ትንቢተ ሕዝቅኤል 4
4
ሕዝቅኤል የኢየሩሳሌምን በጠላት መከበብ እንደ አስረዳ
1“አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ጡብን ወስደህ በፊትህ አኑራት፤ የኢየሩሳሌምንም ከተማ ሥዕል ሣልባት፤ 2በውስጧም የሚዋጉበት ግንብን ሥራ፤ በሠራዊትም ክበባት፤ በዙሪያዋም ጦር አስፍር፤ የሚዋጋ ጦርንም ወደ አደባባይዋ ላክ። 3የብረት ምጣድም ወስደህ በአንተና በከተማዪቱ መካከል ለብረት ቅጥር አድርገው፤ ፊትህንም ወደ እርስዋ አቅና፤ የተከበበችም ትሆናለች፤ አንተም ትከብባታለህ። ይህም ለእስራኤል ልጆች ምልክት ይሆናል።
4“አንተም በግራ ጎንህ ተኛ፤ በምትተኛበትም ቀን ቍጥር#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አንድ መቶ አምሳ” ይላል። የእስራኤልን ቤት ኀጢአት አኑርባት፤ ኀጢአታቸውንም ትሸከማለህ። 5እኔም የኀጢአታቸውን ዓመታት ለአንተ የቀን ቍጥር እንዲሆንልህ ሦስት መቶ ዘጠና#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አንድ መቶ ዘጠና” ይላል። ቀን ሰጥቼሃለሁ፤ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ፤ 6እነዚህንም በፈጸምህ ጊዜ በቀኝ ጎንህ ትተኛለህ፤ የይሁዳንም ቤት ኀጢአት አርባ ቀን ትሸከማለህ፤ አንዱን ቀን አንድ ዓመት አደረግሁልህ። 7ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ፊትህን ታቀናለህ፤ ክንድህንም ታጸናለህ፤ በእርሷም ትንቢትን ትናገራለህ። 8እነሆም ገመድ አደርግብሃለሁ፤ የምትከበብበትንም ወራት እስክትፈጽም ድረስ ከጎን ወደ ጎንህ አትገላበጥም።
9“አንተም ስንዴንና ገብስን፥ አተርንና ባቄላን፥ ምስርንና አጃን ወደ አንተ ውሰድ፤ በአንድ ዕቃም ውስጥ አድርገህ እንጀራ ጋግር፤ በጎንህ እንደ ተኛህባት ቀን ቍጥር ሦስት መቶ ዘጠና#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አንድ መቶ ዘጠና” ይላል። ቀን ትበላዋለህ። 10የምትበላውም በሚዛን በየቀኑ ሃያ ሃያ ሰቅል ይሁን፤ በየጊዜው ትበላዋለህ። 11ውኃውንም በልክ የኢን መስፈሪያ ከስድስት እጅ አንድ እጅ ትጠጣለህ፤ በየጊዜው ትጠጣዋለህ። 12የገብስ እንጎቻንም ትበላለህ፤ በሰው ኵስም ታበስለዋለህ፤ በፊታቸውም ታዳፍነዋለህ።”
13እግዚአብሔርም፥ “እንዲሁ የእስራኤል ልጆች እነርሱን በምበትንባቸው በአሕዛብ መካከል ንጹሕ ያልሆነ እንጀራቸውን ይበላሉ” አለ። 14እኔም፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ይህ አግባብ አይደለም፤ እነሆ ሰውነቴ አልረከሰችም፤ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ጥንብና አውሬ የሰበረውን ከቶ አልበላሁም፤ ርኵስም ሥጋ በአፌ ውስጥ አልገባም” አልሁ። 15እርሱም፥ “እነሆ በሰው ኵስ ፋንታ የከብት ኩበት ሰጥቼሃለሁ፤ በእርሱም እንጀራህን ትጋግራለህ” አለኝ። 16ደግሞም እንዲህ አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! የኢየሩሳሌምን እንጀራ በትር እሰብራለሁ፤ በችግር እያሉ እንጀራን በሚዛን ይበላሉ፥ እየደነገጡም ውኃን በልክ ይጠጣሉ፤ 17ይህም እንጀራንና ውኃን እንዲያጡ፥ እርስ በርሳቸውም እንዲገዳደሉ፥ በኀጢአታቸውም እንዲጠፉ ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 4: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ