ትንቢተ ኤርምያስ 7
7
1ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው፤ እንዲህም አለ፦#ምዕ. 7 ቍ. 1 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 2“በእግዚአብሔር ቤት በር ቁም፤ ይህንም ቃል እንዲህ ብለህ ተናገር፦ ለእግዚአብሔር ትሰግዱ ዘንድ በእነዚህ በሮች የምትገቡ#“በእግዚአብሔር ቤት በር ቁም ይህን ቃል እንዲህ ብለህ ተናገር ለእግዚአብሔር ትሰግዱ ዘንድ በእነዚህ በሮች የምትገቡ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ከይሁዳ ያላችሁ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 3የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ መንገዳችሁንና ሥራችሁን አቅኑ፤ በዚህም ስፍራ አሳድራችኋለሁ። 4የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ#ዕብ. “ሶስት ጊዜ” የእግዚአብሔር መቅደስ” ይላል። ይህ ነው እያላችሁ በሐሰት ቃል በራሳችሁ አትታመኑ። 5መንገዳችሁንና ሥራችሁን ፈጽማችሁ ብታቃኑ፥ በሰውና በጓደኛው መካከል ቅን ፍርድ ብትፈርዱ፤ 6መጻተኛውንና ድሃአደጉን፥ መበለቲቱንም ባትገፉ፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን ባታፈስሱ፥ ክፉም ሊሆንባችሁ እንግዶችን አማልክት ባትከተሉ፤ 7ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር በዚህ ስፍራ አሳድራችኋለሁ።
8“እነሆ በማትጠቀሙበት በሐሰት ቃል ብትተማመኑም፤ 9ብትገድሉም፥ ብታመነዝሩም፥ ብትሰርቁም፥ በሐሰትም ብትምሉ፥ ለበአልም ብታጥኑ፥ የማታውቋቸውንም እንግዶች አማልክት ብትከተሉ ክፉ ያገኛችኋል። 10መጥታችሁም ስሜ በተጠራበት በዚህ ቤት በፊቴ ብትቆሙ፦ ይህን አስጸያፊ የሆነ ነገርን ሁሉ ከማድረግ ተለይተናል ብትሉ፥ 11ይህ ስሜ የተጠራበት ቤት በዐይናችሁ የሌቦች ዋሻ ነውን? እነሆ፥ እኔ አይቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
12“ነገር ግን በቀድሞ ዘመን ስሜን ወዳሳደርሁበት በሴሎ ወደ ነበረው ስፍራዬ ሂዱ፤ ከሕዝቤም ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ያደረግሁበትን እዩ። 13አሁንም ይህን ነገር ሁሉ ስላደረጋችሁ፥ ተናገርኋችሁ፤ ነገር ግን አልሰማችሁም፤ ጠራኋችሁም፤ ነገር ግን አልመለሳችሁም፤ 14ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ እንዲሁ ስሜ በተጠራበት፥ እናንተም በምትተማመኑበት ቤት ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ስፍራ እንዲሁ አደርጋለሁ። 15ወንድሞቻችሁን የኤፍሬምን ዘር ሁሉ፥ እንደ ጣልሁ፥ እንዲሁ ከፊቴ እጥላችኋለሁ።”
16እግዚአብሔርም አለኝ፥ “ስለዚህ ሕዝብ አንተ አትጸልይ፤ ይቅር እላቸው ዘንድ አትማልደኝ፤ የእነርሱን ነገር አልሰማህምና ትለምንላቸው ዘንድ ወደ እኔ አትምጣ።” 17እነርሱስ በይሁዳ ከተሞች ውስጥና በኢየሩሳሌም መንገዶች የሚያደርጉትን አታይምን? 18ያስቈጡኝ ዘንድ፥ ለሰማይ ንግሥት እንጎቻ እንዲያደርጉ፥ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን እንዲያፈስሱ ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ፤ አባቶችም እሳት ያነድዳሉ፤ ሴቶችም ዱቄት ይለውሳሉ። 19እኔን ያስቈጣሉን? ይላል እግዚአብሔር፤ ፊታቸው ያፍር ዘንድ ለራሳቸው አይደለምን? 20እንግዲህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ ላይ፥ በሰውና በእንስሳ ላይ፥ በዱር ዛፎችና በምድር ፍሬ ላይ ይፈስሳል፤ ይነድዳል፤ አይጠፋምም።”
21የሠራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ከቍርባናችሁ ጋር የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን ጨምሩ፤ ሥጋውንም ብሉ። 22ከግብፅ ምድር ባወጣኋችሁ ቀን ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ቍርባን ለአባቶቻችሁ አልተናገርሁምና፥ አላዘዝኋቸውምም። 23ነገር ግን፦ ቃሌን ስሙ፤ እኔ አምላክ እሆናችኋለሁ፤ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ መልካምም ይሆንላችሁ ዘንድ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሂዱ ብዬ በዚህ ነገር አዘዝኋቸው። 24ነገር ግን በክፉ ልባቸው አሳብና እልከኝነት ሄዱ፤ ወደፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም። 25አባቶቻቸው ከግብፅ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፤ በቀንና በሌሊት ባሪያዎችን ነቢያትን ሁሉ ልኬባቸው ነበር፤ አዎ ልኬባቸዋለሁ። 26ነገር ግን አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙኝም፤ ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ አባቶቻቸውም ከአደረጉት ይልቅ የባሰ አደረጉ።
27“ይህን ሁሉ ቃል ለዚህ ሕዝብ ትነግራለህ፤ ነገር ግን አይሰሙህም፤ ትጠራቸውማለህ፤ ነገር ግን አይመልሱልህም።#“ትጠራቸውማለህ ነገር ግን አይመልሱልህም” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 28አንተም፦ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቃል ያልሰማ፥ ተግሣጽንም ያልተቀበለ ሕዝብ ይህ ነው፤ እውነት ጠፍቶአል፤ ከአፋቸውም ተቈርጦአል ትላቸዋለህ።
29“እግዚአብሔር የቍጣውን ትውልድ ጥሎአልና፥ ትቶታልምና ጠጕርሽን ቈርጠሽ፥ ጣዪው፤ በከንፈሮችሽም ሙሾ አውርጂ። 30የይሁዳ ልጆች በፊቴ ክፉ ነገርን ሠርተዋል፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ያረክሱትም ዘንድ ስሜ በተጠራበት ቤት ርኵሰታቸውን አኑረዋል። 31እኔም ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ያለችውን የቶፌትን መሥዊያዎች#ዕብ. “መስገጃዎች” ይላል። ሠርተዋል።
32“ስለዚህ እነሆ ስፍራ ከማጣት የተነሣ በቶፌት ይቀበራሉና የታረዱት ሰዎች ሸለቆ ይባላል እንጂ የቶፌት ኮረብታ ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥” ይላል እግዚአብሔር። 33የዚህ ሕዝብ ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚቀብራቸው የለምና።#ዕብ. “የሚያስፈራችህው የለምና” ይላል። 34ምድሪቱም ባድማ ትሆናለችና ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም አደባባይ የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ አጠፋለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 7: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ