ትንቢተ ዳንኤል 8
8
ዳንኤል በራእይ ያያቸው አውራ በግና ፍየል
1በመጀመሪያ ከተገለጠልኝ ራእይ በኋላ፥ ንጉሡ ብልጣሶር በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለእኔ ለዳንኤል ራእይ ተገለጠልኝ፤ 2በኤላም አውራጃ በአለው በሱሳ ግንብ ሳለሁ ራእይ አየሁ፤ በኡባልም ወንዝ አጠገብ ነበርሁ። 3ዐይኖችንም አቅንቼ አየሁ፤ እነሆም አንድ የበግ አውራ መጥቶ በኡባል አጠገብ ቆመ፤ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ቀንዶቹም ረዣዥሞች ነበሩ፤ አንዱ ቀንዱ ግን ከሌላው ቀንዱ ይበልጥ ነበር፤ ረዥሙም ቀንዱ በስተኋላ የበቀለ ነበር። 4አውራውም በግ ወደ ምዕራብ፥ ወደ ሰሜንም፥ ወደ ደቡብም በቅንዱ ሲጐሽም አየሁ፤ አራዊትም ሁሉ በፊቱ አይቆሙም ነበር፤ ከእጁም የሚያድን አልነበረም፤ እንደ ፈቃዱም አደረገ፤ ከፍ ከፍም አለ።
5እኔ ዳንኤልም የባሪ ክፍል በምትሆን በሱሳ ነበርሁ፤#“እኔ ዳንኤልም የባሪ ክፍል በምትሆን በሱሳ ነበርሁ” የሚለው በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ስመለከትም እነሆ ከምዕራብ ወገን አንድ አውራ ፍየል በምድር ሁሉ ፊት ላይ ወጣ፤ ምድርንም አልነካም፤ ለፍየሉም በዐይኖቹ መካከል አንድ ታላቅ ቀንድ ነበረው። 6ሁለትም ቀንድ ወደ አለው፥ በኡባል ወንዝም ፊት ቆሞ ወደ አየሁት አውራ በግ መጣ፤ በኀይሉም ቍጣ ፈጥኖ ወደ እርሱ ሮጠ። 7ወደ አውራውም በግ ቀርቦ አየሁት፤ እርሱም ዘልሎ ወጣበት፤ አውራውንም በግ መታ፤ ሁለቱንም ቀንዶች ሰበረ፤ አውራውም በግ በፊቱ ሊቆም ኀይል አልነበረውም፤ እርሱም በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፤ አውራውንም በግ ከእጁ ያድን ዘንድ የሚችል አልነበረም። 8አውራውም ፍየል ራሱን እጅግ ታላቅ አደረገ፤ በበረታም ጊዜ ታላቁ ቀንዱ ተሰበረ፤ ወደ አራቱም የሰማይ ነፋሳት የሚመለከቱ አራት ቀንዶች ከበታቹ ወጡ።
9ከእነርሱም ከአንደኛው አንድ ጠንካራ ቀንድ ወጣ፤ ወደ ደቡብም፥ ወደ ምሥራቅም፥ ወደ መልካሚቱም ምድር#“ወደ መልካሚቱ ምድር” የሚለው በዕብ. ብቻ። እጅግ ከፍ አለ። 10እስከ ሰማይም ሠራዊት ድረስ ከፍ አለ፤ ከሰማይ ሠራዊትና ከሰማይ ከዋክብትም የተወሰኑትን ወደ ምድር ጣለ፥ ረገጣቸውም። 11እስከ ሠራዊትም አለቃ ድረስ ምርኮን አዳነ፤#ዕብ. “ራሱን ታላቅ አደረገ” ይላል። ከእርሱም የተነሣ የዘወትሩ መሥዋዕት ተሻረ፤ የመቅደሱም ስፍራ ፈረሰ። 12የኀጢአትም መሥዋዕት ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ተሰጠ፤ እውነትም ወደ ምድር ተጣለች፤ አደረገም፤ ተከናወነም። 13ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ለተናገረው ለቅዱሱም ሁለተኛው ቅዱስ “ስለ ዘወትሩ መሥዋዕት፥ መቅደሱና ሠራዊቱም ይረገጡ ዘንድ ስለሚሰጥና ስለሚያጠፋ ኀጢአት የሆነው ይህ ራእይ እስከ መቼ ይቈያል?” አለው። 14እርሱም፥ “እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ማታና ጥዋት ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ መቅደሱ ይነጻል” አለኝ።
መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ራእዩን ለዳንኤል እንደ ተረጐመለት
15እኔም ዳንኤል ራእዩን በአየሁ ጊዜ ልረዳው ፈለግሁ፤ እነሆም የሰው አምሳል በፊቴ ቆሞ ነበር። 16በኡባልም ወንዝ መካከል የሰው ድምፅ ሰማሁ፤ ጠርቶም “ገብርኤል ሆይ! ራእዩን ለዚህ ሰው ግለጥለት” አለ። 17እኔም ወደ ቆምሁበት ቀረበ፤ በመጣም ጊዜ ፈርቼ በግንባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ራእዩ ለፍጻሜ ዘመን እንደ ሆነ አስተውል” አለኝ። 18ሲናገረኝም ደንግጬ በምድር ላይ በግንባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም ዳሰሰኝ፤ አንሥቶም በእግሬ አቆመኝ። 19እንዲህም አለኝ- “እነሆ በመቅሠፍቱ በመጨረሻ ዘመን የሚሆነውን አስታውቅሃለሁ፤ ይህ ገና ለፍጻሜ ዘመን ነውና። 20ያየኸው፥ ቀንዶች ያሉት አውራ በግ የሜዶንና የፋርስ ንጉሥ ነው።#ዕብ. “በአየኸው በአውራው በግ ላይ የነበሩ ሁለቱ ቀንዶች እነርሱ የሜዶንና የፋርስ ነገሥታት ናቸው” ይላል። 21አውራውም ፍየል የግሪኮች ንጉሥ ነው፤ በዐይኖቹም መካከል ያለው ታላቁ ቀንድ መጀመሪያው ንጉሥ ነው። 22እርሱም በቆመበት በተሰበረ ጊዜ በእርሱ ፋንታ አራቱ እንደ ተነሡ፤ እንዲሁ ከወገኑ አራት መንግሥታት ይነሣሉ፤ ነገር ግን በኀይል አይተካከሉትም። 23በመንግሥታቸውም መጨረሻ ኀጢአታቸው በተሞላች ጊዜ፥ እንቆቅልሽን የሚያስተውል፥ ፊቱ ጨካኝ የሆነ ንጉሥ ይነሣል። 24ኀይሉም ይበረታል፤ በተአምርም ያጠፋል፤ ያደርግማል፤ ያከናወንማል፤ ኀያላንንና ቅዱሳንን ሕዝብ ያጠፋል። 25ያንገቱን ቀንበር ያቀናል። ተንኰል በእጁ አለ፤ በልቡም ይታበያል፤ በሽንገላም ብዙዎችን ያጠፋል፤ በአለቆቹም አለቃ ላይ ይቆማል፤ ያለ እጅም ይሰብራል። 26የተነገረውም የማታውና የጥዋቱ ራእይ እውነተኛ ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ ስለሚሆን ራእዩን ዝጋ።” 27እኔም ዳንኤል ተኛሁ፤ አያሌም ቀን ታመምሁ፤ ከዚያም በኋላ ተነሥቼ የንጉሡን ሥራ እሠራ ነበር፤ ስለ ራእዩም አደንቅ ነበር፤ የሚያስተውለው ግን አልነበረም።
Currently Selected:
ትንቢተ ዳንኤል 8: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ