የሐዋርያት ሥራ 10
10
የመቶ አለቃዉ ቆርኔሌዎስ
1በቂሳርያም ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራም የመቶ አለቃ ነበር። 2እርሱም ጻድቅና ከነቤተ ሰቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፤ ለሕዝቡም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወትርም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር። 3የእግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በግልጥ ታየው፤ ወደ እርሱም ገብቶ፥ “ቆርኔሌዎስ ሆይ፥” አለው። 4ወደእርሱም ተመልክቶ ፈራና፥ “አቤቱ፥ ምንድን ነው?” አለ፤ መልአኩም እንዲህ አለው፥ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጎአል። 5አሁንም ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን ይጠሩልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎችን ላክ። 6እርሱም ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት እንግድነት ተቀምጦአል። ልታደርገው የሚገባህን#“አንተ ከቤተ ሰቦችህ ጋር የምትድንበትን ይነግርሃል” የሚል በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ ይገኛል። እርሱ ይነግርሃል።” 7ያነጋገረውም መልአክ ከሄደ በኋላ ከሎሌዎቹ ሁለት፥ ከማይለዩት ጭፍሮቹም አንድ ደግ ወታደር ጠራ። 8ነገሩንም ሁሉ ነግሮ ወደ ኢዮጴ ከተማ ላካቸው።
ጴጥሮስ ስለ አየው ራእይ
9በማግሥቱም ሄደው ወደ ከተማዪቱ በር ደረሱ፤ ጴጥሮስም በቀትር ጊዜ ሊጸልይ ወደ ሰገነት ወጥቶ ነበር። 10በተራበ ጊዜም ምሳ ሊበላ ወደደ፤ እነርሱም እያዘጋጁ ሳሉ ተመስጦ መጣበት። 11ሰማይም ተከፍቶ በአራቱ ማዕዘን የተያዘ እንደ ታላቅ መጋረጃ ያለ ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ። 12በውስጡም አራት እግር ያለው እንስሳ ሁሉ፥ አራዊትም፥ የሚንቀሳቀስም፥ የሰማይም ወፎች ነበሩበት። 13“ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሥና አርደህ ብላ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። 14ጴጥሮስ ግን፥ “አቤቱ፥ ከቶ አይሆንም፤ ርኩስ፥ የሚያጸይፍም ከቶ በልች አላውቅም” አለው። 15ዳግመኛም፥ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ አታርክስ” የሚል ቃል ወደ እርሱ መጣ። 16ይህንም ሦስት ጊዜ አለው፤ ወዲያውኑም ዕቃዉ ወደ ሰማይ ተመለሰ።
17ጴጥሮስም ስለ አየው ራእይ ምን እንደ ሆነ ሲያወጣና ሲያወርድ ከቆርኔሌዎስ ተልከው የመጡ ሰዎች የስምዖንን ቤት እየጠየቁ በደጅ ቁመው ነበር። 18ተጣርተውም፦ ጴጥሮስ የተባለ ስምዖን በእንግድነት በዚያ ይኖር እንደ ሆነ ጠየቁ። 19ጴጥሮስም ስለ ታየው ራእይ ሲያወጣ ሲያወርድ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አለው፥ “እነሆ፥ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል። 20ተነሥና ውረድ፤ ምንም ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ፤ እኔ ልኬአቸዋለሁና።” 21ጴጥሮስም ወደ እነዚያ ሰዎች ወረደና፥ “እነሆ፥ የምትፈልጉኝ እኔ ነኝ፤ ለምን መጥታችኋል?” አላቸው። 22እነርሱም፥ “የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ጻድቅ ሰው ነው፤ በአይሁድም ወገኖች ሁሉ የተመሰከረለት ነው፤ ቅዱስ መልአክ ተገልጦ አንተን ወደ ቤቱ እንዲጠራህ የምታስተምረውንም እንዲሰማ አዝዞታል፤” አሉት።#“እርሱም ወደ አንተ ልኮናል” የሚል በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ ይገኛል። 23እርሱም ተቀብሎ አሳደራቸው፤ በማግሥቱም ተነሥቶ አብሮአቸው ሄደ፤ በኢዮጴ ከተማ ከሚኖሩት ወንድሞችም አብረውት የሄዱ ነበሩ። 24በማግሥቱም ወደ ቂሳርያ ከተማ ገባ፤ ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ጠርቶ ይጠብቃቸው ነበር። 25ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ ከእግሩ በታችም ወድቆ ሰገደለት። 26ጴጥሮስም፥ “ተነሥ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” ብሎ አነሣው። 27ከእርሱም ጋር እየተነጋገረ ገባ፤ ወደ እርሱም የመጡ ብዙ ሰዎችን አገኘ። 28ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፥ “ለአይሁዳዊ ሰው ሄዶ ከባዕድ ወገን ጋር መቀላቀል እንደማይገባው ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን ከሰው ማንንም ቢሆን እንዳልጸየፍና ርኩስ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳየኝ። 29አሁንም ስለ ላካችሁብኝ ሳልጠራጠር ወደ እናንተ መጣሁ፤ በምን ምክንያት እንደ ጠራችሁኝ እጠይቃችኋለሁ።” 30ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፥ “የዛሬ አራት ቀን በዘጠኝ ሰዓት በዚች ሰዓት በቤቴ ስጸልይ የሚያንፀባርቅ ልብስ የለበሰ አንድ ሰው በፊቴ ቆሞ ታየኝ። 31እንዲህም አለኝ፦ ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ፤ ምጽዋትህም ታሰበልህ። 32አሁንም ወደ ኢዮጴ ከተማ ላክና በባሕር አቅራቢያ ባለችው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት የሚኖረውን ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን ይጥሩልህ፤ እርሱ መጥቶ የምትድንበትን#“አንተ ከነቤተ ሰብህ የምትድንበትን” የሚለው በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ ይገኛል። ይነግርሃል። 33ስለዚህም ወዲያውኑ ወደ አንተ ላክሁ፤ ወደ እኛ በመምጣትህም መልካም አደረግህ፤ አሁንም እግዚአብሔር ያዘዘህን ሁሉ ልንሰማ እነሆ፥ እኛ ሁላችን በእግዚአብሔር ፊት በዚህ አለን።”
የጴጥሮስ ንግግር
34 #
ዘዳ. 10፥17። ጴጥሮስም አፉን ከፈተና እንዲህ አለ፥ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንደማያዳላ በእውነት አየሁ። 35ነገር ግን በሕዝብ ሁሉ ዘንድ እርሱን የሚፈራና እውነትን የሚያደርግ በእርሱ ዘንድ የተወደደ ነው። 36ቃሉን ለእስራኤል ልጆች ላከ፤ በኢየሱስ ክርስቶስም ሰላምን ነገራቸው፤ እርሱም የሁሉ ገዢ ነው። 37ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በይሁዳ የሆነውን ነገር ሁሉ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። 38ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ በኀይልም እንደ ቀባው፥ እየዞረም መልካም እንደ አደረገ፥ ሰይጣን ያሸነፋቸውንም እንደ ፈወሰ ታውቃላችሁ። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበርና። 39በይሁዳና በኢየሩሳሌም ባደረገውም ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በዕንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። 40እግዚአብሔር ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ በግልጥ እንዲታይም አደረገው። 41ይኸውም ለሕዝቡ ሁሉ አይደለም፤ ነገር ግን አስቀድሞ ለመረጣቸውና ምስክሮች ለሚሆኑት ብቻ ነው እንጂ፤ የመረጣቸው የተባልንም እኛ ነን፤ ከሙታንም ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን። 42በእግዚአብሔር ዘንድ በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ ሆኖ የተሾመ እርሱ እንደ ሆነ ለሕዝብ እናስተምር ዘንድ አዘዘን። 43ለሚያምኑበትም ሁሉ ኀጢአታቸው በስሙ እንደሚሰረይላቸው ነቢያት ሁሉ ምስክሮቹ ናቸው።”
በምእመናን ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ስለ መውረዱ
44ጴጥሮስም ይህን ነገር ሲነግራቸው ይህን ትምህርት በሰሙት ሰዎች ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። 45ከጴጥሮስ ጋር የመጡ ከአይሁድ ወገን የሆኑ ምእመናን ሁሉ ደነገጡ፤ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በአሕዝብ ላይ ወርዶአልና። 46በልዩ ልዩ ሀገር ቋንቋ ሲናገሩ፥ እግዚአብሔርንም ሲያመሰግኑ ሰምተዋቸዋልና። 47ጴጥሮስም፥ “እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ እንግዲህ በውኃ እንዳይጠመቁ ውኃን ሊከለክላቸው የሚችል ማነው?” አለ። 48በኢየሱስ ክርስቶስም ስም እንዲጠመቁ አዘዛቸው። ከዚህም በኋላ ጥቂት ቀን አብሮአቸው እንዲቀመጥ ጴጥሮስን ማለዱት።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 10: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ