ኦሪት ዘኍልቍ 7
7
የእስራኤል አለቆች መባእ
1እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ድንኳኑን ፈጽሞ በተከለባት፥ እርስዋንና ዕቃዋን ሁሉ በቀባና በቀደሰባት፥ መሠዊያውንና ዕቃውንም ሁሉ በቀባና በቀደሰባት ቀን፥ 2ዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል አለቆች፥ የአባቶቻቸው ቤቶች አለቆች፥ ቍርባናቸውን አቀረቡ፤ እነዚህም ከተቈጠሩት በላይ የተሾሙ የነገዶች አለቆች ነበሩ። 3መባቸውንም በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፤ የተከደኑ ስድስት ሰረገሎች ዐሥራ ሁለትም በሬዎች፤ በየሁለቱም አለቆች አንድ ሰረገላ አቀረቡ፤ ሁሉም እያንዳንዱ አንድ በሬ በድንኳኑ ፊት አቀረቡ። 4እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 5“ለምስክሩ ድንኳን ሥራ የሚያገለግል ይሆን ዘንድ፥ ከእነርሱ ተቀብለህ ለሌዋውያን ለእያንዳንዱ እንደ አገልግሎታቸው ስጣቸው።” 6ሙሴም ሰረገሎችንና በሬዎችን ተቀብሎ ለሌዋውያን ሰጣቸው። 7ለጌድሶን ልጆች እንደ አገልግሎታቸው ሁለት ሰረገሎችንና አራት በሬዎችን ሰጣቸው። 8ከካህኑም ከአሮን ልጅ ከኢታምር እጅ በታች ላሉት ለሜራሪ ልጆች እንደ አገልግሎታቸው መጠን አራት ሰረገሎችንና ስምንት በሬዎችን ሰጣቸው። 9ለቀዓት ልጆች ግን መቅደሱን ማገልገል የእነርሱ ነውና፥ በትከሻቸውም ይሸከሙት ነበርና ምንም አልሰጣቸውም። 10መሠዊያውም በተቀባ ቀን አለቆቹ መሠዊያውን ለመቀደስ ቍርባንን አቀረቡ፤ አለቆችም መባቸውን በመሠዊያው ፊት አቀረቡ። 11እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “እያንዳንዱ አለቃ በየቀኑ መሠዊያውን ለመቀደስ እያንዳንዱ አለቃ መባውን በቀን በቀኑ ያቅርብ” አለው። 12በመጀመሪያውም ቀን መባውን ያቀረበ ከይሁዳ ነገድ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነበረ። 13መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 14ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 15ለሚቃጠልም መሥዋዕት ከመንጋዎች አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦት፤ 16ለኀጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 17ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት ጊደሮች፥#ዕብ. “በሬዎች” ይላል። አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት እንስት#ዕብ. “ተባት” ይላል። የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የአሚናዳብ ልጅ የነአሶን መባ ይህ ነበረ። 18በሁለተኛውም ቀን የይሳኮር አለቃ የሰገር ልጅ ናትናኤል አቀረበ። 19ለመባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉትን፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነውን አንድ የብር ድስት፤ 20ዕጣንም የተሞላውን ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነውን አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 21ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦት፤ 22ለኀጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 23ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት ጊደሮች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት እንስት የበግ ጠቦቶች አቀረበ፤ የሰገር ልጅ የናትናኤል መባ ይህ ነበረ።
24በሦስተኛውም ቀን የዛብሎን ልጆች አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ መባውን አቀረበ። 25መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 26ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 27ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦት፤ 28ለኀጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 29ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት ጊደሮች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት እንስት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኬሎን ልጅ የኤልያብ መባ ይህ ነበረ።
30በአራተኛውም ቀን የሮቤል ልጆች አለቃ የሴድዮር ልጅ ኤሊሱር መባውን አቀረበ፤ 31መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ስቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 32ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 33ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦት፤ 34ለኀጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 35ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት ጊደሮች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት እንስት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የሴድዮር ልጅ የኤሊሱር መባ ይህ ነበረ።
36በአምስተኛውም ቀን የስምዖን ልጆች አለቃ የሲሩሳዴ ልጅ ሰላምያል መባውን አቀረበ፤ 37መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 38ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 39ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦት፤ 40ለኀጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 41ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት ጊደሮች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት እንስት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የሲሩሳዴ ልጅ የሰላምያል መባ ይህ ነበረ።
42በስድስተኛውም ቀን የጋድ ልጆች አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ መባውን አቀረበ፤ 43መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 44ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 45ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት፤ 46ለኀጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 47ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት ጊደሮች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት እንስት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የራጉኤል ልጅ የኤሊሳፍ መባ ይህ ነበረ።
48በሰባተኛውም ቀን የኤፍሬም ልጆች አለቃ የኤሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ መባውን አቀረበ፤ 49መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑ ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 50ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 51ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦት፤ 52ለኀጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 53ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት ጊደሮች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት እንስት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኤሚሁድ ልጅ የኤሊሳማ መባ ይህ ነበረ።
54በስምንተኛውም ቀን የምናሴ ልጆች አለቃ የፈዳሱር ልጅ ገማልያል መባውን አቀረበ፤ 55መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑ ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 56ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 57ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦት፤ 58ለኀጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 59ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት ጊደሮች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት እንስት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የፈዳሱር ልጅ የገማልያል መባ ይህ ነበረ።
60በዘጠነኛውም ቀን የብንያም ልጆች አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን መባውን አቀረበ፤ 61መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 62ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 63ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦት፤ 64ለኀጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 65ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት ጊደሮች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት እንስት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የጋዴዮን ልጅ የአቢዳን መባ ይህ ነበረ።
66በዐሥረኛውም ቀን የዳን ልጆች አለቃ የአሚሳዲ ልጅ አኪያዜር መባውን አቀረበ፤ 67መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 68ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 69ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦት፤ 70ለኀጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 71ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት ጊደሮች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት እንስት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የአሚሳዲ ልጅ የአኪያዜር መባ ይህ ነበረ።
72በዐሥራ አንደኛውም ቀን የአሴር ልጆች አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል መባውን አቀረበ፤ 73መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 74ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 75ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦት፤ 76ለኀጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 77ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት ጊደሮች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት እንስት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የኤክራን ልጅ የፋግኤል መባ ይህ ነበረ።
78በዐሥራ ሁለተኛውም ቀን የንፍታሌም ልጆች አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ መባውን አቀረበ፤ 79መባውም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት የተሞሉ፥ ሚዛኑ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን መቶ ሠላሳ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ወጭት፥ ሚዛኑም ሰባ ሰቅል የሆነ አንድ የብር ድስት፤ 80ዕጣንም የተሞላ ሚዛኑ ዐሥር ሰቅል የሆነ አንድ የወርቅ ጭልፋ፤ 81ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦት፤ 82ለኀጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፤ 83ለደኅንነትም መሥዋዕት ሁለት ጊደሮች፥ አምስት አውራ በጎች፥ አምስት አውራ ፍየሎች፥ አምስት የአንድ ዓመት እንስት የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ የዔናን ልጅ የአኪሬ መባ ይህ ነበረ።
84መሠዊያው በተቀባ ቀን የእስራኤል ልጆች አለቆች ለመሠዊያው መቀደሻ ያቀረቡት መባ ይህ ነበረ፤ ዐሥራ ሁለት የብር ወጭቶች፥ ዐሥራ ሁለት የብር ድስቶች፥ ዐሥራ ሁለት የወርቅ ጭልፋዎች፤ 85እያንዳንዱም የብር ወጭት መቶ ሠላሳ ሰቅል፥ እያንዳንዱም ድስት ሰባ ሰቅል ነበረ፤ የዚህም ዕቃ ሁሉ ብር በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ። 86ዕጣንም የተሞሉ ዐሥራ ሁለት የወርቅ ጭልፋዎች፥ እያንዳንዱ በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ዐሥር ዐሥር ሰቅል ነበረ፤ የጭልፋዎቹ ወርቅ ሁሉ መቶ ሃያ ሰቅል ነበረ። 87የሚቃጠለው መሥዋዕት ከብት ሁሉ ከእህሉ ቍርባን ጋር ዐሥራ ሁለት ወይፈኖች፥ ዐሥራ ሁለትም አውራ በጎች፥ ዐሥራ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ነበሩ፤ የኀጢአትም መሥዋዕት አውራ ፍየሎች ዐሥራ ሁለት ነበሩ። 88የደኅንነትም መሥዋዕት ከብት ሁሉ፥ ሃያ አራት ጊደሮች፥#ዕብ. “በሬዎች” ይላል። ስድሳም አውራ በጎች፥ ስድሳም አውራ ፍየሎች፥ ስድሳም ነውር የሌለባቸው#“ነውር የሌለባቸው” የሚለው በዕብ. የለም። የአንድ ዓመት እንስት#ዕብ. “ተባት” ይላል። የበግ ጠቦቶች ነበሩ። መሠዊያው ከተቀባ በኋላ ለመቀደሻው የቀረበ ቍርባን ይህ ነበረ።
89ሙሴም ወደ ምስክሩ ድንኳን እርሱን ለመነጋገር በገባ ጊዜ በቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ ካለው ከስርየት መክደኛው በላይ ከኪሩቤልም መካከል የእግዚአብሔርን ድምፅ ይሰማ ነበር፤ ከእርሱም ጋር ይናገር ነበር።
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 7: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ