ኦሪት ዘኍልቍ 16
16
ቆሬ፥ ዳታንና አቤሮን እንደ ዐመፁ
1የሌዊም ልጅ የቀዓት ልጅ የይስዓር ልጅ ቆሬ ከኤልያብ ልጆች ከዳታንና ከአቤሮን፥ ከሮቤልም ልጅ ከፋሌት ልጅ ከአውናን ጋር ተናገረ። 2በሙሴም ላይ ተነሡ፤ ከእስራኤልም ልጆች በምክር የተመረጡ፥ ዝናቸውም የተሰማ ሁለት መቶ አምሳ የማኅበሩ አለቆች ከእነርሱ ጋር ነበሩ። 3በሙሴና በአሮን ላይ ተነሡ፤ “ለእናንተ ይበቃችኋል፤ ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና፤ በእግዚአብሔርስ ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ?” አሉአቸው።
4ሙሴም በሰማ ጊዜ በግንባሩ ወደቀ። 5ለቆሬም ለማኅበሩም ሁሉ እንዲህ አላቸው፥ “ነገ እግዚአብሔር የእርሱ የሚሆኑትን፥ ቅዱሳንም የሆኑትን ያያል፥ ያውቃልም፤ የመረጣቸውንም ሰዎች ወደ እርሱ ያቀርባቸዋል። 6እንዲሁ አድርጉ፤ ቆሬና ማኅበሩ ሁሉ፥ ጥናዎቹን ውሰዱ፤ 7ነገም በእግዚአብሔር ፊት እሳት አድርጉባቸው፤ ዕጣንም ጨምሩባቸው፤ እግዚአብሔርም የሚመርጠው ይህ ሰው ለሌዊ ልጆች ቅዱስ ይሁንላቸው።” 8ሙሴም ቆሬን አለው፥ “እናንተ የሌዊ ልጆች፥ ስሙኝ፤ 9የእስራኤል አምላክ ከእስራኤል ማኅበር ለይቶ የመረጣችሁን፥ የእግዚአብሔርን ድንኳን አገልግሎት ትሠሩ ዘንድ፥ እንድታገለግሉአቸውም በማኅበሩ ፊት ትቆሙ ዘንድ ወደ እርሱ ያቀረባችሁን ታሳንሱታላችሁን? 10አንተን ከአንተም ጋር የሌዊን ልጆች ወንድሞችህን ሁሉ ወደ እርሱ አቅርቦአል፤ ካህናትም ትሆኑ ዘንድ ትፈልጋላችሁን? 11ስለዚህም አንተና ማኅበርህ ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ተሰብስባችኋል፤ በእርሱም ላይ ታጕረመርሙ ዘንድ አሮን ማንነው?”
12ሙሴም የኤልያብን ልጆች ዳታንንና አቤሮንን እንዲጠሩአቸው ላከ፤ እነርሱም፥ “አንመጣም፤ 13በምድረ በዳ ትገድለን ዘንድ፥ በእኛም ላይ አለቃችን ትሆን ዘንድ ወተትና ማር ከምታፈስሰው ምድር ያወጣኸን#ግእዙ “ወተትና ማር ወደምታፈስሰው ምድር ያገባኸን” ይላል። አነሰህን? 14አንተ አለቃ ነህን? ደግሞስ ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር አገባኸንን? እርሻንና የወይን ቦታንስ አወረስኸንን? የእነዚህንስ ሰዎች ዐይኖቻቸውን ታወጣለህን? አንመጣም” አሉ።
15ሙሴም እጅግ አዘነ፤ እግዚአብሔርንም አለው፥ “ወደ መሥዋዕታቸው አትመልከት፤ እኔ ከእነርሱ አንዳችም#ዕብ. “አንድ አህያ እንኳ” ይላል። ተመኝቼ አልወሰድሁም፤ ከእነርሱም አንድ ሰው አልበደልሁም።” 16ሙሴም ቆሬን አለው፥ “ማኅበርህን ለይ፤ ነገ አንተ፥ ማኅበርህም ሁሉ፥ አሮንም በእግዚአብሔር ፊት ዝግጁዎች ሁኑ። 17ሁላችሁም ጥናዎቻችሁን ውሰዱ፤ ዕጣንም አድርጉባቸው፤ እያንዳንዳችሁም ሁለት መቶ አምሳ ጥናዎቻችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት አምጡ፤ አንተ ደግሞ አሮንም ጥናዎቻችሁን አምጡ” አለው። 18እያንዳንዱም ጥናውን ወሰደ፤ እሳትም አደረገበት፤ ዕጣንም ጨመረበት፤ ሙሴና አሮንም በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ቆሙ። 19ቆሬም ማኅበሩን ሁሉ ወደ ምስክሩ ደጃፍ በእነርሱ ላይ ሰበሰበ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለማኅበሩ ሁሉ ተገለጠ።
20እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 21“ሁሉን በቅጽበት አጠፋቸው ዘንድ ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ።” 22እነርሱም በግንባራቸው ወድቀው፥ “የነፍስና የሥጋ ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንድ ሰው ኀጢአት ቢሠራ የእግዚአብሔር ቍጣ በማኅበሩ ላይ ይሆናልን?” አሉ። 23እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 24“ለማኅበሩ፦ ከቆሬ ማኅበር#ዕብ. “ከቆሬና ከዳታን ከአቤሮንም ማኅበር” ይላል። ዙሪያ ፈቀቅ በሉ ብለህ ንገራቸው።” 25ሙሴም ተነሥቶ ወደ ዳታንና ወደ አቤሮን ሄደ፤ የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ሄዱ። 26ማኅበሩንም፥ “ከእነዚህ ክፉዎች ሰዎች ድንኳን ፈቀቅ በሉ፤ በኀጢአታቸውም ሁሉ እንዳትጠፉ ለእነርሱ የሆነውን ሁሉ አትንኩ” ብሎ ተናገራቸው። 27ከቆሬ ድንኳን#ዕብ. “ከዳታንና ከአቤሮንም” የሚል ይጨምራል። ዙሪያም ሁሉ ፈቀቅ አሉ፤ ዳታንና አቤሮንም ከሴቶቻቸው፥ ከልጆቻቸውና ከጓዛቸው ጋር ወጥተው በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ቆሙ። 28ሙሴም አለ፥ “ይህን ሥራ ሁሉ አደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ላከኝ እንጂ ከልቤ እንዳይደለ በዚህ ታውቃላቸሁ። 29እነዚህ ሰዎች ሰው እንደሚሞት ቢሞቱ፥ ወይም መቅሠፍታቸው እንደ ሰው ሁሉ መቅሠፍት ቢሆን እግዚአብሔር አልላከኝም። 30እግዚአብሔር ግን አዲስ ነገር ቢፈጥር፥ ምድርም አፍዋን ከፍታ እነርሱን፥ ቤታቸውን፥ ድንኳናቸውን፥ ለእነርሱም ያለውን ሁሉ ብትውጣቸው፥ በሕይወታቸውም ወደ ሲኦል ቢወርዱ፥ ያንጊዜ እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን እንደ አስቈጡ ታውቃላቸሁ።”
31እንዲህም ሆነ፤ ይህን ቃል ሁሉ መናገር በፈጸመ ጊዜ ከበታቻቸው ያለችው መሬት ተሰነጠቀች፤ 32ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ እነርሱን፥ ቤተ ሰቦቻቸውንም፥ ለቆሬም የነበሩትን ሰዎች ሁሉ፥ ከብቶቻቸውንም ሁሉ ዋጠቻቸው። 33እነርሱም፥ ለእነርሱም የነበሩ ሁሉ በሕይወታቸው ወደ ሲኦል ወረዱ፤ ምድሪቱም ተዘጋችባቸው፤ ከማኅበሩም መካከል ጠፉ። 34በዙሪያቸው የነበሩ የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ከጩኸታቸው የተነሣ፥ “ምድሪቱ እንዳትውጠን” ብለው ሸሹ። 35እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥታ ያጥኑ የነበሩትን ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች በላች።#አንዳንድ ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 16 በቍ. 35 ያልቃል።
36እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 37ለካህኑ ለአሮን ልጅ ለአልዓዛር እንዲህ ብለህ ንገረው፥ “ከተቃጠሉት ሰዎች መካከል የናስ የሚሆኑ ጥናዎችን አውጣ፤ ከሌላ ያመጡትን ያንም እሳት ወዲያ ጣል፤ 38የእነዚህ ኃጥኣን ጥናዎቻቸው በሰውነታቸው ጥፋት ተቀድሰዋልና፤ የተጠፈጠፈ ሰሌዳ አድርጋቸው፤ ለመሠዊያ መለበጫም ይሁኑ፤ በእግዚአብሔር ፊት አቅርበዋቸዋልና የተቀደሱ ናቸው፤ ለእስራኤልም ልጆች ምልክት ይሆናሉ።” 39የካህኑም የአሮን ልጅ አልዓዛር የተቃጠሉት ሰዎች ያቀረቡአቸውን የናስ ጥናዎች ወስዶ ጠፍጥፎም ለመሠዊያ መለበጫ አደረጋቸው። 40እንደ ቆሬና ከእርሱም ጋር እንደ ተቃወሙት ሰዎች እንዳይሆን፥ ከአሮን ልጆች ያልሆነ ሌላ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ዕጣን ያጥን ዘንድ እንዳይቀርብ፥ እግዚአብሔር በሙሴ ቃል እንደ ተናገረው፥ ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ አደረጋቸው።
አሮን ሕዝቡን እንደ አዳናቸው
41በነጋውም የእስራኤል ልጆች ሁሉ፥ “እናንተ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ገድላችኋል” ብለው በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ። 42እንዲህም ሆነ፤ ማኅበሩ በሙሴና በአሮን ላይ በተሰበሰቡ ጊዜ በምስክሩ ድንኳን ከበቡአቸው፤ እነሆም፥ ደመናው ሸፈናት፤ የእግዚአብሔርም ክብር ተገለጠ። 43ሙሴና አሮንም ወደ ምስክሩ ድንኳን ፊት ገቡ። 44እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ 45“ከዚህ ማኅበር መካከል ፈቀቅ በሉ፥ እኔም በቅጽበት አጠፋቸዋለሁ።” በግንባራቸውም ወደቁ። 46ሙሴም አሮንን፥ “ጥናህን ውሰድ፤ ከመሠዊያውም ላይ እሳት አድርግበት፤ ዕጣንም ጨምርበት፤ ወደ ማኅበሩም ፈጥነህ ውሰደው፤ አስተስርይላቸውም፤ ከእግዚአብሔር ፊት ቍጣ ወጥቶአልና፥ ሕዝቡንም ያጠፋቸው ዘንድ ጀምሮአል” አለው። 47አሮንም ሙሴ እንደ ተናገረው ጥናውን ወስዶ ወደ ማኅበሩ መካከል ፈጥኖ ሮጠ፤ እነሆም፥ መቅሠፍቱ በሕዝቡ መካከል ጀምሮ ነበር፤ ዕጣንም ጨመረ፤ ለሕዝቡም አስተሰረየላቸው። 48በሙታንና በሕያዋን መካከል ቆመ፤ መቅሠፍቱም ተከለከለ። 49በቆሬም ምክንያት ከሞቱት ሌላ በመቅሠፍቱ የሞቱት ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 50አሮንም ወደ ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ተመለሰ፤ መቅሠፍቱም ፀጥ አለ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 16: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ