ኦሪት ዘዳግም 28
28
በታዛዥነት የሚገኝ በረከት
(ዘሌ. 26፥3-13፤ ዘዳ. 7፥12-24)
1 # ግሪክ ሰባ. ሊ. “አምላካችን እግዚአብሔር ወደሚሰጠን ምድር ለመግባት ዮርዳኖስን በተሻገርህ ጊዜ” የሚል አለው። “እንዲህም ይሆናል፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽመህ ብትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ትእዛዙን ሁሉ ብታደርግ፥ ብትጠብቅም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከምድር አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል። 2የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል፤ ያገኙህማል። 3አንተ በከተማ ቡሩክ ትሆናለህ፤ በእርሻም ቡሩክ ትሆናለህ። 4የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህም ፍሬ፥#“የከብትህም ፍሬ” የሚለው በግእዝና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። የላምህም መንጋ፥ የበግህም መንጋ ቡሩክ ይሆናል። 5መዛግብትህና የቀረውም ሁሉ ቡሩክ ይሆናል።#ዕብ. “እንቅብህና ቡሃቃህ ቡሩክ ይሆናል” ይላል። 6አንተም በመግባትህ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በመውጣትህም ቡሩክ ትሆናለህ።
7“እግዚአብሔርም ከእግርህ በታች ይወድቁ ዘንድ የሚቃወሙህን ጠላቶችህን በእጅህ ይጥላቸዋል፤ በአንድ መንገድ ይመጡብሃል፤ በሰባትም መንገድ ከፊትህ ይሸሻሉ። 8እግዚአብሔር በረከቱን በአንተ ላይ፥ በጎተራህ፥ በእህልህም ሥራ ሁሉ እንዲወርድ ይልካል፤ አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ይባርክሃል። 9የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትሰማ፥ በመንገዱም ብትሄድ፥ እግዚአብሔር ለአባቶችህ እንደ ማለ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል። 10የምድር አሕዛብም ሁሉ የአምላክህ የእግዚአብሔር ስም በአንተ ላይ እንደ ተጠራ አይተው ይፈሩሃል። 11አምላክህ እግዚአብሔርም እርስዋን ይሰጥህ ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው በምድርህ ላይ፥ በሆድህ ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ፥ ከብቶችህን በማብዛት እግዚአብሔር በጎነቱን ያበዛልሃል። 12እግዚአብሔርም ለምድርህ በወራቱ ዝናብን ይሰጥ ዘንድ፥ የእጅህንም ሥራ ሁሉ ይባርክ ዘንድ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ ለብዙ አሕዛብም ታበድራለህ፥ አንተ ግን ከማንም አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብን ትገዛለህ፥ አንተን ግን እነርሱ አይገዙህም።#“ብዙ አሕዛብን ትገዛለህ ፤ አንተን ግን እነርሱ አይገዙህም” የሚለው በዕብ. የለም። 13ዛሬም ያዘዝሁህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሰምተህ ብትጠብቃት፥ ብታደርጋትም፥ እግዚአብሔር ራስ ያደርግሃል እንጂ ጅራት አያደርግህም፤ ሁልጊዜም በላይ እንጂ በታች አትሆንም። 14ዛሬም ካዘዝሁህ ከእነዚህ ቃሎች ወደ ቀኝ፥ ወደ ግራም ፈቀቅ ባትል፥ ታመልካቸውም ዘንድ ሌሎችን አማልክት ባትከተል።
በማይታዘዙ ላይ የሚደርስ ርግማን
(ዘሌ. 26፥14-46)
15“ነገር ግን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዐቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ፥ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል፤ ያገኙህማል። 16በከተማ ርጉም ትሆናለህ፤ በእርሻም ርጉም ትሆናለህ። 17መዛግብትህና የቀረውም ርጉማን ይሆናሉ። 18የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የላምህም መንጋ፥ የበግህም መንጋ ርጉማን ይሆናሉ። 19አንተ በመግባትህና በመውጣትህም ርጉም ትሆናለህ። 20እኔን ስለተውኸኝ፥ ስለ ሥራህ ክፋት፥ እስክትጠፋ፥ ፈጥነህም እስክታልቅ ድረስ በምትሠራው ሥራ ሁሉ እግዚአብሔር ችግርን፥ ረኃብን፦ ቸነፈርንም ይልክብሃል። 21እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ከምትገባባት ምድር እስኪያጠፋህ ድረስ ሞትን ያመጣብሃል። 22እግዚአብሔር በክሳት፥ በንዳድም፥ በጥብሳትም፥ በትኵሳትም፥ በድርቅም፥ በዋግም፥ በአረማሞም ይመታሃል፤ እስክትጠፋም ድረስ ያሳድዱሃል። 23በራስህም ላይ ሰማይ ናስ ይሆንብሃል፤ ከእግርህም በታች ምድሪቱ ብረት ትሆንብሃለች። 24እግዚአብሔር የምድርህን ዝናብ ጭጋግ#ዕብ. “የምድርህን ዝናብ ትቢያና አፈር ያደርጋል” ይላል። ያደርጋል፤ እስክትጠፋም ድረስ ከሰማይ አፈር ይወርድብሃል።
25“እግዚአብሔር ከጠላቶችህ ፊት የተመታህ ያደርግሃል፤ በአንድ መንገድ ትወጣባቸዋለህ፤ በሰባት መንገድም ከእነርሱ ትሸሻለህ፤ በምድርም መንግሥታት ሁሉ የተበተንህ ትሆናለህ። 26ሬሳህ ለሰማይ ወፎች ሁሉ፥ ለምድርም አራዊት#“ለምድር አራዊት” የሚለው በግእዝ የለም። መብል ይሆናል፤ የሚቀብርህም አታገኝም።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “የሚያስፈራቸውም የለም” ይላል። 27እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በግብፅ ቍስል፥ በእባጭም፥ በቋቁቻም፥ በችፌም ይመታሃል። 28እግዚአብሔር በዕብደት፥ በዕውርነት፥ በልብ ድንጋጤም ይመታሃል። 29ዕውር በጨለማ እንደሚዳብስ በቀትር ጊዜ ትዳብሳለህ፤ መንገድህም የቀና አይሆንም፤ በዘመንህም ሁሉ የተገፋህ፥ የተዘረፍህም ትሆናለህ፤ የሚረዳህም የለም። 30ሚስት ታገባለህ፤ ሌላም ሰው ይነጥቅሃል፤ ቤት ትሠራለህ፤ በእርሱም አትቀመጥበትም፤ ወይን ትተክላለህ፤ ከእርሱም አትለቅምም። 31በሬህ በፊትህ ይታረዳል፤ ከእርሱም አትበላም። አህያህ ከእጅህ በግድ ይወሰዳል፤ ወደ አንተም አይመለስም፤ በጎችህ ለጠላቶችህ ይሰጣሉ፤ የሚረዳህም አታገኝም። 32ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ ለሌላ ሕዝብ ይሰጣሉ፤ ራሳቸውንም ሲመቱአቸው በዐይኖችህ ታያለህ፤ ልታደርገውም የምትችለው የለም። 33የምድርህን ፍሬ፥ ድካምህንም ሁሉ የማታውቀው ሕዝብ ይበላዋል፤ አንተም ሁልጊዜ የተጨነቅህ፥ የተገፋህም ትሆናለህ። 34ዐይኖችህም ከሚያዩት የተነሣ ዕብድ ትሆናለህ። 35እግዚአብሔር ልትድን በማትችልበት በክፉ ቍስል ጕልበትህንና ጭንህን ከእግርህ ጫማ እስከ አናትህ ድረስ ይመታሃል።
36“እግዚአብሔርም አንተን፥ በአንተም ላይ የምትሾማቸውን አለቆችህን#ዕብ. “የምታነግሠውን ንጉሥ” ይላል። አንተና አባቶችህ ወዳላወቃችኋቸው ሕዝብ ይወስድሃል፤ በዚያም ሌሎችን የእንጨትና የድንጋይ አማልክትን ታመልካለህ። 37እግዚአብሔርም ወደ እነርሱ በሚወስድህ አሕዛብ መካከል ሁሉ የደነገጥህ፥ ለምሳሌና ለተረትም ትሆናለህ። 38ብዙ ዘርም ወደ እርሻ ታወጣለህ፤ አንበጣም ይበላዋልና ጥቂት ትሰበስባለህ። 39ወይን ትተክላለህ፤ ታበጀውማለህ፤ ከወይኑም አትጠጣም፤ ክፉ ትልም ይበላዋልና በእርሱ ደስ አይልህም። 40የወይራ ዛፍ በሀገርህ ሁሉ ይሆንልሃል፤ ፍሬውም ይረግፋልና ዘይቱን አትቀባም። 41ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ትወልዳለህ፤ ማርከው ይወስዷቸዋልና አይቀሩልህም። 42ዛፍህን ሁሉ፤ የምድርህንም ፍሬ ሁሉ ኩብኩባ ያጠፋዋል። 43በአንተ መካከል ያለ መጻተኛ በአንተ ላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አንተ ግን ዝቅ ዝቅ ትላለህ። 44እርሱ ያበድርሃል፤ አንተ ግን አታበድረውም፤ እርሱ ራስ ይሆናል፤ አንተም ጅራት ትሆናለህ። 45የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ስላልሰማህ፥ ያዘዘህንም ትእዛዙንና ሥርዐቱን ስላልጠበቅህ፥ እስክትጠፋ ድረስ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይወርዱብሃል፤ ያሳድዱህማል፤ ያገኙህማል። 46በአንተም በልጅ ልጅህም ላይ ለዘለዓለም ለምልክትና ለድንቅ ይሆናሉ።
47“ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ#“ሁሉን አብዝቶ ስለ ሰጠህ” የሚለው በግእዝ የለም። አምላክህን እግዚአብሔርን በፍሥሓና በቀና ልብ አላመለክኸውምና፥ 48በራብና በጥማት፥ በዕራቁትነትም፥ ሁሉንም በማጣት እግዚአብሔር ለሚልክብህ ለጠላቶችህ ትገዛለህ፤ እስኪያጠፋህም ድረስ በአንገትህ ላይ የብረት ቀንበር ይጭናል። 49እግዚአብሔርም ንስር እንደሚበርር ከሩቅ ሀገር፥ ከምድር ዳር ቋንቋቸውን የማትሰማውን ሕዝብ፥ 50ፊቱ የሚያስፈራውን፥ የሽማግሌውንም ፊት የማያፍረውን፥ ሕፃኑንም የማይምረውን ሕዝብ ያመጣብሃል። 51እስክትጠፋም ድረስ የከብትህን ፍሬ፥ የምድርህንም ፍሬ ይበላል፤ እስኪያጠፋህም ድረስ እህልህን፥ ወይንህንም፥ ዘይትህንም፥ የላምህንና የበግህንም መንጋ አይተውልህም። 52በሀገርህ ሁሉ ያሉ፥ ትታመንባቸው የነበሩ፥ የረዘሙ፥ የጸኑም ቅጥሮች እስኪፈርሱ ድረስ፥ በከተሞችህ ሁሉ ያጠፋሃል፤ አምላክህም እግዚአብሔር በሰጠህ ምድር ሁሉ፥ በደጆች ሁሉ ያስጨንቅሃል። 53ጠላቶችህም በሀገርህ ውስጥ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር የሚሰጥህን የሆድህን ፍሬ፥ የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ሥጋ ትበላለህ። 54በአንተ ዘንድ የተደላደለና የተቀማጠለ ሰው በወንድሙ፥ አብራውም በምትተኛ በሚስቱ፥ በቀሩትም ልጆቹ ይቀናል፤ 55በከተሞችህ ሁሉ ውስጥ ጠላቶችህ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሌላ ነገር የቀረው የለምና ከሚበላው ከልጆቹ ሥጋ ለአንዱ አይሰጥም። 56በአንተ ዘንድ የተለሳለሰችና የተቀማጠለች፥ ከልስላሴና ከቅምጥልነት የተነሣ የእግር ጫማዋን በምድር ላይ ያላደረገችው ሴት፥ አቅፋ በተኛችው ባልዋ፥ በወንድና በሴት ልጅዋም ትቀናለች፥ 57ከአካልዋ የሚወጣውን የእንግዴ ልጅ፥ የምትወልዳቸውንም ልጆች፤#ዕብ. “በእግርዋ መካከል በሚወጣው በእንግዴ ልጅዋና በምትወልዳቸው ልጆችዋ ትቀናለች” ይላል። በደጆችህ ውስጥ ጠላቶችህ፤ ከብበው ባስጨነቁህና መከራ ባሳዩህ ጊዜ ሁሉን ስላጣች በስውር ትበላቸዋለች።
58“በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ታደርግ ዘንድ፥ ይህንም ክቡርና ምስጉን ስም እግዚአብሔር አምላክህን ትፈራ ዘንድ ባትሰማ፥ 59እግዚአብሔር መቅሠፍትህን፥ የዘርህንም መቅሠፍት፥ ታላቅና የሚያስፈራ መቅሠፍትን፥ ለብዙ ጊዜ የሚኖር ክፉ ደዌና ሕማምን ሁሉ ያመጣብሃል። 60የፈራኸውንም የግብፅ ደዌ ሁሉ እንደገና ያመጣብሃል፤ ያጣብቅብህማል። 61ደግሞም ይህ ሕግ ባለበት መጽሐፍ ውስጥ ያልተጻፈውን ደዌ ሁሉ፥ መቅሠፍትንም ሁሉ እስክትጠፋ ድረስ እግዚአብሔር ያመጣብሃል። 62የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁምና ከብዛታችሁ የተነሣ እንደ ሰማይ ከዋክብት የነበረው ቍጥራችሁ ጥቂት ሆኖ ይቀራል። 63እግዚአብሔርም በጎ ያደርግልህ ዘንድ፥ ያበዛህም ዘንድ ደስ ይለው እንደ ነበረ፥ እንዲሁ እግዚአብሔር ሲያጠፋህ፥ ሲያፈርስህም ደስ ይለዋል፤ ትወርሳትም ዘንድ ከምትገባባት ምድር ትነቀላለህ ። 64እግዚአብሔርም ከምድር ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ወደ አሉ አሕዛብ ሁሉ ይበትንሃል፤ በዚያም አንተና አባቶችህ ያላወቃችኋቸውን ሌሎችን አማልክት፥ እንጨትንና ድንጋይን ታመልካለህ። 65በእነዚያም አሕዛብ መካከል ዕረፍት አታገኝም፤ ለእግርህም ጫማ ማረፊያ አይሆንም፤ በዚያም እግዚአብሔር ተንቀጥቃጭ ልብ ፥ ፈዛዛ ዐይን፥ ደካማም ነፍስ ያመጣብሃል። 66ሕይወትህ በዐይኖችህ ፊት የተሰቀለች ትሆናለች፤#ዕብ. “ነፍስህም ታመነታለች” ይላል። ሌሊትና ቀንም ትደነግጣለህ፤ በሕይወትህም አትታመንም፤ 67ከፈራህበት ከልብህ ፍርሀት የተነሣ፥ በዐይንህም ካየኸው የተነሣ፥ ሲነጋ እንዴት ይመሽ ይሆን? ትላለህ፤ ሲመሽም እንዴት ይነጋ ይሆን? ትላለህ። 68ከእንግዲህ ወዲህ ተመልሰህ አታያትም ባልሁህ መንገድም እግዚአብሔር በመርከብ ወደ ግብፅ ይመልስሃል፤ በዚያም ለጠላቶቻችሁ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮች ትሆናላችሁ፤ የሚራራላችሁም አይኖርም።”#ዕብ.“በዚያም ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች ትሆኑአቸው ዘንድ ለጠላቶቻችሁ ራሳችሁን ትሸጣላችሁ የሚገዛችሁም አይገኝም” ይላል።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 28: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ