ኦሪት ዘዳግም 3
3
እስራኤላውያን የባሳን ንጉሥ ዐግን ድል እንደ ነሡ
(ዘኍ. 21፥31-35)
1“ተመልሰንም በባሳን መንገድ ወጣን፤ የባሳን ንጉሥ ዐግም፥ ሕዝቡም ሁሉ በኤድራይን ሊዋጉን ወጡ። 2እግዚአብሔርም፦ እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ፥ ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦን ይኖር በነበረው በአሞሬዎናውያን ንጉሥ በሴዎን ላይ እንዳደረግህ በእርሱም ታደርግበታለህ አለኝ። 3አምላካችን እግዚአብሔርም ደግሞ የባሳንን ንጉሥ ዐግን ሕዝቡንም ሁሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጠን፤ እኛም አጠፋነው፤ አንድ ሰው እንኳን ለዘር አልቀረለትም። 4በዚያን ጊዜም ከተሞቹን ሁሉ ወሰድን፤ ከእነርሱም ያልወሰድነው ሀገር የለም፤ በባሳን ያለውን የዐግን መንግሥት፥ የአርጎብን አውራጃዎች ሁሉ፥ ስድሳ ከተሞችን ወሰድን። 5እጅግ ብዙ ከሆኑት#“በቅጥር ካልተመሸጉት” ይላል። ከፌርዜዎን ከተሞች ሌላ፥ እነዚህ ከተሞች ሁሉ ቁመቱ ረዥም በሆነ ቅጥር በመዝጊያና በመወርወሪያም የተመሸጉ ነበሩ። 6በሐሴቦንም ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግን ፈጽሞ አጠፋናቸው፤ ከተሞቻቸውን ሁሉ#ዕብ. “ወንዶችንም” የሚል ይጨምራል። በአንድነት፥ የሚሸሽ ሳናስቀር ሴቶችንም፥ ሕፃናቱንም ፈጽሞ አጠፋናቸው። 7ከብቶቹን ሁሉ የከተሞቹንም ምርኮ ለእኛ ወሰድን።
8“በዚያም ዘመን ከአርኖን ሸለቆ ጀምሮ እስከ ኤርሞን ድረስ ምድሪቱን በዮርዳኖስ ማዶ ከነበሩ ከሁለቱ ከአሞሬዎን ነገሥታት እጅ ወሰድን፤ 9ፊኒቃውያን#ዕብ. “ሲዶናውያን” ይላል። ኤርሞንን “ሳኒዮር” ብለው ይጠሩታል፤ አሞሬዎናውያንም ሳኔር ብለው ይጠሩታል። 10#ዕብ. “በሜዳውም” ይላል።የሚሶርንም ከተሞች ሁሉ፥ የገለዓድንም ሁሉ፥ የባሳንንም ሁሉ እስከ ኤልከድና እስከ ኤድራይን ድረስ በባሳን የሚኖር የዐግን መንግሥት ከተሞች ሁሉ ወሰድን። 11ከራፋይንም ወገን የባሳን ንጉሥ ዐግ ብቻውን#“ብቻውን” የሚለው በግእዝና በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ቀርቶ ነበር፤ እነሆ፥ አልጋው የብረት አልጋ ነበረ፤ እርሱ በአሞን ልጆች ሀገር ዳርቻ#ዕብ. “በራባት” ይላል። አለ፤ ርዝመቱ ዘጠኝ ክንድ ወርዱም አራት ክንድ በሰው ክንድ ልክ ነበረ።
ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ የሰፈሩ ነገዶች
(ዘኍ. 32፥1-42)
12“ይህችንም ምድር በዚያን ዘመን ወረስን፤ በአርኖንም ሸለቆ አጠገብ ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ የገለዓድን ተራራማ ሀገር እኩሌታ፥ ከተሞቹንም ለሮቤልና ለጋድ ነገድ ሰጠኋቸው። 13ከገለዐድም የቀረውን የዐግን መንግሥት ባሳንን ሁሉ፥ የአርጎብንም ምድር ሁሉ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ ሰጠሁ፤ ያችም ባሳን ሁሉ የራፋይም ሀገር ተብላ ተቈጠረች። 14የምናሴ ልጅ ኢያዕር እስከ ጌርጋሴና እስከ መካቲ ዳርቻ ድረስ የአርጎብን አውራጃ ሁሉ ወሰደ፤ ይህችንም የባሳንን ምድር እስከዚች ቀን ድረስ በስሙ አውታይ ኢያዕር ብሎ ጠራ። 15ለማኪርም ገለዓድን ሰጠሁት። 16ለሮቤልና ለጋድም ከገለዓድ ምድር ጀምሮ እስከ አርኖን ሸለቆ ድረስ የሸለቆውን እኩሌታ ዳርቻውንም፥ እስከ አሞን ልጆች ዳርቻ እስከ ኢያቦቅ ወንዝ ድረስ፥ 17ከመካናራ ወሰን ከፈስጋ ተራራ በታች ወደ ምሥራቅ እስከ ዓረባ ባሕር እርሱም የጨው ባሕር ድረስ ዓረባን፥ ዮርዳኖስንም ሰጠኋቸው።
18“በዚያም ዘመን እንዲህ ብዬ አዘዝኋችሁ፦ አምላካችሁ እግዚአብሔር ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ሰጥቶአችኋል፤ መሣሪያችሁን ይዛችሁ እናንተ አርበኞች ሁሉ በወንድሞቻችሁ በእስራኤል ልጆች ፊት ትሻገራላችሁ። 19ነገር ግን እጅግ ከብቶች እንዳሉአችሁ አውቃለሁና ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ፥ ከብቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ከተሞች ይቀመጣሉ፤ 20ይኸውም እግዚአብሔር እንደ እናንተ፥ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ፥ እነርሱም ደግሞ በዮርዳኖስ ማዶ አምላካችሁ እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ ነው። ከዚያም በኋላ ሁላችሁ ወደ ሰጠኋችሁ ርስት ትመለሳላችሁ። 21በዚያም ጊዜ ኢያሱን እንዲህ ብዬ አዘዝሁት፦ አምላካችሁ እግዚአብሔር በእነዚህ በሁለቱ ነገሥት ያደረገውን ሁሉ ዐይኖችህ አይተዋል፤ እንዲሁ በምታልፍባቸው መንግሥታት ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያደርጋል። 22አምላካችሁ እግዚአብሔር እርሱ ስለ እናንተ ይዋጋልና ከእነርሱ የተነሣ አትፍሩ።
ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ መከልከሉ
23“በዚያም ዘመን እኔ እግዚአብሔርን እንዲህ ብዬ ለመንሁት፦ 24ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ታላቅነትህንና ኀይልህን፥ የጸናች እጅህንና የተዘረጋች ክንድህን#“የጸናችውን እጅህንና ከፍ ከፍ ያለች ክንድህን” የሚለው በዕብ. የለም። ለእኔ ለአገልጋይህ ማሳየት ጀምረሃል፤ በሰማይና በምድርም እንደ ሥራህ፥ እንደ ኀይልህም ይሠራ ዘንድ የሚችል አምላክ ማን ነው? 25እኔ እንድሻገርና፥ በዮርዳኖስም ማዶ ያለችውን መልካሚቱን ምድር፥ ያንም መልካሙን ተራራማውን ሀገር አንጢ ሊባኖስንም እንዳይ ፍቀድልኝ። 26እግዚአብሔር ግን በእናንተ ምክንያት ተቈጣኝ፤ አልሰማኝምም፤ እግዚአብሔርም አለኝ፦ ‘ይበቃሃል፤ በዚህ ነገር ደግመህ አትናገረኝ።’ 27ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርምና ወደ ተራራው#ዕብ. “ፈስጋ” ይላል። ራስ ውጣ፤ ዐይንህንም ወደ ባሕር ወደ መስዕም፥ ወደ አዜብም ወደ ምሥራቅም አንሥተህ በዐይንህ ተመልከት። 28ኢያሱ በዚህ ሕዝብ ፊት ይሻገራልና፥ አንተም የምታያትን ምድር እርሱ ያወርሳቸዋልና ኢያሱን እዘዘው፤ አደፋፍረውም፥ አጽናውም። 29በቤተ ፌጎርም ፊት ለፊት በሸለቆው ውስጥ ተቀመጥን።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 3: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ