የሉቃስ ወንጌል 15
15
ስለ ባለ መቶ በጎች ምሳሌ
1ቀራጮችና ኀጢኣተኞችም ሊሰሙት ወደ እርሱ ይቀርቡ ነበር። 2#ሉቃ. 5፥29-30። ጻፎችና ፈሪሳውያንም፥ “ይህስ ኀጢኣተኞችን ይቀበላል፤ አብሮአቸውም ይበላል” ብለው አንጐራጐሩ። 3እንዲህም ብሎ መሰለላቸው። 4“ከእናንተ መካከል መቶ በጎች ያሉት ሰው ቢኖር፥ ከእነርሱ አንዲቱ ብትጠፋው ዘጠና ዘጠኙን በምድረ በዳ ትቶ እስኪያገኛት ድረስ ይፈልጋት ዘንድ ወደ ጠፋችው ይሄድ የለምን? 5በአገኛትም ጊዜ ደስ ብሎት በትከሻው ላይ ይሸከማታል። 6ወደ ቤቱም በገባ ጊዜ፥ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹን ጠርቶ፦ የጠፋችኝን በጌን አግኝቼአታለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ይላቸዋል። 7እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሓ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኙ ጻድቃን ይልቅ ንስሓ ስለሚገባ ስለ አንድ ኀጢኣተኛ በሰማያት ፍጹም ደስታ ይሆናል።
ድሪም ስለ ጠፋባት ሴት
8“ዐሥር ድሪም ያላት ሴት ብትኖር፥ አንዲቱ ብትጠፋባት መብራት አብርታ በቤቷ ያለውን ሁሉ እየፈነቀለች እስክታገኛት ድረስ ተግታ ትፈልግ የለምን? 9ያገኘቻት እንደ ሆነም ወዳጆችዋንና ጎረቤቶችዋን ጠርታ፦ ‘የጠፋችኝን ድሪሜን አግኝቼአታለሁና፥ ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ’ ትላቸዋለች። 10እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሓ ስለሚገባ ስለ አንድ ኀጢኣተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት በሰማያት#“በሰማያት” የሚለው በግሪኩና በአንዳንድ የግእዝ ዘርዕ የለም። ደስታ ይሆናል።”
ሁለት ልጆች ስላሉት ሰው
11ዳግመኛም እንዲህ አለ፥ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። 12ታናሹ ልጁም አባቱን፦ ‘አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ከፍለህ ስጠኝ’ አለው፤ ገንዘቡንም ከፍሎ ሰጠው። 13ከጥቂት ቀን በኋላም ያ ትንሹ ልጁ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ ሀገር ሄደ፤ በዚያም በመዳራት እየኖረ ገንዘቡን ሁሉ በተነ፤ አጠፋም። 14ገንዘቡንም ሁሉ በጨረሰ ጊዜ፥ በዚያ ሀገር ጽኑ ራብ መጣ፤ እርሱም ተቸገረ። 15ሄዶም ከዚያ ሀገር ሰዎች ለአንዱ ተቀጠረ፤ እሪያዎችንም ይጠብቅ ዘንድ ወደ እርሻው ቦታ ሰደደው። 16እሪያዎች ከሚመገቡት ተረንቃሞም ይጠግብ ዘንድ ተመኘ፤ ግን የሚሰጠው አልነበረም። 17በልቡም እንዲህ ብሎ ዐሰበ፦ እህል የሚተርፋቸው የአባቴ ሠራተኞች ምን ያህል ናቸው? እኔ ግን በዚህ በረኃብ ልሞት ነው። 18ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና እንዲህ ልበለው፦ ‘አባቴ ሆይ፥ በሰማይም፥ በፊትህም በደልሁ። 19እንግዲህ ወዲህስ ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ።’ 20ተነሥቶም ወደ አባቱ ሄደ፤ አባቱም ከሩቅ አየውና ራራለት፤ ሮጦም አንገቱን አቅፎ ሳመው። 21ልጁም፦ ‘አባቴ ሆይ፥ በሰማይም፥ በፊትህም በደልሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ነገር ግን ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ’#“ነገር ግን ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ” የሚለው በግሪኩ የለም። አለው። 22አባቱም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ያማሩ ልብሶችን ቶሎ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱም ቀለበት፥ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤’ 23የሰባውን ፍሪዳም አምጡና እረዱ፤ እንብላ፤ ደስም ይበለን። 24ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኖአልና፥ ጠፍቶም ነበር፤ ተገኝቶአልና ደስ ይላቸውም ጀመር።
25“ታላቁ ልጁም በእርሻ ነበርና ተመልሶ ወደ ቤቱ አጠገብ በደረሰ ጊዜ የዘፈኑንና የመሰንቆውን ድምፅ ሰማ። 26ከአባቱ ብላቴኖችም አንዱን ጠርቶ፦ ‘ይህ የምሰማው ምንድን ነው?’ አለው። 27እርሱም፦ ‘ወንድምህ ከሄደበት መጣ፤ አባትህም የሰባውን ፍሪዳ አረደ፤ በሕይወት አግኝቶታልና’ አለው። 28ተቈጥቶም ‘አልገባም’ አለ፤ አባቱም ወጥቶ ማለደው። 29መልሶም አባቱን እንዲህ አለው፦ ‘እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት ተገዛሁልህ፤ ፈጽሞ ከትእዛዝህ አልወጣሁም፤ ለእኔ ግን ከባልንጀሮች ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ የፍየል ጠቦት እንኳ አልሰጠኸኝም። 30ከአመንዝሮች ጋር ገንዘብህን ሁሉ የጨረሰ ይህ ልጅህ በተመለሰ ጊዜ ግን የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት።’ 31አባቱም እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ አንተማ እኮ ዘወትር ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው። 32ነገር ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ፤ ሕያው ሆኖአልና፥ ጠፍቶም ተገኝቶአልና፥ ደስ ሊለን፥ ሐሤትም ልናደርግ ይገባል።”
Currently Selected:
የሉቃስ ወንጌል 15: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ