መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 26
26
ዳዊት ለሳኦል እንደ ገና እንደ ራራለት
1የዚፍ ሰዎችም ከአውክሞዲስ ወደ ኮረብታው ወደ ሳኦል መጥተው፥ “እነሆ፥ ዳዊት በየሴሞን ፊት ለፊት ባለው በኤኬላ ኮረብታ ላይ ከእኛ ጋር ተሸሽጎ አለ” አሉት። 2ሳኦልም ተነሥቶ ዳዊትን በዚፍ ምድረ በዳ ይሻ ዘንድ ከእስራኤል የተመረጡ ሦስት ሺህ ሰዎችን ይዞ ወደ ዚፍ ምድረ በዳ ወረደ። 3ሳኦልም በየሴሞን ፊት ለፊት ባለው በኤኬላ ኮረብታ ላይ በመንገዱ አጠገብ ሰፈረ። ዳዊትም በምድረ በዳ ውስጥ ተቀምጦ ነበር፥ ዳዊትም ሳኦል ሊፈልገው ወደ ምድረ በዳ እንደ መጣ ዐወቀ። 4ዳዊትም ሰላዮችን ላከ፤ ሳኦልም ተዘጋጅቶ ወደ ቂአላ እንደ መጣ በርግጥ ዐወቀ። 5ዳዊትም በቀስታ ተነሥቶ ሳኦል ወደ ሰፈረበት ቦታ መጣ፤ ሳኦልና የሠራዊቱ አለቃ የኔር ልጅ አቤኔርም የተኙበትን ስፍራ አየ፤ ሳኦልም በድንኳን ውስጥ ተኝቶ ነበር፤ ሕዝቡም በዙሪያው ሰፍሮ ነበር።
6ዳዊትም ኬጤያዊዉን አቤሜሌክንና የሶርህያን ልጅ የኢዮአብን ወንድም አቢሳን፥ “ወደ ሳኦል ወደ ሰፈሩ ከእኔ ጋር የሚገባ ማን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው፤ አቢሳም፥ “እኔ ከአንተ ጋር እገባለሁ” አለ። 7ዳዊትና አቢሳም ወደ ሕዝቡ በሌሊት መጡ፤ እነሆም፥ ሳኦል በድንኳን ውስጥ ተኝቶ ነበር፤ ጦሩም በራስጌው አጠገብ በምድር ተተክሎ ነበር፤ አቤኔርና ሕዝቡም በዙሪያው ተኝተው ነበር። 8አቢሳም ዳዊትን፥ “ዛሬ እግዚአብሔር ጠላትህን በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶታል፤ አሁንም እኔ በጦር አንድ ጊዜ ከምድር ጋር ላጣብቀው፤ ሁለተኛም አልደግመውም” አለው። 9ዳዊትም አቢሳን፥ “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጁን የሚዘረጋ ንጹሕ አይሆንምና አትግደለው” አለው። 10ደግሞም ዳዊት አለው፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! እግዚአብሔር ካልገደለው፥ ወይም ቀኑ ደርሶ ካልሞተ፥ ወይም ወደ ጦርነት ወርዶ ካልሞተ እኔ አልገድለውም። 11እግዚአብሔርም በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው፤ አሁንም በራሱ አጠገብ ያለውን ጦርና የውኃውን መንቀል ይዘህ እንሂድ፤” አለው። 12ዳዊትም በሳኦል ራስጌ የነበረውን ጦርና የውኃውን መንቀል ወሰደ፤ ወደ ቤታቸውም ተመለሱ። ማንም ያየ አልነበረም፤ ያወቃቸውም ማንም አልነበረም፤ የነቃም ማንም አልነበረም፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከባድ እንቅልፍ ወድቆባቸው ነበርና ሁሉ ተኝተው ነበር።
13ዳዊትም ወደ ማዶ ተሻገረ፤ በተራራውም ራስ ላይ ርቆ ቆመ፤ በመካከላቸውም ሰፊ ርቀት ነበረ። 14ዳዊትም ሕዝቡንና የኔር ልጅ አቤኔርን ጠራቸው፥ “አቤኔር ሆይ፥ አትመልስምን?” አለው። አቤኔርም መልሶ፥ “አንተ የምትጠራኝ ማን ነህ?” አለ። 15ዳዊትም አቤኔርን፥ “አንተ ጐልማሳ አይደለህምን? በእስራኤል ዘንድ አንተን የሚመስል ማን ነው? ጌታህን ንጉሡን ለመግደል አንድ ሰው ገብቶ ነበርና ጌታህን ንጉሡን የማትጠብቅ ስለምን ነው? 16ይህ ያደረግኸው ነገር መልካም አይደለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! እናንተ እግዚአብሔር የቀባውን ጌታችሁን አልጠበቃችሁምና ሞት ይገባችኋል፤ አሁንም የንጉሡ ጦርና በራሱ አጠገብ የነበረው የውኃ መንቀል የት እንደ ሆነ ተመልከት” አለው።
17ሳኦልም የዳዊት ድምፅ እንደ ሆነ ዐውቆ፥ “ልጄ ዳዊት ሆይ! ይህ ድምፅህ ነውን?” አለው። ዳዊትም፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! አዎ እኔ ባሪያህ ነኝ” አለው። 18ደግሞም አለ፥ “ጌታዬ አገልጋዩን ስለምን ያሳድዳል? ምን አደረግሁ? ምንስ ክፋት በእጄ ላይ ተገኘብኝ? 19አሁንም ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! የእኔን የአገልጋይህን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በእኔ ላይ አስነሥቶህ እንደሆነ፥ ቍርባንህን ይቀበል፤ የሰው ልጆች ግን ቢሆኑ፦ ሂድ ሌሎችን አማልክት አምልክ ብለው በእግዚአብሔር ርስት ላይ እንዳልቀመጥ ዛሬ ጥለውኛልና በእግዚአብሔር ፊት ርጉማን ይሁኑ። 20አሁንም በተራራው ላይ ሰው ቆቅን እንደሚሻ የእስራኤል ንጉሥ ነፍሴን ለመሻት ወጥቶአልና ደሜ በእግዚአብሔር ፊት በምድር ላይ አይፍሰስ።”
21ሳኦልም፥ “በድያለሁ፤ ልጄ ዳዊት ሆይ! ተመለስ፤ ዛሬ ነፍሴ በዐይንህ ፊት ከብራለችና ከዚህ በኋላ ክፉ አላደርግብህም፤ እነሆ፥ ስንፍና እንደ አደረግሁና፥ እጅግ ብዙም እንደ ሳትሁ ዐወቅሁ” አለ። 22ዳዊትም መልሶ አለ፥ “የንጉሥ ጦር እነሆ፤ ከብላቴኖችም አንድ ይምጣና ይውሰዳት። 23ዛሬም እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ሰጥቶህ ሳለ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን እዘረጋ ዘንድ አልወደድሁምና ለሁሉ እያንዳንዱ እግዚአብሔር እንደ ጽድቁና እንደ እምነቱ ፍዳውን ይክፈለው። 24ነፍስህም ዛሬ በዐይኔ ፊት እንደ ከበረች እንዲሁ ነፍሴ በእግዚአብሔር ፊት ትክበር፤ ከመከራም ሁሉ ይሰውረኝ፤ ያድነኝም።” 25ሳኦልም ዳዊትን፥ “ልጄ ዳዊት ሆይ! ቡሩክ ሁን፤ ማድረግን ታደርጋለህ፤ መቻልንም ትችላለህ” አለው። ዳዊትም መንገዱን ሄደ፤ ሳኦልም ወደ ስፍራው ተመለሰ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 26: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ