መጽሐፈ መክብብ 2
2
1እኔ በልቤ፥ “ና በደስታም እፈትንሃለሁ፥ እነሆ፥ መልካምንም እይ” አልሁ፤ ይህም እነሆ፥ ከንቱ ነበረ። 2ሣቅን፥ “ሽንገላ ነህ፤ ደስታንም፦ ምን ታደርጋለህ?” አልሁት።
3የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች የሚሠሩት መልካም ነገር ምን እንደ ሆነ እስካይ ድረስ ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ደስ ለማሰኘት፥ ስንፍናንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ። 4እኔ ሥራዬን አበዛሁ፥ ቤቶችንም ለእኔ ሠራሁ፥ ወይንም ተከልሁ። 5የወይንና የአትክልት ቦታን አደረግሁ፥ ወይንና ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው። 6የሚያፈራ እንጨትንና የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያን አደረግሁ። 7ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን ገዛሁ፤ በቤት የተወለዱ አገልጋዮችም ነበሩኝ፤ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ የበጎችና የከብቶች መንጋዎች ነበሩኝ። 8ብርንና ወርቅን፥ የከበረውንም የነገሥታትንና የአውራጆችን መዝገብ ለራሴ ሰበሰብሁ፤ ሴቶችና ወንዶች አዝማሪዎችን፥ የሰዎች ልጆችንም ተድላ አደረግሁ፤ የወይን ጠጅ ጠማቂዎችንና አሳላፊዎችንም አበዛሁ። 9ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፥ ታላቅም ሆንሁ። ጥበቤም ከእኔ ጋር ጸናችልኝ። 10ዐይኖቼ ከፈለጉት ሁሉ አላጣሁም፥ ልቤንም ከደስታ ሁሉ አልከለከልሁትም፤ ልቤ በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና፤ ከድካሜም ሁሉ ይህ ዕድል ፋንታዬ ሆነ። 11እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ፥ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም።
12እኔም ጥበብን፥ ሽንገላንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ ፥ ምክርን የሚከተል፥ ምሳሌንስ ሁሉ የሚያደርግላት ሰው ማን ነው? 13እኔም ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ከአላዋቂ ይልቅ ለብልህ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከስንፍና ጥበብ እንደሚበልጥ” ይላል። ብልጫ እንዳለው ተመለከትሁ። 14የጠቢብ ዐይኖች በራሱ ላይ ናቸውና፤ አላዋቂ ግን በጨለማ ይሄዳል፤ ደግሞ የሁለቱም መጨረሻቸው አንድ እንደ ሆነ አስተዋልሁ። 15እኔም በልቤ፥ “አላዋቂን የሚያገኘው እንዲሁ እኔንም ያገኘኛል፤ እኔም ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ?” አልሁ፤ የዚያን ጊዜም በልቤ፥ “ይህ ደግሞ ከንቱ ነው” አልሁ፥ አላዋቂ በከንቱ መናገርን ያበዛልና። 16ለብልህ ከአላዋቂ ጋር ለዘለዓለም መታሰቢያ የለውም፤ እነሆ፥ ዘመን ይመጣልና ሁሉም ይረሳል፤ ብልህስ ከአላዋቂ ጋር እንዴት ይሞታል? 17ከፀሐይም በታች የተሠራው ሥራ ሁሉ በእኔ ላይ ክፉ ነውና ሕይወትን ጠላሁ፥ ሁሉም ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
18ከእኔ በኋላ ለሚወለድ ሰው እተወዋለሁና ከፀሐይ በታች እኔ የደከምሁበትን ድካም ሁሉ ጠላሁት። 19ጠቢብ ወይም አላዋቂ እንደሚሆን ከፀሐይ በታችም በደከምሁበትና ጠቢብ በሆንሁበት በድካሜ ሁሉ ይሰለጥን እንደ ሆነ የሚያውቅ ሰው ማን ነው? ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 20እኔም ተመልሼ ልቤን ከፀሐይ በታች በደከምሁበት ድካም ሁሉ ተስፋ አስቈረጥሁት። 21ሰው በጥበብና በዕውቀት በብርታትም ከደከመ በኋላ ለሌላ ላልደከመበት ሰው ዕድሉን ያወርሳልና፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ትልቅም መከራ ነው። 22ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካምና በልቡ ዐሳብ ሁሉ ለሰው አይሆንለትምና፤ 23ዘመኑ ሁሉ መከራ፥ ቍጣም፥ ቅሚያም ነው፤ ልቡም በሌሊት አይተኛም፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።
24ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት በድካሙም ለሰውነቱ መልካም ነገር ከሚያሳያት በቀር በጎ ነገር የለም፤ ይህ ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደ ተሰጠ አየሁ። 25ያለ እርሱ ፈቃድ የሚበላ ወይም የሚጠጣ ማን ነው? 26እርሱ በፊቱ ደግ ለሆነ ሰው ጥበብንና ዕውቀትን፥ ደስታንም ይሰጠዋል፤ ለኀጢአተኛ ግን በእግዚአብሔር ፊት ደግ ለሆነ ይሰጥ ዘንድ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ጥረትን ይሰጠዋል። ይህ ደግሞ ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 2: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ