ኦሪት ዘዳግም 11
11
መታዘዝ የሚያስገኘው ጥቅም
1“አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ፤ ሕጉንም፥ ሥርዐቱንም፥ ትእዛዙንም፥ ፍርዱንም በዘመንህ ሁሉ ጠብቅ። 2ዛሬ ልጆቻችሁ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ተግሣጽ፥ ታላቅነቱንም፥ የጸናችም እጁን፥ የተዘረጋውንም ክንዱን፥ ያዩና ያወቁ እንዳይደሉ ዕወቁ። 3በግብፅም መካከል በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንና በሀገሩ ሁሉ ላይ ያደረጋትን ተአምራቱንና ድንቅ ሥራዉን፥ 4በተከተሉአችሁም ጊዜ በኤርትራ ባሕር ውኃ እንዳሰጠማቸው፥ እግዚአብሔርም እስከ ዛሬ ድረስ እንዳጠፋቸው፥ በግብፅ ጭፍራ በፈረሶቻቸውም፥ በሰረገሎቻቸውም ያደረገውን፥ 5ወደዚህ ስፍራ እስክትመጡ ድረስ በምድረ በዳ ያደረገላችሁን ሁሉ፥ 6በእስራኤልም ሁሉ መካከል ምድር አፍዋን ከፍታ እነርሱንና ቤተ ሰቦቻቸውን፥ ድንኳኖቻቸውንም፥ ለእነርሱም የነበራቸውን ሁሉ በዋጠቻቸው በሮቤል ልጅ በኤልያብ ልጆች በዳታንና በአቤሮን ያደረገውን ሁሉ፤ 7እግዚአብሔር ያደረጋቸውን ታላላቅ ሥራዎች ሁሉ ዐይኖቻችሁ አይተዋልና።
የተስፋይቱ ምድር በረከት
8“በሕይወት ትኖሩ ዘንድ፥ ትበዙም ዘንድ፥ ትወርሱአትም ዘንድ ዮርዳኖስን የምትሻገሩላትን ምድር እንድትወርሷት ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ጠብቁ፤ 9እግዚአብሔር ለእነርሱና ከእነርሱም በኋላ ለዘራቸው ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ይሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር ላይ ዕድሜያችሁ እንዲረዝም። 10ትወርሳት ዘንድ የምትገባባት ምድር፥ በአትክልት ስፍራ እንደሚዘሩ ዘርህን እንደ ዘራህባት፥ በእግርህም እንዳጠጣሃት፥ እንደ ወጣህባት እንደ ግብፅ ምድር አይደለችም። 11ነገር ግን ትወርሱአት ዘንድ ተሻግራችሁ የምትገቡባት ምድር ተራሮችና ሜዳዎች ያሉባት ሀገር ናት፤ በሰማይ ዝናብ ውኃ ትረካለች። 12አምላክህ እግዚአብሔር የሚጐበኛት ሀገር ናት፤ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዐይን ሁል ጊዜ በእርስዋ ላይ ነው።
13“እናንተ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩት ዘንድ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዜን ፈጽማችሁ ብትሰሙ፥ 14እህልህን፥ ወይንህንም፥ ዘይትህንም ትሰበስብ ዘንድ በየጊዜው የበልጉን ዝናብና የክረምቱን ዝናብ ለምድርህ ይሰጣል። 15በሜዳህ ለእንስሶችህ ሣርን ይሰጣል፤ ትበላማለህ፤ ትጠግብማለህ። 16ልባችሁ እንዳይስት፥ ፈቀቅ እንዳትሉ፥ ሌሎችንም አማልክት እንዳታመልኩ፥ እንዳትሰግዱላቸውም ተጠንቀቁ። 17የእግዚአብሔርም ቍጣ እንዳይነድድባችሁ፥ ዝናብም እንዳይዘንብ፥ ምድሪቱም ፍሬዋን እንዳትሰጥ ሰማይን እንዳይዘጋባችሁ፥ እግዚአብሔርም ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ፈጥናችሁ እንዳትጠፉ ተጠንቀቁ።
18“እንግዲህ እነዚህን ቃሎች በልባችሁና በነፍሳችሁ አኑሩ፤ እነርሱንም ለምልክት በእጃችሁ ላይ እሰሩአቸው፤ በዐይኖቻችሁም መካከል እንደማይንቀሳቀስ ይሁኑ። 19ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው፤ በቤትም ሲቀመጡ፥ በመንገድም ሲሄዱ፥ ሲተኙም፥ ሲነሡም እንዲነጋገሩበት፤ 20በቤትህ መቃኖችና በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው። 21በምድር ላይ የሰማይን ዘመን ያህል ይሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ በማለላቸው ምድር ዘመናችሁ የልጆቻችሁም ዘመን ይረዝም ዘንድ፤ 22አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ እርሱንም ትከተሉ ዘንድ፥ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቁ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ብትሰሙ” ይላል። ብታደርጉአትም፥ 23እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያወጣል፤ ከእናንተም የሚበልጡትን፥ የሚበረቱትንም አሕዛብ ትወርሳላችሁ። 24የእግራችሁ ጫማ የምትረግጣት ስፍራ ሁሉ ለእናንተ ትሆናለች፤ ከምድረ በዳም፥ ከአንጢሊባኖስም፥ ከታላቁም ከኤፍራጥስ ወንዝ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል። 25በእናንተም ፊት ማንም መቆም አይችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር እርሱ እንደ ተናገራችሁ፥ ማስፈራታችሁን፥ ማስደንገጣችሁንም በምትረግጡአት ምድር ሁሉ ላይ ያኖራል።
26“እነሆ፥ እኔ ዛሬ በፊታችሁ በረከትንና መርገምን አኖራለሁ፤ 27በረከትም፥ እኔ ዛሬ ለእናንተ የማዝዘውን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትሰሙ ነው፤ 28መርገምም፥ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባትሰሙ፥ ዛሬ ካዘዝኋችሁ መንገድ ፈቀቅ ብትሉ፥ ሌሎችንም የማታውቁአቸውን አማልክት ብትከተሉ፥ ብታመልኳቸውም ነው። 29አምላክህም እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ አንተን ወደምትሄድባት ምድር ባገባህ ጊዜ፥ በረከቱን በገሪዛን ተራራ፥ መርገሙንም በጌባል ተራራ ታኖራለህ። 30እነርሱም በዮርዳኖስ ማዶ፥ ከፀሐይ መግቢያ ካለችው መንገድ በኋላ በዓረባ በተቀመጡት በከነዓናውያን ምድር፥ በጌልጌላ ፊት ለፊት በረዥሙ ዛፍ አጠገብ ናቸው። 31አምላካችሁ እግዚአብሔር በዕጣችሁ ለሁልጊዜ የሚሰጣችሁን ምድር ትገቡና ትወርሱ ዘንድ ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁ፤ ትወርሱአታላችሁም፤ ትቀመጡባታላችሁም። 32እኔም ዛሬ በፊታችሁ የማኖራትን ሥርዐትና ፍርድ ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 11: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ