ትንቢተ ኤርምያስ 19
19
የተሰበረው ገንቦ ምሳሌ
1እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ሂድ፤ የሸክላ ሠሪ የሠራውን ገምቦ ግዛ፤ ከሕዝቡም ሽማግሌዎችና ከካህናት ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤ 2በከርሲት በር መግቢያ አጠገብ ወዳለው ወደ ሄኖም ልጅ ሸለቆ ሂድ፥ በዚያም የምነግርህን ቃል አንብብ፤ እንዲህም በል፦
3“የይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በዚህ ስፍራ ክፉ ነገርን አመጣለሁ፤ የሰማውም ሰው ሁሉ ይደነግጣል፤ ጆሮዎቹንም ይይዛል። 4ትተውኛልና፥ ይህንም ስፍራ እንግዳ አድርገውታልና፥ እነርሱና አባቶቻቸውም ለማያውቋቸው ለሌሎች አማልክት ዐጥነዋልና፥ የይሁዳም ነገሥታት ይህን ስፍራ በንጹሓን ደም ሞልተዋልና፥ 5እኔም ያላዘዝሁትን፥ ያልተናገርሁትንም፥ ወደ ልቤም ያልገባውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ለበዓል ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ የበዓልን የኮረብታውን መስገጃዎች ሠርተዋልና፤ 6ስለዚህ እነሆ ይህ ስፍራ የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥” ይላል እግዚአብሔር። 7በዚህም ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ምክር አፈርሳለሁ፤ በጠላቶቻቸው ፊት በጦርና ነፍሳቸውን በሚሹት እጅ እጥላቸዋለሁ፤ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ። 8ይህችንም ከተማ ለጥፋትና ለማፍዋጫ አደርጋታለሁ፤ በእርስዋም የሚያልፍ ሁሉ ስለ ተደረገባት መቅሠፍት ሁሉ ይደነግጣል፤ ያፍዋጫልም። 9የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውንም ሥጋ አበላቸዋለሁ፤ ሁሉም እያንዳንዳቸው ጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውን የሚሹት በሚያስጨንቋቸው ጭንቀትና መከበብ የባልንጀሮቻቸውን ሥጋ ይበላሉ።
10“ገምቦውንም ከአንተ ጋር በሚሄዱ ሰዎች ፊት ትሰብራለህ፤ 11እንዲህም ትላቸዋለህ፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሸክላ ማድጋ እንደሚሰባበር ደግሞም ይጠገን ዘንድ እንደማይቻል፥ እንዲሁ ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ እሰብራለሁ፤ የሚቀበሩበትም ስፍራ ሌላ የለምና በቶፌት ይቀበራሉ።#“የሚቀበሩበትም ስፍራ ሌላ የለምና በቶፌት ይቀበራሉ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 12እንዲሁ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ አደርጋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ይህችንም ከተማ እንደ ቶፌት አደርጋለሁ፤ አፈርሳታለሁም። 13የኢየሩሳሌም ቤቶችና የይሁዳ ነገሥታት ቤቶች እንደ ቶፌት የረከሱ ይሆናሉ፤ እነዚያም በሰገነታቸው ላይ ለሰማይ ሠራዊት ሁሉ ያጠኑባቸው፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን ያፈሰሱባቸው ቤቶች ሁሉ ይፈርሳሉ።”
14ኤርምያስም እግዚአብሔር ትንቢት ሊናገር ወደዚያ ልኮት ከነበረው ስፍራ ከቶፌት ተመለሰ፤ በእግዚአብሔርም ቤት አደባባይ ቆሞ ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አላቸው፦ 15የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ቃሌን እንዳይሰሙ አንገታቸውን አደንድነዋልና እነሆ በዚች ከተማና በመንደሮችዋ ሁሉ ላይ የተናገርሁባትን ክፉ ነገር ሁሉ አመጣለሁ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 19: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ