ኦሪት ዘኍልቍ 33
33
ከግብፅ እስከ ሞዐብ የተደረገ ጕዞ
1በሙሴና በአሮን እጅ ከሠራዊቶቻቸው ጋር ከግብፅ ከወጡ በኋላ የእስራኤል ልጆች የሰፈሩበት ይህ ነው። 2ሙሴም በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ተጓዙ የሰፈሩበትን ጻፈ፥ እየተጓዙ ያደሩበት ይህ ነው። 3በመጀመሪያው ወር ከመጀመሪያውም ወር በዐሥራ አምስተኛው ቀን ከራምሴ ተጓዙ፤ ከፋሲካ በኋላ በነጋው የእስራኤል ልጆች ከግብፃውያን ሁሉ ፊት ከፍ ባለች እጅ ወጡ። 4በዚያም ጊዜ ግብፃውያን እግዚአብሔር የገደላቸውን በኵሮቻቸውን ይቀብሩ ነበር፤ በአማልክቶቻቸውም ደግሞ እግዚአብሔር ፈረደባቸው።
5የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተጕዘው በሱኮት ሰፈሩ። 6ከሱኮትም ተጕዘው በምድረ በዳ ዳርቻ ባለች በኤታም ሰፈሩ። 7ከኤታምም ተጕዘው በኤልሴፎን ፊት ወደ ነበረች በኤሮት በር፤ በመግደሎ ፊት ለፊት ሰፈሩ። 8ከኤሮትም ፊት ለፊት ተጕዘው በባሕሩ መካከል ወደ ምድረ በዳ ተሻገሩ፤ በኤታምም በረሃ የሦስት ቀን መንገድ ሄደው በምረት ሰፈሩ። 9ከምረትም ተጕዘው ወደ ኤሊም መጡ፤ በኤሊምም ዐሥራ ሁለት የውኃ ምንጮች፥ ሰባ ዘንባቦችም ነበሩ፤ በዚያም በውኃ አጠገብ ሰፈሩ። 10ከኤሊምም ተጕዘው በኤርትራ ባሕር ዳር ሰፈሩ። 11ከኤርትራም ባሕር ተጕዘው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ። 12ከሲና ምድረ በዳም ተጕዘው በራፋቃ ሰፈሩ። 13ከራፋቃም ተጕዘው በኤሉስ ሰፈሩ። 14ከኤሉስም ተጕዘው በራፊድን ሰፈሩ፤ በዚያም ሕዝቡ የሚጠጡት ውኃ አልነበረም። 15ከራፊድንም ተጕዘው በሲና ምድረ በዳ ሰፈሩ። 16ከሲና ምድረ በዳም ተጕዘው በምኞት መቃብር ሰፈሩ። 17ከምኞት መቃብርም ተጕዘው በአቤሮት ሰፈሩ። 18ከአቤሮትም ተጕዘው በራታማ ሰፈሩ። 19ከራታማም ተጕዘው በሬሞት ዘፋሬስ ሰፈሩ። 20ከሬሞት ዘፋሬስም ተጕዘው በልብና ሰፈሩ። 21ከልብናም ተጕዘው በሪሳ ሰፈሩ። 22ከሪሳም ተጕዘው በመቄላት ሰፈሩ። 23ከመቄላትም ተጕዘው በሳፋር ሰፈሩ። 24ከሳፋርም ተጕዘው በካሬደት ሰፈሩ። 25ከካሬደትም ተጕዘው በመቄሎት ሰፈሩ። 26ከመቄሎትም ተጕዘው በቀጠአት ሰፈሩ። 27ከቀጠአትም ተጕዘው በተሪት ሰፈሩ። 28ከተሪትም ተጕዘው በሚትቃ ሰፈሩ። 29ከሚትቃም ተጕዘው በኤሴምና ሰፈሩ። 30ከኤሴምናም ተጕዘው በመሱሩት ሰፈሩ። 31ከመሱሩትም ተጕዘው በብንያቅን ሰፈሩ። 32ከብንያቅንም ተጕዘው በገድገድ ተራራ ሰፈሩ። 33ከገድገድም ተጕዘው በአጤቤት ሰፈሩ። 34ከአጤቤትም ተጕዘው በኤብሮና ሰፈሩ። 35ከኤብሮናም ተጕዘው በጋስዮንጋቤር ሰፈሩ። 36ከጋስዮንጋቤርም ተጕዘው በጺን ምድረ በዳ ሰፈሩ። ከጺን ምድረ በዳም ተጕዘው በፋራን ምድረ በዳ ሰፈሩ። ይህችም ቃዴስ ናት። 37ከቃዴስም ተጕዘው በኤዶምያስ ምድር ዳርቻ ባለው በሖር ተራራ ሰፈሩ።
38ካህኑም አሮን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ ሖር ተራራ ላይ ወጣ፤ በዚያም የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በአርባኛው ዓመት፥ በአምስተኛው ወር፥ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ሞተ። 39አሮንም በሖር ተራራ ላይ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሃያ ሦስት ዓመት ነበረ።
40በከነዓን ምድርም ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ የእስራኤል ልጆች እንደ መጡ ሰማ። 41እነርሱም ከሖር ተራራ ተጕዘው በሴልሞና ሰፈሩ። 42ከሴልሞናም ተጕዘው በፌኖ ሰፈሩ። 43ከፌኖም ተጕዘው በአቦት ሰፈሩ። 44ከአቦትም ተጕዘው በሞዓብ ዳርቻ ባለው በጋይ ሰፈሩ። 45ከጋይም ተጕዘው በዲቦንጋድ ሰፈሩ። 46ከዲቦንጋድም ተጕዘው በጌልሞንዲብላታይም ሰፈሩ። 47ከጌልሞንዲብላታይምም ተጕዘው በናባው ፊት ባሉት በአባሪም ተራሮች ላይ ሰፈሩ። 48በናባው ፊት ካሉት ከአባሪም ተራሮችም ተጕዘው በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ በኩል ባለው በሞዓብ ምዕራብ ሰፈሩ። 49በዮርዳኖስም አጠገብ በሞዓብ ምዕራብ ከአሲሞት መካከል እስከ አቤልሰጢም ድረስ ሰፈሩ።
እስራኤላውያን ዮርዳኖስን ከመሻገራቸው በፊት የተሰጣቸው መመሪያ
50እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ በኩል በሞዓብ ምዕራብ እንዲህ ብሎ ተናገረው። 51“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁ፤ 52በዚያችም ምድር የሚኖሩትን ሁሉ ከፊታችሁ አጥፉአቸው፤ የተቀረጹትንም ድንጋዮቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፤ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎቻቸውን ሁሉ ታጠፋላችሁ፤ በኮረብታ ላይ ያሉትን መስገጃዎቻቸውንም ታፈርሳላችሁ፤ 53በዚያች ምድር የሚኖሩትንም አጥፍታችሁ በውስጥዋ ኑሩ። ምድሪቱን ለእናንተ ርስት አድርጌ ሰጥቼአችኋለሁና። 54ምድሪቱንም ትወርሳላችሁ፤ በየወገኖቻችሁም ትከፋፈሏታላችሁ፤ ለብዙዎች ድርሻቸውን አብዙላቸው፤ ለጥቂቶችም ድርሻቸውን ጥቂት አድርጉ፤ እያንዳንዱ ሁሉ ዕጣ እንደ ወደቀለት በዚያ ርስቱ ይሆናል፤ በየአባቶቻችሁ ነገዶች ትወርሳላችሁ። 55የሀገሩንም ስዎች ከፊታችሁ ባታሳድዱ፥ ያስቀራችኋቸው ለዐይናችሁ እንደ እሾህ፥ ለጐናችሁም እንደ አሜከላ ይሆኑባችኋል፤ በምትቀመጡባትም ምድር ያስጨንቁአችኋል። 56እኔም በእነርሱ አደርገው ዘንድ ያሰብሁትን በእናንተ አደርግባችኋለሁ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 33: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ