የማርቆስ ወንጌል 1
1
የመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት
(ማቴ. 3፥1-12፤ ሉቃ. 3፥1-18፤ ዮሐ. 1፥19-28)
1የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ።
2-3“እነሆ፥ መንገድህን የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ፤
‘የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ፤’ እያለ
በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ”
ተብሎ በነቢዩ በኢሳይያስ እንደ ተጻፈ፥ 4ዮሐንስ በምድረ በዳ እያጠመቀ የንስሐንም ጥምቀት ለኀጢአት ስርየት እየሰበከ መጣ። 5የይሁዳም አገር ሁሉ የኢየሩሳሌምም ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤ ኀጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። 6ዮሐንስም የግመል ጠጉር ለብሶ በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ አንበጣና የበረሓ ማርም ይበላ ነበር። 7“ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል። 8እኔ በውሃ አጠመቅኋችሁ፤ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል፤” እያለ ይሰብክ ነበር።
የጌታችን የኢየሱስ መጠመቅ
(ማቴ. 3፥13-17፤ ሉቃ. 3፥21-22)
9በዚያ ወራትም ኢየሱስ ከገሊላ ናዝሬት መጥቶ ከዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ። 10ወዲያውም ከውሃው በወጣ ጊዜ ሰማያት ሲቀደዱ መንፈስም እንደ ርግብ ሲወርድበት አየና “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፤ 11በአንተ ደስ ይለኛል፤” የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መፈተን
(ማቴ. 4፥1-11፤ ሉቃ. 4፥1-13)
12ወዲያውም መንፈስ ወደ ምድረ በዳ አወጣው። 13በምድረ በዳም ከሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ሰነበተ፤ ከአራዊትም ጋር ነበረ፤ መላእክቱም አገለገሉት።
ኢየሱስ የማስተማር ሥራውን በገሊላ እንደ ጀመረ
(ማቴ. 4፥14-17፤ ሉቃ. 4፥14-15)
14ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና 15“ዘመኑ ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሐ ግቡ፤ በወንጌልም እመኑ፤” እያለ ወደ ገሊላ መጣ።
ኢየሱስ አራት ዓሣ አጥማጆችን እንደጠራ
(ማቴ. 4፥18-22፤ ሉቃ. 4፥14-15፤ 5፥1-11)
16በገሊላ ባሕርም አጠገብ ሲያልፍ ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፤ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና። 17ኢየሱስም “በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ፤” አላቸው። 18ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት። 19ከዚያም ጥቂት እልፍ ብሎ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ደግሞ በታንኳ ላይ መረባቸውን ሲያበጁ አየ። 20ወዲያውም ጠራቸው፤ አባታቸውንም ዘብዴዎስን ከሞያተኞቹ ጋር በታንኳ ላይ ትተው ተከትለውት ሄዱ።
ርኵስ መንፈስ ያደረበት ሰው እንደዳነ
(ሉቃ. 4፥31-37)
21ወደ ቅፍርናሆምም ገቡ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ። 22እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ። 23በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤ 24እርሱም “የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ! ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ! የእግዚአብሔር ቅዱሱ!” ብሎ ጮኸ። 25ኢየሱስም “ዝም በል፤ ከእርሱም ውጣ፤” ብሎ ገሠጸው። 26ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ። 27ሁሉም “ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው?” ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ። 28ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ።
ብዙ ሰዎች እንደተፈወሱ
(ማቴ. 8፥14-17፤ ሉቃ. 4፥38-41)
29ወዲያውም ከምኵራብ ወጥቶ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገባ። 30የስምዖንም አማት በንዳድ ታማ ተኝታ ነበር፤ ስለ እርስዋም ወዲያው ነገሩት። 31ቀርቦም እጅዋን ይዞ አስነሣት፤ ንዳዱም ወዲያው ለቀቃትና አገለገለቻቸው።
32ፀሐይም ገብቶ በመሸ ጊዜ፥ የታመሙትንና አጋንንት ያደረባቸውን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ 33ከተማይቱም ሁላ በደጅ ተሰብስባ ነበር። 34በልዩ ልዩ ደዌም የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፤ ብዙዎችንም አጋንንት አወጣ፤ አጋንንትም ክርስቶስ መሆኑን አውቀው ነበርና ሊናገሩ አልፈቀደላቸውም።
ኢየሱስ በገሊላ አውራጃዎች ዞሮ እንዳስተማረ
(ሉቃ. 4፥42-44)
35ማለዳም ተነሥቶ ገና ሌሊት ሳለ ወጣ፤ ወደ ምድረ በዳም ሄዶ በዚያ ጸለየ። 36ስምዖንና ከእርሱ ጋር የነበሩትም ገሥግሠው ተከተሉት፤ 37ባገኙትም ጊዜ “ሁሉ ይፈልጉሃል፤” አሉት። 38እርሱም “በዚያ ደግሞ ልሰብክ ወደ ሌላ ስፍራ በቅርብ ወዳሉ መንደሮች እንሂድ፤ ስለዚህ መጥቻለሁና፤” አላቸው። 39በምኵራባቸውም እየሰበከ አጋንንትንም እያወጣ ወደ ገሊላ ሁሉ መጣ።
ኢየሱስ ለምጻሙን ሰው እንዳነጻ
(ማቴ. 8፥1-4፤ ሉቃ. 5፥12-16)
40ለምጻምም ወደ እርሱ መጥቶ ተንበረከከና “ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ፤” ብሎ ለመነው። 41ኢየሱስም አዘነለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና “እወድዳለሁ፤ ንጻ፤” አለው። 42በተናገረም ጊዜ ለምጹ ወዲያው ለቀቀውና ነጻ። 43በብርቱም ተናግሮ ወዲያው አሰናበተው፤ 44“ለማንም አንዳች እንዳትናገር ተጠንቀቅ፤ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፤ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ ያዘዘውን አቅርብ፤” አለው። 45እርሱ ግን ሲወጣ ብዙ ሊሰብክና ነገሩን ሊያወራ ጀመረ፤ ስለዚህም ኢየሱስ ተገልጦ ወደ ከተማ መግባት ወደ ፊት ተሳነው፤ ነገር ግን በውጭ በምድረ በዳ ይኖር ነበር፤ ከየስፍራውም ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።
Currently Selected:
የማርቆስ ወንጌል 1: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ