ትንቢተ ኢሳይያስ 51
51
የኢየሩሳሌም ዘለዓለማዊ ድኅነት
1እናንተ ጽድቅን የምትከተሉ እግዚአብሔርንም የምትሹ፥ ስሙኝ፤ የተቈረጣችሁበትን ጽኑዕ ዓለት የተቈፈራችሁባትንም ጥልቅ ጕድጓድ ተመልከቱ። 2ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፥ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ፤ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፤ ባረክሁትም፤ ወደድሁትም፤#“ወደድሁትም” የሚለው በዕብ. የለም። አበዛሁትም። 3ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ደስ አሰኝሻለሁ፤ ባድማሽንም ሁሉ ደስ አሰኛለሁ፤ ምድረ በዳሽንም እንደ ዔድን፥ በረሃዎችሽንም እንደ እግዚአብሔር ገነት አደርጋለሁ። ደስታና ተድላ እምነትና የዝማሬ ድምፅ በውስጧ ይገኝባታል።
4ሕዝቤ ሆይ፥ ስሙኝ፤ ስሙኝ፤ እናንተም ነገሥታት ተግሣጼን አድምጡኝ፤ ሕግ ከእኔ ይወጣልና፥ ፍርዴም ለአሕዛብ ብርሃን ይሆናልና። 5ጽድቄ ፈጥና ትመጣለች፤ ማዳኔም እንደ ብርሃን ትደርሳለች፤ አሕዛብ በክንዴ ይታመናሉ፤ ደሴቶች እኔን ተስፋ ያደርጋሉ፤ በክንዴም ይታመናሉ። 6ዐይኖቻችሁን ወደ ሰማይ አንሡ፤ ወደ ታችም ወደ ምድር ተመልከቱ፤ ሰማያት እንደ ጢስ በንነው ይጠፋሉ፤ ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፤ የሚኖሩባትም እንዲሁ ይሞታሉ፤ ማዳኔም ለዘለዓለም ናት፤ ጽድቄም አታልቅም።
7ፍርድን የምታውቁ፥ ሕጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብ ሆይ፥ ስሙኝ፤ የሰዎችን ስድብና ማስፈራራት አትፍሩ፤ አትሸነፉም። 8እንደ ልብስ ፈጥነው ያረጃሉና አይቈዩም፤ ብል እንደ በላውም ይሆናሉ፤ ጽድቄ ግን ለዘለዓለም፥ ማዳኔም ለልጅ ልጅ ይሆናል።
9ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ተነሺ፤ ተነሺ፤ የክንድሽንም ኀይል ልበሺ፤ እንደ ቀድሞውም ዘመን እንደ ጥንቱ ትውልድ ተነሺ። 10ባሕሩን ያደረቅሽ፥ ጥልቁንም ውኃ ያደረቅሽው፥ የዳኑትም ይሻገሩ ዘንድ ጥልቁን ባሕር ጥርጊያ ጎዳና ያደረግሽ አይደለሽምን? 11እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ፤ ወደ ጽዮንም በደስታና በሐሤት ይመጣሉ፤ የዘለዓለምም ክብር በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፤ ኀዘንና ልቅሶም ይወገዳሉ።
12እኔ ነኝ፤ የማጽናናሽ እኔ ነኝ፤ አንቺ እንግዲህ ዕወቂ፤ ማንን ፈራሽ? የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ነውን? 13አንቺ ግን ሰማያትን የፈጠረውን፥ ምድርንም የመሠረታትን ፈጣሪሽን እግዚአብሔርን ረስተሻል፤ ያጠፋሽ ዘንድ ባዘጋጀ ጊዜ ከአስጨናቂው ቍጣ የተነሣ ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ፈርተሻል፤ ይቈጣሽ ዘንድ መክሮአልና፤ አሁን የሚያስጨንቅሽ ቍጣው የት አለ? 14ከዳንሽ በኋላ እንግዲህ አይኖርምና፥ አይዘገይምምና። 15ባሕርን የማናውጥ፥ ሞገዱም እንዲተምም የማደርግ አማላክሽ እግዚአብሔር እኔ ነኝና፥ ስሜም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። 16ቃሌን በአፍሽ አደርጋለሁ፤ ሰማይን በዘረጋሁበትና ምድርን በመሠረትሁበት በእጄ ጥላ እጋርድሻለሁ፤ ጽዮንንም አንቺ ሕዝቤ ነሽ እላታለሁ።
17ከእግዚአብሔር እጅ የቍጣውን ጽዋ የጠጣሽ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ተነሺ፤ ተነሺ፤ ቁሚ፤ የሚያንገደግድሽን የቍጣውን ጽዋ ጠጥተሻልና፥ ጨልጠሽውማልና። 18ከወለድሻቸው ልጆችሽ ሁሉ የሚያረጋጋሽ አጣሽ፤ ከአሳደግሻቸውም ልጆችሽ ሁሉ እጁን ሰጥቶ የሚያነሣሽ የለም። 19አሁንም እነዚህ ሁለቱ ይጠብቁሻል፤ ማን ያስተዛዝንሻል? እነርሱም ጥፋትና ውድቀት ራብና ሰይፍ ናቸው፤ እንግዲህ የሚያጽናናሽ ማን ነው? 20ልጆችሽ ዝለዋል፤ እንደ ጠወለገ ቅጠልም በየመንገዱ ዳር ወድቀዋል፤ በአምላክሽ በእግዚአብሔር ቍጣና ተግሣጽ ተሞልተዋል።
21ስለዚህም ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ አንቺ የተዋረድሽ፥ ይህን ስሚ፤ 22ለወገኑ የሚፈርድ አምላክሽ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ፥ የሚያንገደግድሽን ጽዋ የቍጣዬንም ጽዋ ከእጅሽ ወስጃለሁ፤ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ አትጠጪውም። 23ወደ በደሉሽና ወደ አጐሰቈሉሽ ሰዎች እጅ፥ ሰውነትሽንም ዝቅ በዪ፥ ድልድይ አድርገን እንሻገርብሽ ወደሚሏት ሰዎች እጅ እመልሰዋለሁ።” በምድርም ላይ በሆድሽ አስተኙሽ፤ መንገደኞችም ሁሉ ረገጡሽ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 51: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ