመድንምና። 6አሁንም እንደ ፈቀድህ አድርገኝ፤ ከዚህች ምድር ተላቅቄ ዳግም አፈር ልሁን፥ ከመኖር መሞት ይሻለኛልና፥ ከንቱ ስድብን ተቋቁሜአልሁና፥ በታላቅ ኃዘንም ውስጥ ነኝ፤ ጌታ ሆይ ከዚህ መከራ እንድላቀቅ እዘዝ፥ ወደ ዘላለማዊ ቤቴም እንድሄድ ፍቀድ፤ ጌታ ሆይ ፊትህን ከኔ አትመልስ፤ በማያባራ ሰቆቃ ከተሞላ ሕይወት ይልቅ ሞቴን እመርጣለሁ፥ ከዚህ ወዲያ ስድቦችን መሸከም አልችልም።”
3 ሣራ
7በዚያች ቀን በሜዶን በኤቅባጥና ከተማ የራጉኤል ልጅ ሣራ ከአባትዋ አገልጋዮች በአንዷ ተሰደበች። 8ሰባት ጊዜ በጋብቻ ተሰጥታ ወንድ ከሴት ጋር እንደሚያደርገው ከእርሷ ጋር ከመተኛታቸው በፊት አስሞዴዩስ የተባለ ክፉ ጋኔን ባሎችዋን ይገላቸው ነበርና። ያች አገልጋይ እንዲህ አለቻት “ባሎችሽን የምትገድያቸው አንቺ ነሽ፥ ለሰባት ባሎች ተሰጥተሽ ነበር፥ ግን ከአንዱም ጋር አብረሽ አልኖርሽም፥ 9ባሎችሽ ስለ ሞቱ እኛ የምንቀጣበት ምንም ምክንያት የለም፤ ሂጂና ተቀላቀያቸው፥ እኛም መቼም ቢሆን የአንቺን ልጅ አንይ።” 10ያን ቀን አዘነች፥ ምርር ብላ አለቀሰች፥ ራስዋን ለመስቀል ወደ አባቷ ክፍል ገባች፤ ነገር ግን እንዲህ ብላ አሰበች፦ “አባቴን ‘የምትወዳትና ብቸኛዋ ልጅህ ከኀዘንዋ ክብደት የተነሣ እራስዋን ገደለች’ በማለት ይወቅሱታል፥ እኔም የአባቴን ሽምግልና ወደ ሞት የሚያፈጥን ኀዘን ማምጣት የለብኝም፤ ስለ ሆነም ራሴን ከመስቀል ይልቅ ዳግም የስድብ ቃላት ላለመስማት ከምኖር እንዲገድለኝ ጌታን እለምነዋለሁ።” 11በዚያ ሰዓት ወደ መስኮቱ እጆችዋን ዘርግታ እንዲህ ስትል ጸለየች፦ “መሐሪ አምላክ ሆይ፥ የተባረክ ነህ፥ ስምህ ለዘለዓለም ብሩክ ይሁን፥ የሠራሃቸው ነገሮች በሙሉ ለዘለዓለም ይባርኩህ። 12አሁንም ጌታ ፊቴን የምመልሰውና ዓይኔን የማቀናው ወደ አንተ ነው። 13ከዚህ ዓለም እንድላቀቅና ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ ስድብ እንዳልሰማ አድርገኝ። 14ጌታ ሆይ በንጽሕና እንደቆየሁ ታውቃለህ፤ ማንም ወንድ ነክቶኝ አያውቅም፤ 15በስደት ምድር ላይ የራሴንም ስም ሆነ የአባቴን ስም አላጎገፍኩም፤ ለአባቴም ብቸኛ ልጁ ነኝ፥ የሚወርሰው ሌላ ልጅ የለውም፥ እንዲሁም በአጠገቡ ወንድም የለውም፤ እራሴን የማቆይለት ዘመድም የለውም፤ እስከ አሁን ሰባት ባሎች ሞተውብኛል፥ ታዲያ ከዚህ በኋላ ለምን እኖራለሁ? ነፍሴን ለመው ካላስደሰትህ ግን ጌታ ሆይ እዘንልኝ፥ ከዚህ በኋላ ስሜ ሲጠፋ መስማት አልሻም።” 16በዚህ ጊዜ የሁለቱ ጸሎት በእግዚአብሔር ክቡር (ሕልውና) ፊት ተቀባይነትን አገኘ። 17#ዘኍ. 36፥6-9፤ ጦቢ. 6፥10-12።ሁለቱንም እንዲፈውሳቸው ሩፋኤል ተላከ። ከጦቢት ዐይን የእግዚአብሔርን ብርሃን እንዲያይ ዓይኑ ላይ ያለውን ነጥብ ሊያጠፋለት፥ የራጉኤል ልጅ ሣራን ደግሞ ለጦቢት ልጅ ለጦብያ በሙሽርነት በመስጠት፥ ከአጋንንት ሁሉ ከከፋው ከአስሞዴዩስ ለማስጣል፥ በእርግጥም ከሁሉም አድናቂዎች ይልቅ የምትገባው ለጦብያ ነበርና፤ በተመሳሳይ ጊዜ ጦቢት ከግቢው አጥር ሲመለስ ሳለ የራጉኤል ልጅ ሣራ ከነበረችበት ክፍል ወደ ታች ደረጃውን በመውረድ ላይ ነበረች።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ