የሐዋርያት ሥራ 5
5
ስለ ሐናንያና ስለ ሚስቱ
1ሐናንያ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ሚስቱም ሰጲራ ትባል ነበር፤ መሬቱንም ሸጠ። 2ከሚስቱም ጋራ ተማክሮ የዋጋዉን እኩሌታ አስቀረ፤ የዋጋውንም እኩሌታ አምጥቶ በሐዋርያት እግር አጠገብ አስቀመጠ። 3ጴጥሮስም፥ “ሐናንያ ሆይ፥ መንፈስ ቅዱስን ታታልለው ዘንድ፥ የመሬትህንም ዋጋ ከፍለህ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ እንዴት አደረ? 4ጥንቱን ሳትሸጠው ያንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በፈቃድህ አልነበረምን? ይህን ነገር በልብህ ለምን ዐሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አላታለልህም” አለው። 5ሐናንያም ይህን በሰማ ጊዜ ወድቆ ሞተ፤ ጽኑ ፍርሀትም ሆነ፤ የሰሙትም ሁሉ ፈሩ። 6ከእነርሱም ጐልማሶች ተነሥተው ገነዙት፤ ተሸክመውም ወስደው ቀበሩት።
7ይህም ከሆነ ከሦስት ሰዓት በኋላ ሚስቱ መጣች፤ ባልዋም የሆነውን ሳታውቅ ገባች። 8ጴጥሮስም፥ “እስኪ ንገሪኝ፥ መሬታችሁን የሸጣችሁት ይህን ለሚያህል ነውን?” አላት፤ እርስዋም፥ “አዎን፥ እንዲሁ ነው” አለች። 9ጴጥሮስም፥ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን መንፈስ ትፈታተኑት ዘንድ እንዴት ተባበራችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግሮች በበር ናቸው፤ አንቺንም ይወስዱሻል” አላት። 10ያንጊዜም ከእግሩ በታች ወድቃ ሞተች፤ ጐልማሶችም በገቡ ጊዜ በድንዋን አገኙ፤ ወስደውም በባልዋ አጠገብ ቀበሩአት። 11በአብያተ ክርስቲያናትና ይህንም ነገር በሰሙት ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሀት ሆነ።
12በሐዋርያት እጅም በሕዝቡ ዘንድ ተአምራትና ድንቅ ሥራዎች ይሠሩ ነበር፤ በቤተ መቅደስም በሰሎሞን መመላለሻ በአንድነት ነበሩ። 13ሕዝቡም እጅግ ያከብሩአቸው ነበረ። ከሌሎችም ይቀርባቸው ዘንድ አንድ ስንኳን የሚደፍር አልነበረም። 14በጌታችንም የሚያምኑ ብዙዎች ይጨመሩ ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙዎች ነበሩ።
ድውያንን ስለ መፈወሳቸው
15ጴጥሮስም አልፎ ሲሄድ ጥላው ያርፍባቸው ዘንድ ድውዮችን በአልጋና በቃሬዛ እያመጡ በአደባባይ ያስቀምጡአቸው ነበር፤ 16ደግሞም በኢየሩሳሌም ዙሪያ ከአሉ ከተሞች ብዙዎች ይመጡ ነበር፤ የታመሙትንና ክፉዎች አጋንንት የያዙአቸውንም ያመጡ ነበር፥ ሁሉም ይፈወሱ ነበር።
ሊቃነ ካህናትና ሰዱቃውያን ሐዋርያትን እንደ አሳደዱአቸው
17ሊቀ ካህናቱና አብረውት የነበሩት የሰዱቃውያን ወገኖችም ቀንተው በእነርሱ ላይ ተነሡ። 18እጃቸውንም በሐዋርያት ላይ አነሡ፤ ያዙአቸውም፤ በሕዝቡ ወኅኒ ቤትም አስገቧቸው። 19የእግዚአብሔር መልአክ ግን በሌሊት የወኅኒ ቤቱን ደጃፍ ከፍቶ አወጣቸው፤ እንዲህም አላቸው። 20“ሂዱ፤ ወደ ቤተ መቅደስም ግቡና ለሕዝብ ይህን የሕይወት ቃል አስተምሩአቸው።”
21ይህንም በሰሙ ጊዜ ጥዋት ገስግሠው ወደ ቤተ መቅደስ ገቡና አስተማሩ፤ ሊቀ ካህናቱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ግን ጉባኤውንና ከእስራኤልም ቤት ሽማግሌዎችን ሁሉ ሰበሰቡ፤ ሐዋርያትንም ያመጡአቸው ዘንድ ወደ ወኅኒ ቤት ላኩ። 22አሽከሮቻቸውም መጥተው በወኅኒ ቤት አጡአቸውና ተመልሰው ነገሩአቸው። 23“ወኅኒ ቤቱንም ዙሪያውን ተዘግቶ በቍልፍም ተቈልፎ አገኘነው፤ ወታደሮቹም በሩን ይጠብቁ ነበር፤ ነገር ግን ከፍተን በገባን ጊዜ በውስጥ ያገኘነው የለም” አሉአቸው። 24ሊቃነ ካህናትና የቤተ መቅደሱ ሹምም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ፥ የሚያደርጉትን አጥተው፥ “እንጃ ይህ ምን ይሆን?” አሉ። 25አንድ ሰውም መጥቶ፥ “ያሰራችኋቸው እነዚያ ሰዎች እነሆ፥ በቤተ መቅደስ ውስጥ ናቸው፤ ቆመውም ሕዝቡን ያስተምራሉ” ብሎ ነገራቸው። 26ከዚህም በኋላ የቤተ መቅደሱ ሹም ከሎሌዎቹ ጋር ሔዶ አባብሎ አመጣቸው፤ በግድም አይደለም፤ በድንጋይ እንዳይደበድቧቸው ሕዝቡን ይፈሩ ነበርና። 27አምጥተውም በሸንጎ መካከል አቆሙአቸው፤ ሊቀ ካህናቱም መረመራቸው፤ 28#ማቴ. 27፥25። “በኢየሱስ ስም ለማንም እንዳታስተምሩ ከልክለናችሁ አልነበረምን? እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ የዚያንም ሰው ደም በእኛ ላይ ታመጡብን ዘንድ ትሻላችሁን?” አላቸው። 29ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው እንዲህ አሉአቸው፥ “ለሰው ከመታዘዝ ይልቅ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባል። 30የአባቶቻችን አምላክ፥ እናንተ ክዳችሁ በዕንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን አስነሣው። 31እግዚአብሔር እርሱን ለእስራኤል ንስሓን፥ የኀጢአትንም ስርየት ይሰጥ ዘንድ ራስም አዳኝም አደረገው፤ በቀኙም አስቀመጠው። 32እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮቹ ነን፤ እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጣቸው መንፈስ ቅዱስም ምስክር ነው።” 33ይህንም በሰሙ ጊዜ ተበሳጩ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩ፤#“ጥርሳቸውንም አፋጩ” የሚለው በግሪኩ የለም። ሊገድሉአቸውም ወደዱ።
ስለ ገማልያል ምክር
34በሸንጎዉም በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የከበረ የኦሪት መምህር ስሙን ገማልያል የሚሉት አንድ ፈሪሳዊ ተነሣ፤ ሐዋርያትንም ከጉባኤዉ ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጉአቸው አዘዘ። 35እርሱም እንዲህ አላቸው፥ “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ በእነዚህ ሰዎች በምታደርጉት ነገር ለራሳችሁ ተጠንቀቁ። 36ቀድሞም ከዚህ ዘመን በፊት ቴዎዳስ#አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ግብፃዊው ቴዎዳስ” ይላል። ተነሥቶ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ፤ አራት መቶ ሰዎችም ተከተሉት፤ ነገር ግን እርሱም ጠፋ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ፤ እንደ ኢምንትም ሆኑ። 37ከእርሱም በኋላ ሰዎች ለግብር በተቈጠሩበት ወራት ገሊላዊው ይሁዳ ተነሣ፤ ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፤ እርሱም ሞተ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ። 38አሁንም እላችኋለሁ፥ ከእነዚህ ሰዎች ራቁ፤ ተዉአቸውም፤ ይህ ምክራቸው፥ ይህም ሥራቸው ከሰው የተገኘ ከሆነ ያልፋል ይጠፋልም። 39ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን ልታፈርሱት አትችሉም፤ ከእግዚአብሔርም ጋር እንደሚጣላ አትሁኑ።”
40እሺም አሰኛቸው፤ ሐዋርያትንም ጠርተው ገረፉአቸው፤ እንግዲህ ወዲህም በኢየሱስ ስም እንዳያስተምሩ ገሥጸው ተዉአቸው። 41እነርሱም ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ፤ ስለ ስሙ መከራ ይቀበሉ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አድሎአቸዋልና። 42ሁልጊዜም በቤተ መቅደስና በቤት ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አልተዉም።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 5: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ