ኦሪት ዘኍልቍ 3
3
አራቱ የአሮን ወንዶች ልጆች
1እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ሙሴን በተናገረበት ቀን የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበረ። 2የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው፤ በኵሩ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር። 3በክህነት ያገለግሉ ዘንድ የተቀቡና እጆቻቸውን የተቀደሱ የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው። 4ናዳብና አብዩድ በሲና ምድረ በዳ በእግዚአብሔር ፊት ከሌላ እሳት ጭረው አምጥተዋልና በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፤ ልጆችም አልነበሩአቸውም። አልዓዛርና ኢታምር ከአባታቸው ከአሮን ጋር በክህነት ያገለግሉ ነበር።
የሌዋውያን ተግባር
5እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 6“የሌዊን ነገድ አቅርበህ ያገለግሉት ዘንድ በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው። 7የድንኳኑን ሥራ ይሠሩ ዘንድ ሕጉንና የእስራኤልን ልጆች ሕግ በምስክሩ ድንኳን ፊት ይጠብቁ። 8እንደ ድንኳኑ ሥራዎች ሁሉ የምስክሩን ድንኳን ዕቃና የእስራኤልን ልጆች ሕግ ይጠብቁ። 9ሌዋውያንንም ወደ ወንድምህ ወደ አሮንና ወደ ልጆቹ ወደ ካህናቱ ታገባቸዋለህ። ከእስራኤል ልጆች ተለይተው ለእኔ ሀብት ሆነው ተሰጥተዋልና። 10አሮንንና ልጆቹን በምስክሩ ድንኳን ፊት አቁማቸው፤ ክህነታቸውንም፥ በመሠዊያውና በመጋረጃው ውስጥ ያለውንም ሁሉ ይጠብቁ፤ ከሌላ ወገን የዳሰሰ ቢኖር ይገደል።”
11እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 12“እነሆ፥ እኔ በእስራኤል ልጆች ዘንድ መጀመሪያ በሚወለደው በበኵር ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይች ወስጃለሁ፤ በእነርሱ ፋንታ ሌዋውያን ለእኔ ይሁኑ፤ 13በኵር ሁሉ ለእኔ ነውና፤ በግብፅ ምድር በኵርን ሁሉ በመታሁ ቀን ከእስራኤል ዘንድ በኵርን ሁሉ፥ ሰውንና እንስሳን፥ ለእኔ ለይችአለሁ፤ ለእኔ ይሁኑ። እኔ እግዚአብሔር ነኝና።”
የሌዋውያን ቈጠራ
14እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 15“የሌዊን ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ በየወገናቸውም ቍጠር፤ ወንዱን ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን ቍጠራቸው።” 16ሙሴና አሮንም እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ እግዚአብሔር እንደ አዘዛቸው ቈጠሩአቸው። 17የሌዊ ልጆች በየስማቸው እነዚህ ናቸው፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ። 18የጌድሶንም ልጆች ስሞች በየወገናቸው እነዚህ ናቸው፤ ሎቤን፥ ሰሜይ። 19የቀዓትም ልጆች በየወገናቸው እንበረም፥ ይሳዓር፥ ኬብሮን፥ አዛሄል። 20የሜራሪም ልጆች በየወገናቸው፤ ሞሐሊ፥ ሙሲ። የሌዋውያን ወገኖች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ናቸው።
21ለጌድሶን የሎቤን ወገን፥ የሰሜይም ወገን ነበሩት፤ የጌድሶን ወገኖች እነዚህ ናቸው። 22ከእነርሱ የተቈጠሩት የወንዶች ሁሉ ቍጥር ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ሰባት ሺህ አምስት መቶ#ግዕዙ “ሰባት ሺህ አራት መቶ” ይላል። ነበሩ። 23የጌድሶን ልጆች ከድንኳን በኋላ በባሕር በኩል ይሰፍራሉ። 24የጌድሶን አባቶች ቤት አለቃ የዳሔል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል። 25የጌድሶን ልጆች በምስክሩ ድንኳን የሚጠብቁት ማደሪያውና ድንኳኑ፥ መደረቢያውም፥ የምስክሩ ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥ 26የአደባባዩ መጋረጃ፥ በድንኳኑ አደባባይ በር ያለው መጋረጃና የቀረውም ሥራዋ ሁሉ ይሆናል።
27ለቀዓትም የእንበረም ወገን፥ የይስዓር ወገን፥ የኬብሮንም ወገን፥ የአዛሔልም ወገን ነበሩ፤ የቀዓት ወገኖች እነዚህ ናቸው። 28ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ፤ መቅደሱንም ይጠብቁ ነበር። 29የቀዓት ልጆች ወገኖች በድንኳኑ አጠገብ በአዜብ በኩል ይሰፍራሉ። 30የቀዓት ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የአዛሔል ልጅ ኤሊሳፋ ይሆናል። 31ታቦቱንም፥ ገበታውንም፥ መቅረዙንም፥ መሠዊያዎቹንም፥ የሚያገለግሉበትንም የመቅደሱን ዕቃ፥ መጋረጃውንም፥ ማገልገያውንም ሁሉ ይጠብቃሉ። 32የሌዋውያንም አለቆች አለቃ የተቀደሱ ነገሮችን ይጠብቅ ዘንድ የተሾመው የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ነው።#ዕብ. “የሌዋውያንም የአለቆች አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር” ይላል።
33ለሜራሪ የሞሖሊ ወገን የሙሲ ወገን ነበሩ፤ የሜራሪ ወገኖች እነዚህ ናቸው። 34ከእነርሱም ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ስድስት ሽህ አምሳ#ዕብ. “ስድስት ሽህ ሁለት መቶ” ይላል። ነበሩ። 35የሜራሪም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የአቢኪያ ልጅ ሱራሔል ነበረ፤ በድንኳኑ አጠገብ በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ። 36የሜራሪም ልጆች የሚጠብቁት የድንኳኑ ምሰሶዎች፥ ኩላቦች፥ መወርወሪያዎችም፥ ተራዳዎችም፥ እግሮቹም፥ 37ዕቃውም ሁሉ፥ ማገልገያውም ሁሉ፥ በዙሪያውም የሚቆሙ የአደባባይ ምሰሶዎች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም ይሆናሉ።
38በምሥራቅ በኩል በምስክሩ ድንኳን ፊት የሚሰፍሩት ሙሴና አሮን ልጆቹም ይሆናሉ፥ እንደ እስራኤል ልጆች ሕግም የመቅደሱን ሕግ ይጠብቃሉ፥ ከሌላ ወገን የዳሰሰ ቢኖር ይገደል።
39በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ ከሌዋውያን ወንዶች ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ በየወገናቸው የተቈጠሩት ሁሉ ሃያ ሁለት ሺህ ነበሩ።
የሌዋውያን በእስራኤል የበኵር ልጆች መተካት
40እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “የእስራኤልን ልጆች ወንዱን በኵር ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን ቍጠር፤ ቍጥራቸውንም በየስማቸው ውሰድ፤ 41ሌዋውያንንም በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእስራኤል ልጆች እንስሶች በኵር ሁሉ ፋንታ ለእኔ ለእግዚአብሔር አድርጋቸው” አለው። 42ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኵር ሁሉ ቈጠረ። 43ከእነርሱም የተቈጠሩ ወንዶች በኵሮች ሁሉ በየስማቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ሃያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበሩ።
44እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 45“ሌዋውያንን በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእንስሶቻቸው ፋንታ ውሰድ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና። 46በሌዋውያን ላይ ከእስራኤል ልጆች በኵር ስለ ተረፉት ስለ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ቤዛ፥ 47በየራሱ አምስት ዲድርክም ውሰድ፤ እንደ መቅደሱ ዲድርክም ብዛት ትወስዳለህ፤ ዲድርክም#ዕብ. “ሰቅል” ይላል። ሃያ አቦሊ ነው። 48ስለ ተረፉትም የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣቸዋለህ።” 49ሙሴም በሌዋውያን ከተቤዡት በላይ ከተረፉት ዘንድ የመቤዣውን ገንዘብ ወሰደ። 50ከእስራኤል ልጆች በኵሮች ገንዘቡን ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዲድርክም እንደ መቅደሱ ዲድርክም ሚዛን ወሰደ። 51እንደ እግዚአብሔርም ቃል፥ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 3: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ