መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 8
8
የጋይ ከተማ መደምሰስ
1እግዚአብሔርም ኢያሱን፥ “አትፍራ፤ አትደንግጥ፤ ተዋጊዎችን ሁሉ ከአንተ ጋር ውሰድ፤ ተነሥተህም ወደ ጋይ ውጣ፤ እነሆ፥ የጋይንም ንጉሥ፥ ሕዝቡንም ከተማውንም #“ሕዝቡንም ከተማውንም” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ምድሩንም በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ። 2በኢያሪኮና በንጉሥዋም እንዳደረግህ እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋ ታደርጋለህ፤ የከብቱን ምርኮ ግን ለራሳችሁ ትዘርፋላችሁ፤ ከከተማዪቱም በስተኋላ ይከብቧት ዘንድ ጦር ላክ” አለው።
3ኢያሱም፥ ተዋጊዎቹም ሕዝብ ሁሉ ተነሥተው ወደ ጋይ ወጡ፤ ኢያሱም ጽኑዓን፥ ተዋጊዎችና ኀያላን የሆኑትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች መረጠ፤ በሌሊትም ላካቸው። 4እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “እነሆ፥ ሂዱና ከከተማዪቱ በስተኋላ ተደበቁ፤ ከከተማዪቱ አትራቁ፤ ሁላችሁም ተዘጋጅታችሁ ተቀመጡ፤ 5እኔ፥ ከእኔም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ወደ ከተማዪቱ እንቀርባለን፤ የጋይም ሰዎች እኛን ሊገናኙ እንደ ፊተኛው በወጡ ጊዜ ከፊታቸው እንሸሻለን፤ 6ወጥተውም በተከተሉን ጊዜ ከከተማ እናርቃቸዋለን፤ እነርሱም እንደ በፊቱ ከፊታችን ሸሹ ይላሉ፤ እኛም ከፊታቸው እንሸሻለን።#“እኛም ከፊታቸው እንሸሻለን” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 7እንግዲህ እናንተም ከተደበቃችሁበት ስፍራ ተነሡ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር እርስዋን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣልና#“አምላካችሁም እግዚአብሔር እርስዋን በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣልና” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ከተማዪቱን ያዙ። 8በያዛችኋትም ጊዜ ከተማዪቱን በእሳት አቃጥሉአት፤#“በያዛችኋትም ጊዜ ከተማዪቱን በእሳት አቃጥሉአት” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። እንደ አልኋችሁ አድርጉ፤ እነሆ፥ አዝዣችኋለሁ።” 9ኢያሱም ላካቸው፤ ወደሚደበቁበትም ስፍራ ሄዱ፤ በጋይና በቤቴል መካከልም በጋይ በባሕር በኩል ተቀመጡ፤ ኢያሱ ግን በዚያች ሌሊት በሕዝቡ መካከል አደረ።#“ኢያሱ ግን በዚያች ሌሊት በሕዝቡ መካከል አደረ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
10ኢያሱም ማልዶ ተነሣ፤ ሕዝቡንም አያቸው፤ እርሱም፥ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ከሕዝቡ በፊት ወደ ጋይ ወጡ። 11ከእርሱም ጋር የነበሩ ተዋጊዎች ሕዝብ ሁሉ ወጥተው ቀረቡ፤ ወደ ከተማዪቱም ፊት ደረሱ፤ በጋይም በምሥራቅ በኩል ሰፈሩ፤ በእነርሱና በጋይም መካከል ሸለቆ ነበረ። #“በእነርሱና በጋይም መካከል ሸለቆ ነበረ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 12ኢያሱም አምስት ሺህ ሰዎችን ወስዶ በቤቴልና በጋይ መካከል በጋይ ባሕር በኩል ይከብቡ ዘንድ አስቀመጣቸው። 13ሕዝቡም ሁሉ ሠራዊቶቻቸውን በከተማው መስዕ በኩል አኖሩ፤ ዳርቻውም እስከ ከተማው ባሕር ድረስ ነው፤ ኢያሱም በዚያች ሌሊት ወደ ሸለቆው መካከል ሄደ።#ምዕ. 8 ቍ. 13 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 14የጋይም ንጉሥ በሰማ ጊዜ ፈጥኖ ሄደ። የከተማዪቱም ሰዎች ወጡ፤#“የከተማዪቱም ሰዎች ወጡ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። እርሱና ሕዝቡም ሁሉ በተወሰነው ጊዜ በዓረባ ፊት ባለው አንድ ስፍራ እስራኤልን#“በዓረባ ፊት ባለው አንድ ስፍራ እስራኤልን” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በጦርነት ተቀበሉአቸው፤ እርሱ ግን ከከተማዪቱ በስተኋላ እንደ ተደበቁ አያውቅም ነበር። 15በደረሱባቸውም ጊዜ ኢያሱና እስራኤል ሁሉ ከፊታቸው አፈገፈጉ፤ በምድረ በዳው መንገድም#“በምድረ በዳው መንገድም” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ሸሹ። 16የሀገሪቱም ሰዎች ሁሉ#“የሀገሪቱም ሰዎች ሁሉ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ተጠሩ፤ የእስራኤልንም ልጆች ተከትለው አሳደዱአቸው፤ ከከተማዪቱም እንዲርቁ አደረጓቸው። 17በጋይና በቤቴልም ውስጥ እስራኤልን ለማሳደድ ያልወጣ ሰው አልነበረም፤ ከተማዪቱንም ከፍተው ተዉ፤ እስራኤልንም አሳደዱት።
18እግዚአብሔርም ኢያሱን፥ “ጋይን በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁና በእጅህ ያለውን ጦር በላይዋ ዘርጋ፤ ከተማዪቱንም የከበቡአት ፈጥነው ከስፍራቸው ይነሣሉ” አለው፤ ኢያሱም በከተማዋ ላይ በእጁ ያለውን ጦር ዘረጋ። 19የተደበቁትም ፈጥነው ከስፍራቸው ተነሡ፤ ኢያሱም እጁን በዘረጋ ጊዜ ወጡ፤ ወደ ከተማዋም ገብተው ያዙአት፤ ፈጥነውም በእሳት አቃጠሉአት። 20የጋይም ሰዎች ወደ ኋላቸው ዞረው በተመለከቱ ጊዜ የከተማዪቱ ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ አዩ፤ ወዲህና ወዲያ መሸሽ አልቻሉም፤ ወደ ምድረ በዳም የሸሹ ሕዝብ በሚያሳድዱአቸው ላይ ተመለሱ።#“ወደ ምድረ በዳም የሸሹ ሕዝብ በሚያሳድዱአቸው ላይ ተመለሱ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 21ኢያሱ፥ እስራኤልም ሁሉ ተደብቀው የነበሩት ከተማዪቱን እንደ ያዙ፥ የከተማዪቱም ጢስ ወደ ሰማይ ሲወጣ ባዩ ጊዜ ወደኋላ ተመልሰው የጋይን ሰዎች ገደሉአቸው። 22እነዚያም ከከተማ ወጥተው ተቀበሉአቸው፤ በእስራኤል ልጆች ሠራዊት መካከልም አገቡአቸው፤ እኒያ ከወዲያ፥ እኒህም ከወዲህ ሆነው አንድ እንኳን ሳይቀርና ሳያመልጥ ገደሉአቸው። 23የጋይንም ንጉሥ ሳይሞት ይዘው ወደ ኢያሱ አመጡት።
24የእስራኤልም ልጆች ተከትለዋቸው በነበረበት በተራራው ቍልቍለትና በምድረ በዳ የጋይን ሰዎች መግደልን ከጨረሱ፥ ሁሉንም በጦር ወግተው ከአጠፉአቸው በኋላ ኢያሱ ወዲያውኑ ወደ ጋይ ተመልሶ፥ በሰይፍ አጠፋት። 25በዚያም ቀን የወደቁት ሁሉ ወንድም፥ ሴትም፥ የጋይ ሰዎች ሁሉ ዐሥራ ሁለት ሺህ ነፍስ ነበሩ። 26ኢያሱም የጋይን ሰዎች እስኪያጠፋ ድረስ ጦር የዘረጋበትን እጁን አላጠፈም።#ምዕ. 8 ቍጥር 26 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 27ነገር ግን እግዚአብሔር ኢያሱን እንዳዘዘው የዚያችን ከተማ ከብትና ምርኮ ሁሉ የእስራኤል ልጆች ለራሳቸው ዘረፉ፤ 28ኢያሱም ከተማዋን በእሳት አቃጠላት፤ ዐመድም ሆነች፤ እስከ ዛሬም ድረስ ለዘለዓለሙ የሚኖርባት እንዳይኖር አደረጋት። 29የጋይንም ንጉሥ በዝግባ ዛፍ ላይ ሰቀለው፤ እስከ ማታም ድረስ በዛፉ ላይ ቈየ። ፀሐይም በገባች ጊዜ ኢያሱ ያወርዱት ዘንድ አዘዘ፤ ከዛፉም አወረዱት፤ በከተማዪቱም በር አደባባይ ጣሉት፤ በላዩም እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ታላቅ የድንጋይ ክምር ከመሩበት።
የሙሴ ሕግ በጌባል ተራራ መነበቡ
30የዚያ ጊዜም ኢያሱ በጌባል ተራራ ላይ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ። 31የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ የእስራኤልን ልጆች እንዳዘዘ፥ በሙሴም ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው፥ መሠዊያው ካልተወቀረና ብረት ካልነካው ድንጋይ ነበረ፤ በእርሱም ላይ ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ፤ የደኅንነትንም መሥዋዕት ሠዋ። 32ኢያሱም በእስራኤል ልጆች ሁሉ ፊት በድንጋዮቹ ላይ ሙሴ የጻፈውን ይህን ሁለተኛውን ሕግ በድንጋዮች ላይ ጻፈ። 33የእስራኤልንም ሕዝብ አስቀድሞ ይባርኩአቸው ዘንድ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እንዳዘዘ፥ እስራኤል ሁሉ፥ ሽማግሌዎቻቸውም፥ ጸሓፊዎቻቸውም፥ ፈራጆቻቸውም፥ የሀገሩ ልጆችም፥ መጻተኞችም እኩሌቶቹ በገሪዛን ተራራ አጠገብ፥ እኩሌቶቹም በጌባል ተራራ አጠገብ ሆነው፥ የእግዚአብሔርን ታቦተ ሕግ በተሸከሙት በሌዋውያን ካህናት ፊት ለፊት፥ በታቦቱም ፊት በግራና በቀኝ ቆመው ነበር። 34ከዚህም በኋላ ኢያሱ በሙሴ ሕግ የተጻፈውን ሁሉ፥ የሕጉን ቃሎች ሁሉ በረከቱንና ርግማኑን አነበበ። 35ኢያሱም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ፥ በወንዶቹም፥ በሴቶቹም፥ በሕፃናቱም፥ በመካከላቸውም በሚኖሩት መጻተኞች ፊት ሙሴ ካዘዘው ያላነበበውና ያላሰማው ቃል የለም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 8: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ