መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 1
1
የከነዓን ድል መሆን
1እንዲህም ሆነ፤ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“አገልጋዬ ሙሴ ሞቶአል፤ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስን ተሻገሩ። 3ለሙሴ እንደ ነገርሁት የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ ለእናንተ ሰጥቼአለሁ። 4ከሊባኖስ ፊት ለፊት ምድረ በዳ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ የኬጤዎናውያን ምድር ሁሉ#“የኬጤዎናውያን ምድር ሁሉ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም እስከ ፀሐይ መግቢያ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ወሰናችሁ ይሆናል። 5በሕይወትህ ዘመን ሁሉ የሚቋቋምህ የለም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ ቸልም አልልህም። 6ለአባቶቻቸው እሰጣቸው ዘንድ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ በርታ። 7አገልጋዬ ሙሴ እንደ አዘዘህ ሕግን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ ጽና፤ እጅግም በርታ፤ ሁሉን እንዴት እንደምትሠራ ታውቅ ዘንድ ከእርሱ ወደ ቀኝ ወደ ግራም አትበል። 8የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፤ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አንብበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል፤ አስተዋይም ትሆናለህ። 9እነሆ አዝዝሃለሁ፤ በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፥ በርታ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም።”
10ኢያሱም የሕዝቡን ጻፎች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፦ 11“በሰፈሩ መካከል ዕለፉ፥ ሕዝቡንም፦ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ምድር እስከ ሦስት ቀን ይህን ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት ትገቡባታላችሁና ስንቃችሁን አዘጋጁ ብላችሁ እዘዙአቸው።”
12ኢያሱም ሮቤልንና ጋድን#ዕብ. “የሮቤልን ልጆችና የጋድን ልጆች” ይላል። የምናሴንም ነገድ እኩሌታ እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 13“የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ እንዲህ ብሎ ያዘዛችሁን ቃል አስቡ፦ አምላካችሁ እግዚአብሔር ያሳርፋችኋል፤ ይህችንም ምድር ይሰጣችኋል። 14ሚስቶቻችሁና ልጆቻችሁ ከብቶቻችሁም ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ በሰጣችሁ በዚች ምድር ይቀመጡ፤ እናንተ፥ ጽኑዓን ሁሉ ግን ታጥቃችሁ በወንድሞቻችሁ ፊት ዮርዳኖስን ተሻገሩ፤ ለእነርሱም ተዋጉላቸው። 15አምላካችን እግዚአብሔር እንደ እናንተ ወንድሞቻችሁን እስኪያሳርፍ ድረስ፥ እነርሱም ደግሞ አምላካችን እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ምድር እስኪወርሱ ድረስ፤ ከዚያም በኋላ ከእናንተ እያንዳንዱ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በፀሐይ መውጫ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ትገባላችሁ፤ ትወርሱአትማላችሁ።” 16እነርሱም ለኢያሱ እንዲህ ብለው መለሱለት፥ “ያዘዝኸንን ነገር ሁሉ እናደርጋለን ወደምትልከንም ስፍራ እንሄዳለን። 17በሁሉም ለሙሴ እንደ ታዘዝን እንዲሁ ለአንተ ደግሞ እንታዘዛለን፤ ብቻ አምላክህ እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን። 18ለአንተ የማይታዘዝ፥ የምታዝዘውንም ቃል የማይሰማ ሁሉ፥ እርሱ ይገደል፤ አሁንም ጽና፥ በርታ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 1: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ