መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 10
10
ዳዊት አሞናውያንንና ሶርያውያንን ድል እንደ አደረገ
(1ዜ.መ. 19፥1-19)
1ከዚህ በኋላ የአሞን ልጆች ንጉሥ ሞተ፤ ልጁም ሐኖን በፋንታው ነገሠ። 2ዳዊትም፥ “አባቱ ቸርነትን እንዳደረገልኝ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ” አለ። ዳዊትም ስለ አባቱ ያጽናኑት ዘንድ ብላቴኖቹን ላከ፤ የዳዊትም ብላቴኖች ወደ አሞን ልጆች ሀገር መጡ። 3የአሞንም ልጆች አለቆች ጌታቸውን ሐኖንን፥ “ዳዊት አባትህን በፊትህ ለማክበር አጽናኞችን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ዳዊትስ ከተማዪቱን ለመመርመርና ለመሰለል፥ ለመፈተንም#ዕብ. “ለመፈተን” በማለት ፋንታ “ለማጥፋት” ይላል። አገልጋዮቹን የላከ አይደለምን?” አሉት። 4ሐኖንም የዳዊትን አገልጋዮች ወስዶ የጢማቸውን ገሚስ ላጨ፤ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው። 5ለዳዊትም ስለ ሰዎቹ ነገሩት፤ ሰዎቹ እጅግ አፍረው ነበሩና ተቀባዮችን ላከ። ንጉሡም፥ “ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፤ ከዚያም በኋላ ተመለሱ” አላቸው።
6የአሞንም ልጆች የዳዊት ወገኖች እንደ አፈሩ ባዩ ጊዜ፥ የአሞን ልጆች ልከው ከቤትሮዖብ ሶርያውያንና ከሱባ ሶርያውያን ሃያ ሺህ እግረኞችን፥ ከአማሌቅ ንጉሥም አንድ ሺህ ሰዎችን፥ ከአስጦብም ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰዎችን ቀጠሩ። 7ዳዊትም በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኀያላኑን ሰራዊት ሁሉ ላከ። 8የአሞንም ልጆች ወጥተው በበሩ መግቢያ ፊት ለፊት ይዋጉ ጀመሩ፤ የሱባና የሮዖብ ሶርያውያን፥ የአስጦብና የአማሌቅም ሰዎች ለብቻቸው በሰፊ ሜዳ ላይ ነበሩ።
9ኢዮአብም በፊትና በኋላ ሰልፍ እንደ ከበበው ባየ ጊዜ ከእስራኤል ጐልማሶችን ሁሉ መረጠ፤ በሶርያውያንም ፊት አሰለፋቸው። 10የቀረውንም ሕዝብ ከወንድሙ ከአቢሳ ጋር ላከ፤ በአሞን ልጆች ፊትም አሰለፋቸው። 11እርሱም አለው፥ “ሶርያውያን ቢበረቱብኝ ትረዳኛለህ፤ የአሞን ልጆችም ቢበረቱብህ እኔ መጥቼ እረዳሃለሁ። 12በርታ፤ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንጽና፤ እግዚአብሔርም በዐይኑ ፊት ደስ ያሰኘውን መልካሙን ያድርግ።” 13ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ከሶርያውያን ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፤ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ። 14የአሞን ልጆችም ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፤ ወደ ከተማዪቱም ገቡ፤ ኢዮአብም ከአሞን ልጆች ዘንድ ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ።
15ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ በአንድነት ተሰበሰቡ። 16አድርአዛርም ልኮ በካላማቅ ወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን ሰበሰባቸው፤ ወደ ኤላምም መጡ፤ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሶቤቅ በፊታቸው ነበረ። 17ለዳዊትም ነገሩት፤ እስራኤልንም ሁሉ ሰበሰበ፤ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ ወደ ኤላም መጣ፤ ሶርያውያንም በዳዊት ፊት ተሰልፈው ከእርሱ ጋር ተዋጉ። 18ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት መቶ ሰረገለኞችን፥ አርባ ሺህም ፈረሰኞችን ገደለ፤ የሠራዊቱንም አለቃ ሶቤቅን መታ፤ እርሱም በዚያ ሞተ። 19ለአድርአዛርም የሚገብሩ ነገሥታት ሁሉ በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ለእስራኤል ተገዙ፤ ገበሩላቸውም። ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ይረዱ ዘንድ ፈሩ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 10: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ