ኦሪት ዘፀአት 28
28
ስለ ልብሰ ተክህኖ አሠራር
(ዘፀ. 39፥1-7)
1“አንተም ወንድምህን አሮንን ከእርሱም ጋር ልጆቹን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይተህ በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ አንተ አቅርብ፤ አሮንን የአሮንንም ልጆች፥ ናዳብን፥ አብዩድንም፥ አልዓዛርንም ኢታምርንም አቅርብ። 2የተቀደሰውንም ልብስ ለክብርና ለመለያ እንዲሆን ለወንድምህ ለአሮን ሥራለት። 3አንተም የጥበብ መንፈስ ለሞላሁባቸው፥ በልባቸው ጥበበኞች ለሆኑት ሁሉ ተናገር። እነርሱም ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ ለአሮን ለቤተ መቅደስ የሚሆን የተለየ ልብስ ይሥሩ፤ 4የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ ልብሰ እንግድዓ፥ ልብሰ መትከፍ፥ ቀሚስም፥ ዥንጕርጕር እጀ ጠባብ፥ መጠምጠሚያ፥ መታጠቂያም፤ እነዚህንም በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን፥ ለልጆቹም የተቀደሰ ልብስ ያድርጉ። 5ወርቅ፥ ሰማያዊና ሐምራዊ፥ ቀይ ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም ይውሰዱ።
6“ልብሰ መትከፉንም ከወርቅ፥ ከሰማያዊና ከሐምራዊ፥ ከተፈተለ ከቀይ ግምጃ በግብረ መርፌ የተሠራ፥ የተለየ የሽመና ሥራ ያድርጉ። 7ሁለቱ ወገን አንድ እንዲሆን በሁለቱ ጫንቃ ላይ የሚጋጠም ጨርቅ ይሁን። 8በላዩም የተጠለፈው የልብሰ መትከፍ ቋድ እንደ እርሱ፥ ከእርሱም ጋር አንድ ይሁን፤ ከወርቅ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለ፥ ከጥሩ በፍታም የተሠራ ይሁን። 9ሁለትም የመረግድ ድንጋይ ወስደህ የእስራኤልን ልጆች ስም ስማቸውን ቅረጽባቸው፤ 10እንደ አወላለዳቸው ስድስት ስሞችን በአንዱ ድንጋይ፥ የቀሩትንም ስድስቱን ስሞች በሌላው ድንጋይ ቅረጽ። 11በቅርጽ ሠራተኛ ሥራ እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በሁለት ድንጋዮች ቅረጽ፤ በወርቅም ፈርጥ አድርግ። 12ለእስራኤል ልጆችም የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ ሁለቱን ዕንቍዎች በልብሰ መትከፉ ጫንቃዎች ላይ ታደርጋለህ፤ አሮንም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ ለመታሰቢያ ስማቸውን በእግዚአብሔር ፊት ይሸከማል። 13ፈርጦችንም ከጥሩ ወርቅ ሥራ፤ 14ሁለት ቋዶችንም ከጥሩ ወርቅ እንደ ተጐነጐነ ገመድ አድርገህ ሥራ፤ የተጐነጐኑትንም ቋዶች በፈርጦቹ ላይ አንጠልጥል።
ልብሰ እንግድዓ
(ዘፀ. 39፥8-21)
15“ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ የፍርዱን ልብሰ እንግድዓ ሥራው፤ እንደ ልብሰ መትከፍም አሠራር ሥራው፤ ከወርቅና ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊም፥ ከቀይም ግምጃ፥ ከጥሩ በፍታም ሥራው። 16ርዝመቱ ስንዝር ስፋቱም ስንዝር፥ ሆኖ አራት ማዕዘን ድርብ ይሁን። 17በአራት ተራ የሆነ የዕንቍ ፈርጥ አድርግበት፤ የድንጋዮቹም ተራ ሰርድዮን፥ ጳዝዮን፥ መረግድ ነው፤ ይህም መጀመሪያው ተራ ነው፤ 18ሁለተኛውም ተራ በሉር፥#ግእዙ “ፍሕም” ይላል። ሰንፔር፥ ኢያሰጲድ፤ 19ሦስተኛውም ተራ ለግርዮን፥ አካጥስ፥ አሜቴስጢኖስ፤ 20አራተኛውም ተራ ወርቃማ ድንጋይ፥ ቢረሌ፥ ሶም በየተራቸው በወርቅ የተለበጡና የታሠሩ ይሆናሉ። 21የዕንቍም ድንጋዮች እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ዐሥራ ሁለት ይሆናሉ፤ በየስማቸውም ማኅተም አቀራረጽ ይቀረጹ፤ ስለ ዐሥራ ሁለቱ ነገዶችም ይሁኑ። 22ለልብሰ እንግድዓውም የተጐነጐኑትን ቋዶች እንደ ገመድ አድርገህ ከጥሩ ወርቅ ሥራቸው።#ምዕ. 28 ከቍ. 23 እስከ 28 ያለው ንባብ በአንዳንድ የግሪክ ሰባ. ሊ. አይገኝም። 23ለልብሰ እንግድዓውም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፤ ሁለቱንም ቀለበቶች በልብሰ እንግድዓው በሁለቱ ወገን አድርጋቸው። 24የተጐነጐኑትንም ሁለቱን የወርቅ ቋዶች በልብሰ እንግድዓው በሁለት ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለት ቀለበቶች ታገባቸዋለህ። 25የሁለቱንም ቋዶች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተህ በልብሰ መትከፉ ጫንቃዎች ላይ በስተፊት በመጋጠሚያቸው ታደርጋቸዋለህ። 26ሁለት የወርቅ ቀለበቶችንም ሥራ፤ እነርሱንም ልብሰ መትከፉ በውስጥ በሚያልፍበት በከንፈሩ በኩል በሁለቱ የልብሰ እንግድዓ ጫፎች ላይ ታኖራቸዋለህ። 27ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሥራ፤ በልብሰ መትከፉ ፊት ከጫንቃዎች በታች በብልሃት ከተጠለፈ ከልብሰ መትከፉ ቋድ በላይ በመጋጠሚያው አጠገብ ታደርጋቸዋለህ። 28ልብሰ እንግድዓውም በብልሃት ከተጠለፈ ከልብሰ መትክፉ ቋድ በላይ እንዲሆን፥ ከልብሰ መትከፉም እንዳይለይ፥ ልብሰ እንግድዓውን ከቀለበቶቹ ወደ ልብሰ መትከፉ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል ያያይዙታል። 29አሮንም ወደ መቅደስ በገባ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ለዘለዓለም መታሰቢያ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርዱ ልብሰ እንግድዓ ውስጥ በልቡ ላይ ይሸከም። 30በፍርዱ ልብሰ እንግድዓም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን#ግእዙ “መብርሂያት ወማኅተማት” ይላል። ታደርጋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ወደ ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆናሉ፤ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ የእስራኤልን ልጆች ፍርድ በልቡ ላይ ይሸከማል።
ልዩ ልዩ አልባሰ ክህነት
(ዘፀ. 39፥22-31)
31“ቀሚሱንም ሁሉ ሰማያዊ አድርገው። 32ከላይም በመካከል አንገትጌ ይሁንበት፤ እንዳይቀደድም በግብረ መርፌ የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ይሁንበት። 33በታችኛውም ዘርፍ ዙሪያ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይም ግምጃ ሮማኖችን አድርግ፤ በእነዚያም መካከል በዙሪያው በተመሳሳይ ቅርጽ የወርቅ ሮማኖች ሻኵራዎችን አድርግ፤ 34የወርቅ ሻኩራ ሮማንም፥ ሌላም የወርቅ ሻኩራ ሮማንም በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያውን ይሆናሉ። 35በማገልገል ጊዜም በአሮን ላይ ይሆናል፤ እርሱም እንዳይሞት ወደ መቅደሱ በእግዚአብሔር ፊት ሲገባና ሲወጣ ድምፁ ይሰማል።
36“ከጥሩ ወርቅም የወርቅ ቅጠል ሥራ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገህ፦ ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ትቀርጽበታለህ። 37በሰማያዊም ፈትል በመጠምጠሚያው ላይ በስተፊቱ ታንጠለጥለዋለህ ። 38በአሮንም ግንባር ላይ ይሆናል፤ አሮንም የእስራኤል ልጆች በሚያቀርቡትና በሚቀድሱት በቅዱሱ ስጦታቸው ሁሉ ላይ የሠሩትን ኀጢአት ይሸከም፤ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀባይነት ያለው እንዲሆንላቸው ሁልጊዜ በግንባሩ ላይ ይሁን። 39ቀሚሱንም ከጥሩ በፍታ ዝንጕርጕር አድርገህ፥ አክሊልን ከበፍታ ትሠራለህ፤ በጥልፍ አሠራርም መታጠቂያ ትሠራለህ። 40ለአሮንም ልጆች የበፍታ ቀሚሶችን፥ መታጠቂያዎችንም፥ ቆቦችንም ለክብርና ለመለያ ታደርግላቸዋለህ። 41ይህንም ሁሉ ወንድምህን አሮንን፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹን ታለብሳቸዋለህ፤ በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀባቸዋለህ፤ እጆቻቸውንም ታነጻለህ፤ ትቀድሳቸውማለህ። 42ኀፍረተ ሥጋቸውንም ይከድኑበት ዘንድ የተልባ እግር ሱሪ ታደርግላቸዋለህ፤ ከወገባቸውም እስከ ጭናቸው ይደርሳል፤ 43እንዲሁም ኀጢአት እንዳይሆንባቸው፥ እንዳይሞቱም፥ ወደ ምስክሩ ድንኳን ሲገቡ፥ በመቅደሱም ያገለግሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ በአሮንና በልጆቹ ላይ ይሆናል፤ ለእርሱ፥ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ለዘለዓለም ሥርዐት ይሆናል።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፀአት 28: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ