ትንቢተ ኤርምያስ 14
14
ስለ ድርቅ
1ስለ ድርቅ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 2ይሁዳ አለቀሰች፤ ደጆችዋም ባዶ ሆኑ፤ በምድርም ላይ ጨለሙ፤ የኢየሩሳሌምም ጩኸት ከፍ ከፍ ብሎአል። 3ታላላቆችዋም ብላቴኖቻቸውን ወደ ውኃ ሰደዱ፤ ወደ ጕድጓድ መጡ፤ ውኃም አላገኙም፤ ዕቃቸውንም ባዶውን መለሱ፤ ዐፈሩም፤ ተዋረዱም፤ ራሳቸውንም ተከናነቡ።#“አፈሩ ፤ ተዋረዱ ፤ ራሳቸውንም ተከናነቡ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 4በምድር ላይ አልዘነበምና መሬቱ ስንጥቅጥቅ ስለ ሆነ አራሾች ዐፈሩ፤ ራሳቸውንም ተከናነቡ። 5ዋሊያዎች ደግሞ በምድረ በዳ ወለዱ፤ ሣርም የለምና ግልገሎቻቸውን ተዉ። 6የሜዳ አህዮችም በወና ኮረብታ ላይ ቆመዋል፤ እንደ ሰገኖም ወደ ነፋስ አለከለኩ፤ ሣርም የለምና ዐይኖቻቸው ጠወለጉ።
7አቤቱ! ኀጢአታችን ብዙ ነውና፥ በአንተም ላይ ኀጢአት ሠርተናልና ኀጢአታችን ተቃውሞናል፤ ነገር ግን ስለ ስምህ ብለህ አድርግ። 8ጌታ ሆይ! አንተ የእስራኤል ተስፋ ነህ፤ በመከራም ጊዜ ታድነዋለህ፤ በምድር እንደ እንግዳ፥ ወደ ማደሪያም ዘወር እንደሚል መንገደኛ ስለ ምን ትሆናለህ? 9እንዳንቀላፋ ሰው፥ ያድንም ዘንድ እንደማይችል ኀያል ስለ ምን ትሆናለህ? አንተ ግን አቤቱ! በመካከላችን ነህ፤ ስምህም በእኛ ላይ ተጠርትዋል፤ አትርሳንም።
10እግዚአብሔር ለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፥ “መቅበዝበዝን ወድደዋል፤ እግራቸውንም አልከለከሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፤ በደላቸውንም አሁን ያስባል፤ ኀጢአታቸውንም ይጐበኛል።”#“ኀጢአታቸውንም ይጐበኛል” የሚለው በዕብ. እና በግእዝ ብቻ። 11እግዚአብሔርም አለኝ፥ “ለዚህ ሕዝብ ስለ መልካም አትጸልይላቸው። 12ቢጾሙ ጸሎታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ቢያቀርቡም ደስ አልሰኝባቸውም፤ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም አጠፋቸዋለሁ።”
13እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ወዮ! እነሆ ነቢያት፦ እውነትንና ሰላምን በዚህ ስፍራ እሰጣችኋለሁ እንጂ ሰይፍን አታዩም፤ ራብም አያገኛችሁም ይሉአቸዋል” አልሁ። 14እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውም፤ የሐሰቱን ራእይ፥ ምዋርትንም፥ ከንቱንም ነገር፥ በልባቸውም የፈጠሩትን ይተነብዩላችኋል።” 15ስለዚህ እግዚአብሔር በስሜ የሐሰት ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት ስላላክኋቸው፦ በዚህች ሀገር ሰይፍና ረሃብ አይሆንም ስለሚሉ ነቢያት እንዲህ ይላል፥ “እነዚያ ነቢያት በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ። 16ትንቢት የሚናገሩላቸውም ሰዎች ከራብና ከሰይፍ የተነሣ በኢየሩሳሌም መንገዶች ይበተናሉ፤ ክፋታቸውንም አፈስስባቸዋለሁና እነርሱንና ሚስቶቻቸውን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም የሚቀብራቸው አይገኝም።
17“እንደዚህም ብለህ ትነግራቸዋለህ፦ የወገኔ ልጅ ድንግሊቱ#“ድንግሊቱ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በታላቅ ስብራትና እጅግ ክፉ በሆነ ቍስል ተሰብራለችና ዐይኖቻችሁ ሌሊትና ቀን ሳያቋርጡ እንባን ያፍስሱ። 18ወደ ሜዳ ብወጣ፥ እነሆ በሰይፍ የሞቱ አሉ፤ ወደ ከተማም ብገባ፥ እነሆ በራብ የከሱ አሉ፤ ነቢዩና ካህኑ ወደማያውቋት ሀገር ሄደዋልና።”
የሕዝቡ ምልጃ
19በውኑ ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን? ነፍስህስ ጽዮንን ጠልታታለችን? ስለ ምን መታኸን? ፈውስስ ስለ ምን የለንም? ስለ ምን ተስፋ አደረግን? ነገር ግን መልካም ነገር አልተገኘም፤ የፈውስን ጊዜ ተስፋ አደረግን፤ ነገር ግን ድንጋጤ ሆነ። 20አቤቱ በአንተ ላይ ኀጢአትን ሠርተናልና ክፋታችንንና የአባቶቻችንን በደል እናውቃለን። 21ስለ ስምህ ብለህ ተመለስልን፤ የክብርህንም ዙፋን አታጥፋ፤ ከእኛ ጋርም ያደረግኸውን ቃል ኪዳንህን አስብ እንጂ አታፍርስ። 22በውኑ በአሕዛብ ጣዖታት መካከል ያዘንብ ዘንድ የሚችል ይገኛልን? ወይስ ሰማይ ዝናብ ሊሰጥና ሊያጠግብ ይችላልን? አቤቱ አምላካችን ሆይ አንተ አይደለህምን? አንተ ይህን ነገር ሁሉ አድርገሃልና ስለዚህ አንተን በተስፋ እንጠባበቃለን።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 14: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ