ትንቢተ ኢሳይያስ 39
39
ከባቢሎን የመጡ መልእክተኞች
1በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የባልዳን ልጅ መሮዳክ ባልዳን ሕዝቅያስ ታምሞ እንደ ተፈወሰ ሰምቶ ነበርና ደብዳቤና እጅ መንሻን፥ መልእክተኞችንም ላከለት። 2ሕዝቅያስም ስለ እነርሱ እጅግ ደስ አለው፤ ግምጃ ቤቱንም፥ ወርቁንና ብሩን፥ ከርቤውንና ዕጣኑን፥ ዘይቱንም፥ መሣሪያም ያለበትን ቤት ሁሉ፥ ልብሱንና ዕንቍውን ሁሉ፥ በቤተ መዛግብቱም የተገኘውን ሁሉ አሳያቸው፤ በቤቱና በግዛቱ ሁሉ ካለው ሕዝቅያስ ያላሳያቸው የለም።
3ነቢዩም ኢሳይያስ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ መጥቶ፥ “እነዚህ ሰዎች ምን አሉ? ከወዴትስ መጡ?” አለው። ሕዝቅያስም፥ “ከሩቅ ሀገር ከባቢሎን መጡ” አለው። 4ኢሳይያስም፥ “በቤትህ ያዩት ምንድን ነው?” አለው፤ ሕዝቅያስም፥ “በቤቴ ያለውን ሁሉ አይተዋል፤ በቤቴ፥ እንዲሁም በቤተ መዛግብቴ ካለው ያላሳየኋቸው የለም” አለው። 5ኢሳይያስም ሕዝቅያስን፥ “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ። 6እነሆ፥ በቤትህ ያለው ሁሉ፥ አባቶችህም እስከ ዛሬ ድረስ ያከማቹት ሁሉ ወደ ባቢሎን የሚፈልስበት ወራት ይመጣል፤ ምንም አያስቀሩልህም፤ ይላል እግዚአብሔር። 7ከአንተ ከሚወጡት ከምትወልዳቸው ልጆችህ ማርከው ይወስዳሉ፤ በባቢሎንም ንጉሥ ቤት ውስጥ ጃንደረቦችና የቤት አሽከሮች ይሆናሉ” አለው። 8ሕዝቅያስም ኢሳይያስን፥ “እርሱ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል መልካም ነው፤ ነገር ግን፦ በዘመኔ ሰላምና ጽድቅ ይሁን” አለው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 39: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ