ትንቢተ ዳንኤል 10
10
ዳንኤል በጤግሮስ ወንዝ አጠገብ ያየው ራእይ
1በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በሦስተኛው ዓመተ መንግሥት ብልጣሶር ለተባለው ለዳንኤል ነገር ተገለጠለት፤ ነገሩም እውነት ነበረ፤ ታላቅ ኀይልና ማስተዋልም በራእዩ ውስጥ ተሰጠው። 2በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ። 3ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፤ ሥጋና የወይን ጠጅም በአፌ አልገባም፤ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም። 4ከመጀመሪያውም ወር በሃያ አራተኛው ቀን ጤግሮስ በተባለው በታላቁ ወንዝ አጠገብ ነበርሁ። 5ዐይኖችንም አነሣሁ፤ እነሆም በፍታ የለበሰውንም ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ። 6አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፤ ፊቱም እንደ መብረቅ አምሳያ ነበረ፤ ዐይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፥ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፥ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ። 7እኔም ዳንኤል ብቻዬን ራእዩን አየሁ፤ ከእኔ ጋር የነበሩ ሰዎች ግን ራእዩን አላዩም፤ ነገር ግን ታላቅ ድንጋጼ ወደቀባቸው፤ ከፍርሃትም የተነሣ ሸሹ። 8እኔም ብቻዬን ቀረሁ፤ ይህንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኀይልም አልቀረልኝም፤ ክብሬም ወደ ውርደት ተለወጠብኝ፤ ኀይልም አጣሁ። 9የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ።
10እነሆም እጅ ዳሰሰችኝ፤ እጄንም ይዞ#“እጄንም ይዞ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በጕልበቴ አቆመኝ። 11እርሱም፥ “እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ! እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፤ ቀጥ ብለህም ቁም” አለኝ። ይህንም ቃል በአለኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥሁ ቆምሁ። 12እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “ዳንኤል ሆይ! አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ከአደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፤ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ። 13የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሃያ አንድ ቀን በፊቴ ቁሞ ነበር። እነሆም ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም ከፋርስ ንጉሥ ጋር በዚያ ተውሁት። 14የራእዩም ጊዜ ገና ነውና በኋለኛው ዘመን ለሕዝብህ የሚሆነውን አስታውቅህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ።” 15ይህንም ቃል በተናገረኝ ጊዜ ፊቴን ወደ ምድር ደፋሁ፤ ዲዳም ሆንሁ። 16እነሆም የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሬን ዳሰሰኝ፤ ያን ጊዜም አፌን ከፍቼ ተናገርሁ፤ በፊቴም ቁሞ የነበረውን፥ “ጌታዬ ሆይ! ከራእዩ የተነሣ ሰውነቴ ታወከች፤ ኀይልም አጣሁ። 17አቤቱ! አገልጋይህ ከጌታዬ ጋር ይናገር ዘንድ እንዴት ይችላል? ከአሁንም ጀምሮ ኀይሌ አይጸናም፤ እስትንፋስም አልቀረልኝም” አልሁት።
18ደግሞ ሰው የሚመስል ዳሰሰኝ፤ አበረታኝም። 19እርሱም፥ “እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ! አትፍራ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ በርታ፤ ጽና፥” አለኝ። በተናገረኝም ጊዜ በረታሁና፥ “አበርትተኸኛልና ጌታዬ ይናገር” አልሁ። 20እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “ወደ አንተ የመጣሁት ስለ ምን እንደ ሆነ፥ ታውቃለህን? አሁንም የፋርስን አለቃ እወጋው ዘንድ እመለሳለሁ፤ እኔም ስወጣ፥ እነሆ የግሪኮች አለቃ ይመጣል። 21ነገር ግን በእውነት መጽሐፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ ማንም የለም።
Currently Selected:
ትንቢተ ዳንኤል 10: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ