ኦሪት ዘዳግም 14
14
የተከለከለ የልቅሶ ልማድ
1“ለሞተ ሰውም በዐይናችሁ መካከል#“በዐይናችሁ መካከል” የሚለው በግእዝ የለም። ፊታችሁን አትንጩ፤ ራሳችሁንም አትላጩ፤ 2ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፥ በምድርም ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ለራሱ ርስት ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ” ይላል። ዘንድ እግዚአብሔር አንተን መርጦአልና።
የሚበሉና የማይበሉ እንስሶች
(ዘሌ. 11፥1-47)
3“ርኩስን ነገር ሁሉ አትብሉ። 4የምትበሉአቸው እንስሶች እነዚህ ናቸው፤ በሬ፥ በግ፥ ፍየል፥ 5ዋልያ፥ ሚዳቋ፥ የበረሃ ፍየል፥ ጎሽ፥ ብሖር፥ ሳላ፥ ድኵላ። 6ከእንስሶች ሰኰናው የተሰነጠቀውን፥ ጥፍሩም ከሁለት የተከፈለውን፥ የሚያመሰኳውንም እንስሳ ሁሉ ትበላለህ። 7ነገር ግን ከሚያመሰኩ ወይም ሰኰናቸው ከተሰነጠቀ እነዚህን አትበሉም፤ ግመልን፥ ሽኮኮን፥ ጥንቸልን አትበሉም፤ ያመሰኳሉና፥ ነገር ግን ሰኰናቸው አልተሰነጠቀምና እነዚህ ለእናንተ ርኩሳን ናቸው። 8እርያም፥ ሰኰናው ስለተሰነጠቀ፥ ጥፍሩም ከሁለት ስለተከፈለ፥ ነገር ግን ሰለማያመሰኳ፥ እርሱ ለእናንተ ርኩስ ነው፤ ሥጋዉን አትብሉ፤ በድኑንም አትንኩ።
9“በውኆች ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ የምትበሉአቸው እነዚህ ናቸው፤ ክንፍና ቅርፊትም ያላቸውን ትበላላችሁ፤ 10ክንፍና ቅርፊትም የሌላቸውን አትበሉም፤ ለእናንተ ርኩሳን ናቸው።
11“ንጹሓን የሆኑትን ወፎች ሁሉ ብሉ። 12ሊበሉ የማይገባቸው ግን እነዚህ ናቸው፤ ንስር፥ ገዴ፥ ዓሣ አውጭ። 13ጭልፊት፥ ጭላትና መሰሎቻቸው፥ 14ቍራና መሰሎቹ፤ 15ሰጎን፥ አራት ራስ አሞራ፥ ዝዪ፥ በቋል በየወገኑ። 16ጉጉት፥ ጋጋኖ፥ የውኃ ዶሮ። 17ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራና መሰሎቻቸው፥ 18ዕርኩም፥ ሽመላ፥ ሳቢሳና መሰሎቹ፥ ጅንጅላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ። 19የሚበርሩም አዕዋፍ ሁሉ ለእናንተ ንጹሓን አይደሉምና ከእነርሱ አትብሉ፤ 20ነገር ግን ንጹሓን የሆኑትን ወፎች ሁሉ ብሉ። 21የበከተዉን ሁሉ አትብሉ፤ ይበላው ዘንድ በሀገርህ ደጅ ለተቀመጠ መጻተኛ ወይም ለባዕድ ስጠው፤ አንተ ለአምላካህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ነህና፥ የፍየሉን ጠቦት በእናቱ ወተት አትቀቅል።
የዐሥራት አወጣጥ ሕግ
22“ከእርሻህ ዘርተህ በየዓመቱ ከምታገኘው እህልህ ሁሉ ዐሥራት ታወጣለህ። 23በዘመንህም ሁሉ አምላክህን እግዚአብሔርን መፍራትን ትማር ዘንድ፥ ስሙ እንዲጠራበት በመረጠው ስፍራ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት የእህልህን፥ የወይንህን፥ የዘይትህንም ዐሥራት፥ የላምህንና የበግህንም በኵራት ብላ። 24አምላክህ እግዚአብሔር ባርኮሃልና፥ መንገዱ ሩቅ ቢሆን፥ አምላክህም እግዚአብሔር ስሙን ያኖርበት ዘንድ የመረጠው ስፍራ ቢርቅብህ፥ ይህን ወደዚያ ለመሸከም ባትችል፥ 25በብር ትሸጠዋለህ፤ ብሩንም በእጅህ ይዘህ አምላክህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ትሄዳለህ። 26በዚያም በብሩ ሰውነትህ የፈለገውን፥ በሬ ወይም በግ፥ ወይም የወይን ጠጅ፥ ወይም ብርቱ መጠጥ፥ ሰውነትህ የሚሻውን ሁሉ ትገዛለህ፤ በዚያም በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ትበላዋለህ፤ አንተና ቤተ ሰብህም ደስ ይላችኋል። 27ድርሻና ርስት ከአንተ ጋር ስለሌለው በከተማህ ውስጥ ያለውን ሌዋዊ ቸል አትበል።
28“በየሦስተኛው ዓመት መጨረሻ በዚያ ዓመት የፍሬህን ዐሥራት ሁሉ አምጥተህ በከተማዎችህ ውስጥ ታኖረዋለህ። 29ሌዋዊዉም፥ ከአንተ ጋር ክፍልና ርስት የለውምና፥ በከተማህ ውስጥ ያለ መጻተኛ፥ ድሃ-አደግም፥ መበለትም መጥተው ይበላሉ፤ ይጠግባሉም፤ ይኸውም አምላክህ እግዚአብሔር በምታደርገው በእጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 14: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ