መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 2
2
የሳሙኤል እናት የሐና ጸሎት
1ሐናም ጸለየች፤ እንዲህም አለች፦
“ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፤
ቀንዴም#ምሥጢሩ “ኀይል” ነው። በአምላኬ በመድኀኒቴ ከፍ ከፍ አለ፤
አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ፤
በማዳንህም ደስ ብሎኛል።
2እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና፥
እንደ አምላካችንም ጻድቅ የለምና፤
አቤቱ፥ ከአንተም በቀር ቅዱስ የለም።
3አትመኩ፤ የኵራት ነገሮችንም አትናገሩ፤
ፅኑዕ ነገርም ከአፋችሁ አይውጣ፤
እግዚአብሔር አምላክ ዐዋቂ ነውና፥
እግዚአብሔርም ዙፋኑን ያዘጋጃል።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሥራውን የሚመዝን ነውና” ይላል።
4የኀያላንን ቀስት ሰብሮአል፤
ደካሞችንም ኀይልን አስታጥቋቸዋል።
5እንጀራ ጠግበው የነበሩ ተራቡ፤
ተርበውም የነበሩ ጠገቡ፤
መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥
ብዙም የወለደችው መውለድ አልቻለችም።
6እግዚአብሔር ይገድላል፤ ያድናልም፤
ወደ ሲኦል ያወርዳል፤ ያወጣልም።
7እግዚአብሔር ድሀ ያደርጋል፤ ባለጠጋም ያደርጋል፤
ያዋርዳል፤ ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል።
8ችግረኛውን ከመሬት ያነሣዋል፤
ምስኪኑንም ከጕድፍ ያነሣዋል፤
ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጠው ዘንድ፥
የክብርንም ዙፋን ያወርሰው ዘንድ።
9ለሚጸልይ ጸሎቱን ይሰጠዋል፤
የጻድቃንን ዘመን ይባርካል፤
የሰው ኀይል ጽኑዕ አይደለምና።
10እግዚአብሔር ጠላቶቹን ያደክማቸዋል፤
እግዚአብሔር ብቻ ቅዱስ ነው፤
ጥበበኛ በጥበቡ አይመካ፤
ኀይለኛም በኀይሉ አይመካ፤
ሀብታምም በሀብቱ አይመካ፤
የሚመካ ግን በዚህ ይመካ፤
እግዚአብሔርን በማወቅና በማስተዋል፤
በምድርም መካከል ፍርድንና እውነትን በማድረግ፥
እግዚአብሔር ወደ ሰማይ ወጣ፤ አንጐደጐደም።
ጻድቅ እርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፤
ለንጉሦቻችንም ኀይልን ይሰጣል፤
የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።”#ምዕ. 2 ቍ. 8፥ 9 እና 10 በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. ልዩነት አለው።
11በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተዉት።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በእግዚአብሔር ፊት ትታው ሄደች” ይላል። እነርሱም ወደ አርማቴም ወደ ቤታቸው ገቡ፤ ልጁም በካህኑ በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር።
የካህኑ የዔሊ ልጆች ክፉ ሥራ
12የካህኑም የዔሊ ልጆች ክፉዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር። 13መሥዋዕት በሚሠዉ በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የነበረ የካህኑንም ሕግ አያውቁም ነበረ፤ ሕዝቡም ሁሉ መሥዋዕት በሠዉ ጊዜ የካህኑ ብላቴና ይመጣ ነበር፤ በእጁም ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ነበር፤ 14ወደ ድስቱም ወይም ወደ ምንቸቱ ወይም ወደ አፍላሉ ወይም ወደ ቶፋው#“ወደ ቶፋው” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ይሰድደው ነበር። ሜንጦውም ያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለእርሱ ይወስደው ነበር፤ በሴሎም ለእግዚአብሔር ሊሠዉ በሚወጡ በእስራኤላውያን ሁሉ ላይ እንዲህ ያደርጉ ነበር። 15ደግሞም ስቡ ሳይጤስ የካህኑ ልጅ መጥቶ የሚሠዋውን ሰው፥ “ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ አይወስድምና እጠብስለት ዘንድ ለካህኑ ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር። 16የሚሠዋውም ሰው፥ “አስቀድሞ እንደ ሕጉ ስቡ ይጢስ፤ ኋላም ሰውነትህን ደስ የሚያሰኛትን ትወስዳለህ” ቢለው፥ እርሱ፥ “አይሆንም፥ ነገር ግን አሁን ስጠኝ፤ ካልሆነም በግድ አወስደዋለሁ” ይለው ነበር። 17የእግዚአብሔርን ቍርባን ይንቁ ነበርና የዔሊ ልጆች ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረች።
ብላቴናው ሳሙኤል በሴሎ
18ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ የበፍታ ኤፉድ ታጥቆ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር። 19እናቱም ታናሽ መደረቢያ ሠራችለት፤ በየዓመቱም መሥዋዕት ለመሠዋት ከባልዋ ጋር ስትወጣ ትወስድለት ነበር። 20ዔሊም ሕልቃናንና ሚስቱን ባረካቸው፥ “ለእግዚአብሔር ስለ አገባኸው ስጦታ ፈንታ ከዚህች ሴት እግዚአብሔር ዘር ይስጥህ” አለው፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ገቡ። 21እግዚአብሔርም ሐናን ጐበኘ፤ ዳግመኛም ፀነሰች፥#“ፀነሰች” የሚለው በዕብ. ብቻ። ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆችን ወለደች። ብላቴናው ሳሙኤልም በእግዚአብሔር ፊት አደገ።
ካህኑ ዔሊ የልጆቹን ክፉ ሥራ እንደ ሰማ
22ዔሊም እጅግ አረጀ፤ ልጆቹም የእስራኤልን ልጆች ያደረጓቸውን፥ በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉት ሴቶችም ጋር እንደሚተኙ ሰማ።#“በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር እንደሚተኙም ሰማ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 23እርሱም አላቸው፥ “ከእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ አፍ የምሰማውን ይህን ነገር ለምን ታደርጋላችሁ? 24ልጆቼ ሆይ፥ ይህ አይሆንም፤ እኔ የምሰማው ይህ ነገር መልካም አይደለምና እንዲህ አታድርጉ። ሕዝቡንም እግዚአብሔርን ከማገልገል አትከልክሉአቸው። 25ሰውስ ሰውን ቢበድል ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩለታል፤ ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ ወደ ማን ይጸልዩለታል?” እነርሱ ግን እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ወድዶአልና የአባታቸውን ቃል አልሰሙም። 26ብላቴናው ሳሙኤልም አደገ፤ በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ሞገስ እያገኘ ሄደ።
በካህኑ ቤተ ሰብ ላይ የተነገረ ትንቢት
27የእግዚአብሔርም ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ እንዲህ አለው፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በግብፅ በፈርዖን ቤት ባሪያዎች ሳሉ ለአባትህ ቤት ተገለጥሁ፤ 28ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ ካህን ይሆነኝ ዘንድ፥ በመሠዊያዬም ላይ ይሠዋ ዘንድ፥ ዕጣንንም ያጥን ዘንድ፥ ኤፉድንም በፊቴ ይለብስ ዘንድ፥ የአባትህን ቤት ለእኔ መረጥሁት፤ የእስራኤልንም ልጆች የእሳት ቍርባን ሁሉ ስለ ምግብ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ። 29በመሥዋዕቴ ላይና በዕጣኔ ላይ ስለ ምን በክፉ ዐይን ተመለከትህ? የእስራኤል ልጆች በፊቴ ከሚያቀርቡት መሥዋዕት ሁሉ በቀዳምያቱ ስለ አከበርሁህ ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን መረጥህ? 30ስለዚህም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእውነት ቤትህ፥ የአባትህም ቤት፤ ለዘለዓለም በፊቴ እንዲኖር ተናግሬአለሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያከበሩኝን አከብራለሁና፥ የናቁኝም ይናቃሉና ይህ አይሆንልኝም። 31እነሆ፥#ዕብ. “ለቤትህ ሽማግሌ እንዳይገኝ” የሚል ይጨምራል። ዘርህንም፥ የአባትህንም ቤት ዘር የማጠፋበት ዘመን ይመጣል፤ 32#ዕብ. “በእስራኤል በረከት በማደሪያዬ ጠላትህን ታያለህ” የሚል ይጨምራል።በቤትህም ለዘለዓለም ሽማግሌ አይገኝም። 33በዐይኖቹ የሚፈጽም በነፍሱም የሚተጋ ሰውን ከመሠዊያዬ አላጠፋም።#ዕብ. “ከመሠዊያዬ ያልተቈረጠ ልጅህ ቢገኝ ዐይንህን ያፈዝዘዋል ፤ ነፍስህንም ያሳዝናል” ይላል። ከቤትህ የሚቀሩት ሰዎች ሁሉ ግን በጐልማሶች#ዕብ. “በጐልማሳነት ይሞታሉ” ይላል። ሰይፍ ይሞታሉ። 34ይህ በሁለቱ ልጆችህ በአፍኒንና በፊንሐስ ላይ የሚመጣ ለአንተ ምልክት ነው፤ ሁለቱ በአንድ ቀን በጦር ይሞታሉ። 35የታመነ ካህን ለእኔ አስነሣለሁ፤ በልቤም፥ በነፍሴም እንዳለ እንዲሁ ያደርጋል፤ እኔም የታመነ ቤት እሠራለታለሁ፤ ዘመኑን ሁሉ እኔ በቀባሁት ሰው ፊት ይሄዳል። 36ከቤትህም የቀረው ሁሉ ይመጣል፤ ከካህናትም ወደ አንዲቱ ዕጣ፥ እንጀራ ወደምበላበት እባክህ ላከኝ ብሎ ለአንድ ብር መሐልቅ ለቍራሽ እንጀራ በፊቱ ይሰግዳል።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 2: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ