ሰቆቃወ ኤርምያስ ነቢይ 1
1
የኢየሩሳሌም መከራና ኀዘን
እስራኤልን ማርከው ኢየሩሳሌምን ካጠፉአት በኋላ ኤርምያስ ተቀምጦ ያለቅስ ነበር። ለኢየሩሳሌም እንዲህ እያለ ሙሾ እያወጣ አለቀሰ።
1አሌፍ። ሕዝብ ሞልቶባት የነበረች ከተማ ብቻዋን እንዴት ተቀመጠች!
በአሕዛብ ተመልታ የነበረች እንደ መበለት ሆናለች፤
አሕዛብን ትገዛ የነበረች፥ አውራጃዎችንም ትገዛ የነበረች ገባር ሆናለች።
2ቤት። በሌሊት እጅግ ታለቅሳለች፤
እንባዋም በጉንጭዋ ላይ አለ፤
ከሚያፈቅሩአት ሁሉ የሚያጽናናት የለም፤
ወዳጆችዋም ሁሉ ወነጀሉአት፤ ጠላቶችም ሆኑአት።
3ጋሜል። ይሁዳ ስለ ውርደቷና ስለ ባርነቷ ብዛት ተሰደደች፤
በአሕዛብ መካከል ተቀመጠች፤ ዕረፍትም አላገኘችም፤
የሚያሳድዱአት ሁሉ በሚያስጨንቁአት መካከል ያዙዋት።
4ዳሌጥ። ወደ ዓመት በዓል የሚመጣ የለምና የጽዮን መንገዶች አለቀሱ፤
በሮችዋ ሁሉ ፈርሰዋል፤ ካህናቷም ያለቅሳሉ፤
ደናግሎችዋም ተማረኩ፤ እርስዋም በምሬት አለች።
5ሄ። ስለ ኀጢአቷ ብዛት እግዚአብሔር አዋርዶአታልና
የሚዘባበቱባት በራስዋ ላይ ሆኑ፤ ጠላቶችዋም ተደሰቱ፤
ሕፃናቶችዋም በአስጨናቂዎች ፊት ተማርከዋል።
6ዋው። ከጽዮን ሴት ልጅ ውበት ሁሉ ተወስዶአል፤
አለቆችዋ መሰማሪያ እንደማያገኙ አውራ በጎች ሆኑ፤
ከሚያባርሩአቸው ፊት ተዳክመው ሄዱ።
7ዛይ። ኢየሩሳሌም ቀድሞ ወድዳ በሠራችው ሥራ ሁሉ የመከራዋን ወራት አሰበች፤
ሕዝብዋ በአስጨናቂዎች እጅ በወደቀ ጊዜ፥ የሚረዳትም በሌላት ጊዜ፥
አስጨናቂዎች አዩአት፤ በመፍረስዋም ሳቁ።
8ሔት። ኢየሩሳሌም እጅግ ኀጢአት ሠርታለች፤ ስለዚህ ረክሳለች፤
በተጨነቀችበት ቦታ ያከብሩአት የነበሩ ሁሉ ውርደቷን አይተዋልና አቃለሉአት፤
እርስዋም እየጮኸች ታለቅሳለች፤ ወደ ኋላዋም ዘወር አለች።
9ጤት። ግዳጅዋ ከእግርዋ በታች ነበረ፤ ፍጻሜዋን አላሰበችም፤
ከባድ ሸክምን ተሸከመች፤ የሚያጽናናትም የለም፤
አቤቱ! ጠላት ከፍ ከፍ ብሎአልና መከራዬን ተመልከት።
10ዮድ። አስጨናቂው በምኞቷ ሁሉ ላይ እጁን ዘረጋ፤
ወደ ጉባኤህ እንዳይገቡ ያዘዝሃቸው አሕዛብ
ወደ መቅደስዋ ሲገቡ አይታለችና።
11ካፍ። ሕዝብዋ ሁሉ እንጀራ አጥተው ያለቅሳሉ፤
ሰውነታቸውን ለማበርታት ፍላጎታቸውን ስለ መብል ሰጥተዋል፤
አቤቱ! ተጐሳቍያለሁና እይ፤ ተመልከትም።
12ላሜድ። እናንተ መንገድ ዐላፊዎች ሁሉ! በእናንተ ዘንድ ምንም የለምን?
እግዚአብሔር በጽኑ ቍጣው ቀን እኔን እንዳስጨነቀበት
በእኔ ላይ እንደ ተደረገው እንደ እኔ ቍስል የሚመስል ቍስል እንዳለ ተመልከቱ፤ እዩም።
13ሜም። ከላይ እሳትን ሰደደ፤ አጥንቶችንም አቃጠለ፤
ለእግሬ ወጥመድ ዘረጋ፤ ወደ ኋላም መለሰኝ፥
አጠፋኝም፤ ቀኑንም ሁሉ መከራ አጸናብኝ።
14ኖን። በእጄ ስለተታቱ ኀጢአቶች ተጋ፤
በአንገቴ ላይ ወጥተዋል፤ ጕልበቴ ደከመ።
እግዚአብሔር ልቋቋመው በማልችለው መከራ እጅ ሰጥቶኛልና።
15ሳምኬት። እግዚአብሔር ኀያላኖችን ሁሉ ከመካከሌ አስወገዳቸው፤
ምርጦችን#ዕብ. “ጐልማሶችን” ይላል። ያደቅቅ ዘንድ ጊዜን#ዕብ. “ጉባኤን” ይላል። ጠራብኝ፤
እግዚአብሔር ድንግሊቱን የይሁዳን ልጅ በመጭመቂያ እንደሚጨመቅ ወይን ረገጣት።
ስለዚህም አለቅሳለሁ።
16ዔ። የሚያጽናናኝ፥ ነፍሴንም የሚመልሳት ከእኔ ርቆአልና ዐይኔ ውኃ ያፈስሳል።
ጠላት በርትቶአልና ልጆች ጠፍተዋል።
17ፌ። ጽዮን እጅዋን ዘረጋች፤ የሚያጽናናትም የለም፤
እግዚአብሔር በያዕቆብ ዙሪያ ያሉትን እንዲያስጨንቁት አዘዘ፤
ኢየሩሳሌም በመካከላቸው እንደ ረከሰች ሆናለች።
18ጻዴ። ቃሉን አማርሬአለሁና እግዚአብሔር ጻድቅ ነው።
እናንተ አሕዛብ ሁሉ እባካችሁ ስሙ፤ መከራዬንም ተመልከቱ፤
ደናግሎችና ጐልማሶች ተማርከው ሄደዋልና።
19ቆፍ። ወዳጆችን ጠራሁ፤ እነርሱም ቸል አሉኝ፤
ካህናቶችና ሽማግሌዎች ሰውነታቸውን ያበረቱ ዘንድ
መብል ሲፈልጉ በከተማ ውስጥ ሳያገኙ አለቁ።
20ሬስ። አቤቱ! ተጨንቄአለሁና፥ አንጀቴም ታውኮብኛልና ተመልከት፤
መራራ ኀዘን አዝኛለሁና ልቤ በውስጤ ተገላበጠብኝ፤
በሜዳ ሰይፍ አመከነችኝ፤ በቤትም ሞት አለ።
21ሣን። እኔ እንደማለቅስ ሰምተዋል፤ የሚያጽናናኝ የለም፤
ጠላቶች ሁሉ መከራዬን ሰምተዋል፤ አንተ አድርገኸዋልና ደስ አላቸው፤
ስለ እርሱ የተናገርኸውን ቃል ታመጣለህ፤ እነርሱም እንደ እኔ ይሆናሉ።
22ታው። ልቅሶዬ እጅግ ነውና፥ ልቤም ደክሞአልና፥
ክፋታቸው ሁሉ ወደ ፊትህ ይድረስ፥
ስለ ኀጢአቴ ሁሉ እኔን እንደ ቃረምኸኝ እነርሱን ቃርማቸው።
Currently Selected:
ሰቆቃወ ኤርምያስ ነቢይ 1: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ