ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2 2
2
የዐመፅ ሰው
1-2ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት “የጌታ ቀን ደርሶአል፤” ብላችሁ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን። 3ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዐመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ አይደርስምና። 4“እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤” ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው። 5ገና ከእናንተ ጋር ሳለሁ ይህን እንዳልኋችሁ ትዝ አይላችሁምን? 6በገዛ ራሱ ጊዜም ይገለጥ ዘንድ የሚከለክለውን አሁን ታውቃላችሁ። 7የዐመፅ ምሥጢር አሁን ይሠራልና፤ ብቻ ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ አሁን የሚከለክል አለ። 8በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፥ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዐመፀኛ ይገለጣል፤ 9-10ይድኑ ዘንድ የእውነት ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዐመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው። 11-12ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዐመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል።
ለድኅነት የተመረጡ ሰዎች
13እኛ ግን በጌታ የተወደዳችሁ ወንድሞች ሆይ! ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ልናመሰግን ግድ አለብን፤ እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ እውነትንም በማመን ለመዳን እንደ በኵራት መርጦአችኋልና፤ 14ለዚህም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ለማግኘት በወንጌላችን ጠራችሁ። 15እንግዲያስ ወንድሞች ሆይ! ጸንታችሁ ቁሙ፤ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ።
16-17ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የወደደን በጸጋም የዘላለምን መጽናናት በጎንም ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን ልባችሁን ያጽናኑት፤ በበጎም ሥራና በቃል ሁሉ ያጽኑአችሁ።
Currently Selected:
ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 2 2: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ