ትንቢተ ኢሳይያስ 42
42
የእግዚአብሔር ባለሟል
1እነሆ፥ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ ያዕቆብ፤ ነፍሴ የተቀበለችው ምርጤ እስራኤልም፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፤ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያመጣል። 2አይጮኽም፤ ቃሉንም አያነሣም፤ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። 3የተቀጠቀጠ ሸንበቆን አይሰብርም፤ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፤ ነገር ግን በእውነት ፍርድን ያመጣል። 4በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ያበራል እንጂ አይጠፋም፤ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ።
5ሰማይን የፈጠረ፥ የዘረጋውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ሁሉ ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 6“እኔ እግዚአብሔር አምላክ በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፤ በእጄም እይዝሃለሁ፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እጅህንም እይዛለሁ” ይላል። አበረታሃለሁም፤ ለልጅ ልጅ ቃል ኪዳን፥ ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ። 7የዕውራንንም ዐይን ትከፍት ዘንድ፥ የተጋዙትንም ከግዞት ቤት፥ በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ። 8እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። 9እነሆ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፤ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይነገር እርሱን አስታውቃችኋለሁ።”
10ወደ ባሕር የምትወርዱ፥ በእርስዋም ውስጥ የምትጓዙ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር ዘምሩ፤ ከምድርም ዳርቻ ስሙን አክብሩ። 11ምድረ በዳውና ከተሞችዋ፥ የቄዳርም ነዋሪዎችና መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፤ በዋሻም የሚኖሩ እልል ይበሉ፤ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። 12ለእግዚአብሔር ክብርን ይስጡ፤ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ። 13የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይወጣል፤ ኀይለኛውንም ያጠፋል፤ ቅንአትንም ያስነሣል፤ በጠላቶቹም ላይ በኀይል ይጮኻል።
14ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፤ እንግዲህ ለዘለዓለም ዝም እላለሁን? አሁን ምጥ እንደ ያዛት ሴት እታገሣለሁ፤ አጠፋለሁ፤ በአንድነትም እጨርሳለሁ። 15ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፤ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፤ ኩሬዎችንም አደርቃለሁ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ዛፎችን” ይላል። 16ዕውሮችንም በማያውቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፤ የማያውቋትንም ጎዳና እንዲረግጡ አደርጋቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፤ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህንም አደርግላቸዋለሁ፤ አልተዋቸውምም። 17በተቀረጹትም ምስሎች የሚታመኑ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች፥ “አምላኮቻችን ናችሁ” የሚሉ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ ፈጽመውም ያፍራሉ።
18እናንተ ደንቆሮች፥ ስሙ፤ እናንተም ዕውሮች እዩ፤ ተመልከቱም። 19ከባሪያዎች በቀር ዕውር ማን ነው? ከአለቆቻቸውስ በቀር ደንቆሮ የሆነ ማን ነው? የእግዚአብሔር ባሪያዎች ታወሩ። 20ብዙ ነገርን ታያላችሁ፤ ነገር ግን አትጠባበቁትም፤ ጆሮዎቻችሁም ተከፍተዋል፤ ነገር ግን አትሰሙም። 21እግዚአብሔር አምላክ ምስጋናውን ያጸድቅና ከፍ ያደርግ ዘንድ መከረ። 22እነሆ፥ ተመለከትሁ፤ ሕዝቡ የተበዘበዘና የተዘረፈ ነው፤ ወጥመድ በሁሉም ቦታ በዋሻዎችና እነርሱን በሸሸጉባቸው ቤቶች ተጠምዶአል፤ ብዝበዛ ሆነዋል፤ የሚያድንም የለም፤ ምርኮም ሆነዋል፤ የሚያስጥላቸውም የለም።
23ከመካከላችሁ ይህን የሚያደምጥ፥ ለሚመጣውም ጊዜ የሚሰማ ማን ነው? 24ያዕቆብን እንዲማርኩት፥ እስራኤልንም እንዲበዘብዙት ያደረገ ማን ነው? እነርሱም የበደሉት፥ በመንገዱም ይሄዱ ዘንድ ያልወደዱት፥ ሕጉንም ያልሰሙት እግዚአብሔር እርሱ አይደለምን? 25ስለዚህ የቍጣውን መዓትና የሰልፉን ጽናት አመጣባቸው፤ በዙሪያቸው አቃጠላቸው፤ እነርሱ ግን አላወቁም፤ በልባቸውም አላስተዋሉም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 42: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ