መዝሙረ ዳዊት 118
118
አሌፍ።
1በመንገዳቸው ንጹሓን የሆኑ፥
በእግዚአብሔርም ሕግ የሚሄዱ ብፁዓን ናቸው።
2ምስክሩን የሚፈልጉ፥
በፍጹም ልብ የሚሹት ብፁዓን ናቸው፤
3ዐመፃን የሚያደርጉ ግን በመንገዱ አይሄዱም።
4ትእዛዛትህን እጅግ ይጠብቁ ዘንድ አንተ አዘዝህ።
5ሥርዐትህን እጠብቅ ዘንድ
የሚቀናስ ከሆነ መንገዴ ይቅና።
6ትእዛዝህን ሁሉ ስመለከት
በዚያን ጊዜ አላፍርም።
7አቤቱ፥ የጽድቅህን ፍርድ ስማር
በቅን ልብ አመሰግንሃለሁ።
8ሥርዐትህንም እጠብቃለሁ፤
ለዘለዓለም አትጣለኝ።
ቤት።
9ጐልማሳ መንገዱን በምን ያቀናል?
ቃልህን በመጠበቅ ነው።
10በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ፥
ከትእዛዝህ አታርቀኝ።
11አንተን እንዳልበድል፥
ቃልህን በልቤ ሰወርሁ።
12አቤቱ፥ አንተ ቡሩክ ነህ፤
ሥርዐትህንም አስተምረኝ።
13የአፍህን ፍርድ ሁሉ በከንፈሬ ነገርሁ።
14እንደ ብልጥግና ሁሉ
በምስክርህ መንገድ ደስ አለኝ።
15ትእዛዝህን አሰላሰልሁ፥
መንገድህንም እፈልጋለሁ።
16ትእዛዞችህን አነብባለሁ፤
ቃልህንም አልረሳም።
ጋሜል።
17ሕያው እንድሆን ቃልህንም እንድጠብቅ
ለባሪያህ ስጠው።
18ዓይኖችን ክፈት፥
ከሕግህም ድንቅ ነገርን አያለሁ።
19እኔ በምድር ስደተኛ ነኝ፤
ትእዛዛትህን ከእኔ አትሰውር።
20ነፍሴ ሁልጊዜ ፍርድህን እጅግ ናፈቀች።
ትዕቢተኞችን ገሠጽኻቸው፥
21ከትእዛዛትህ የሚርቁ ርጉማን ናቸው።
22ትእዛዝህን#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ምስክርህን” ይላል። ፈልጌአለሁና
ስድብንና ነውርን ከእኔ አርቅ።
23አለቆች ደግሞ ተቀምጠው እኔን አሙኝ፤
ባሪያህ ግን ፍርድህን ያሰላስል ነበር።
24ምስክርህም ትምህርቴ ነው፥
ሥርዐትህም መካሬ ነው።
ዳሌጥ።
25ሰውነቴ ወደ ምድር ተጣበቀች፤
እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ።
26መንገድህንና ምስክርህን ነገርሁ፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሰማኸኝም” የሚል ይጨምራል።
ፍርድህን አስተምረኝ።
27የእውነትህን መንገድ እንዳስተውል አድርገኝ፥
ተአምራትህንም አሰላስላለሁ።
28ከኀዘን የተነሣ ሰውነቴ አንቀላፋች፤
በቃልህ አጠንክረኝ።
29የዐመፃን መንገድ ከእኔ አርቅ፥
በሕግህም ይቅር በለኝ፤
30የእውነትህን መንገድ መረጥሁ፥
ፍርድህንም አልረሳሁም።
31አቤቱ፥ ምስክርህን ተከተልሁ፥ አታሳፍረኝ።
32ልቤን ባሰፋኸው ጊዜ፥
በትእዛዝህ መንገድ ሮጥሁ።
ሄ።
33አቤቱ፥ የእውነትህን መንገድ አስተምረኝ፥
ሁልጊዜም እፈልጋታለሁ።
34እንዳስተውል አድርገኝ፥ ሕግህንም እፈልጋለሁ፤
በፍጹም ልቤም እጠብቀዋለሁ።
35እርስዋን ወድጃለሁና
የትእዛዝህን መንገድ ምራኝ።
36ልቤን ወደ ምስክርህ መልስ፥
ወደ ቅሚያም አይሁን።
37ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዐይኖቼን መልስ፤
በመንገድህም ሕያው አድርገኝ።
38እንዲፈራህ#“እንዲፈራህ” የሚለው በግእዝ የለም። ለባሪያህ በቃልህ የተናገርኸውን አጽና።
39ፍርድህ መልካም ነውና
የተጠራጠርሁትን ስድብ ከእኔ አርቅ።
40እነሆ፥ ትእዛዝህን ናፈቅሁ፥
በጽድቅህም ሕያው አድርገኝ።
ዋው።
41አቤቱ፥ ምሕረትህ ይምጣልኝ፥
አቤቱ፥ ማዳንህ እንደ ቃልህ ነው።
42በቃልህ ታምኛለሁና
ለሚሰድቡኝ በነገር እመልስላቸዋለሁ።
43በፍርድህም ታምኛለሁና
የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ።
44ለዘለዓለም ዓለም
ሁልጊዜ ሕግህን እጠብቃለሁ።
45ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና
አስፍቼ እሄዳለሁ።
46በነገሥታት ፊት ምስክርህን እናገራለሁ፥ አላፍርምም፤
47እጅግም የወደድኋቸውን ትእዛዛትህን እናገራለሁ።
48እጆቼንም ወደ ወደድኋቸው ወደ ትእዛዛትህ አነሣለሁ፤
ፍርድህንም አሰላስላለሁ።
ዛይ።
49ለባሪያህ ተስፋ ያስደረግኸውን ቃልህን አስብ።
50ቃልህ ሕያው አድርጎኛልና።
ይህች በመከራዬ ደስ አሰኘችኝ።
51ትዕቢተኞች እጅግ ዐመፁ፤
እኔ ግን ከሕግህ አልራቅሁም።
52ከጥንት የነበረውን ፍርድህን ዐሰብሁ፥
አቤቱ፥ደስ አለኝ።
53ሕግህን ከተዉ ኃጥኣን የተነሣ ኀዘን ያዘኝ።
54በእንግድነቴ ሀገር ፍርድህ መዝሙር ሆነኝ።
55አቤቱ፥ በሌሊት ስምህን ዐሰብሁ፥
ሕግህንም ጠበቅሁ።
56ትእዛዛትህንም ፈልጌአለሁና ይህች ሆነችልኝ።
ሔት።
57እግዚአብሔር ክፍሌ ነው፤
ሕግህን ይጠብቁ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እጠብቃለሁ” ይላል። አልሁ።
58አቤቱ በፍጹም ልቤ ወደ ፊትህ ለመንሁ፤
እንደ ቃልህ ይቅር በለኝ።
59ስለ መንገዶችህ ዐሰብሁ፥
እግሬንም ወደ ምስክርህ መለስሁ።
60ትእዛዝህን ለመጠበቅ ጨከንሁ፥ አልተጠራጠርሁምም።
61የኃጥኣን ገመዶች ተተበተቡብኝ፤
ሕግህን ግን አልረሳሁም።
62ስለ ጽድቅህ ፍርድ፥ አመሰግንህ ዘንድ
በእኩለ ሌሊት እነሣለሁ።
63እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፥
ትእዛዝህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ።
64አቤቱ፥ ይቅርታህ በምድር ሁሉ ሞላች፤
ሥርዐትህንም አስተምረኝ።
ጤት።
65አቤቱ፥ እንደ ቃልህ
ለባሪያህ መልካም አደረግህ።
66በትእዛዛትህ ታምኛለሁና
መልካም ምክርንና ጥበብን አስተምረኝ።
67እኔ ሳልጨነቅ ተጸጸትሁ፤#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “በደልሁ” ይላል።
ስለዚህም ቃልህን ጠበቅሁ።
68አቤቱ፥ አንተ ቸር ነህ፥
በቸርነትህም ፍርድህን አስተምረኝ።
69የትዕቢተኞች ዐመፃ በላዬ በዛ፤
እኔ ግን በፍጹም ልቤ ትእዛዛትህን እፈልጋለሁ።
70ልባቸው እንደ ወተት ረጋ፤
እኔ ግን ሕግህን አነብባለሁ
71ፍርድህን አውቅ ዘንድ
ያስጨነቅኸኝ መልካም ሆነልኝ።
72ከአእላፋት ወርቅና ብር ይልቅ።
የአፍህ ሕግ ይሻለኛል።
ዮድ።
73እጆችህ ሠሩኝ፥ አበጃጁኝም፤
እንዳስተውል አድርገኝ፥ ትእዛዛትህንም እማራለሁ።
74በቃልህ ታምኛለሁና
የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይላቸዋል።
75አቤቱ፥ ፍርድህ ጽድቅ እንደ ሆነች፥
በሚገባም እንዳስጨነቅኸኝ ዐወቅሁ።
76ምሕረትህ ለደስታዬ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ለመጽናናቴ” ይላል። ይሁነኝ፥
እንደ ቃልህም ለባሪያህ ይሁነው።
77ሕግህ ትምህርቴ ነውና
ቸርነትህ ይምጣልኝ፥ በሕይወትም ልኑር።
78ትዕቢተኞች ዐመፃን መክረውብኛልና ይፈሩ፤
እኔ ግን ትእዛዝህን አሰላስላለሁ።
79የሚፈሩህና ምስክሮችህን የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ።
80እንዳላፍር ልቤ በፍርድህ ንጹሕ ይሁን።
ካፍ።
81ነፍሴ ወደ ማዳንህ አለፈች፤
በቃልህም ታመንሁ።
82መቼ ታጽናናኛለህ እያልሁ
ዐይኖቼ ትድግናህን በመጠበቅ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ስለ ቃልህ” ይላል። ፈዘዙ።
83በውርጭ እንዳለ ረዋት ሆኛለሁና፤
ፍርድህን ግን አልረሳሁም።
84የባሪያህ ዘመኖች ምን ያህል ናቸው?
በሚያሳድዱኝስ ላይ መቼ ትፈርድልኛለህ?
85ኃጥኣን ዋዛ-ፈዛዛን ነገሩኝ፥
አቤቱ፥ እንደ ሕግህ ግን አይደለም።
86ትእዛዝትህ ሁሉ እውነት ናቸው፤
በዐመፃ አሳድደውኛል፤ ርዳኝ።
87ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቶአቸው ነበር፤
እኔ ግን ትእዛዛትህን አልተውሁም።
88እንደ ምሕረትህ ሕያው አድርገኝ፤
የአፍህንም ምስክር እጠብቃለሁ።
ላሜድ።
89አቤቱ፥ ቃልህ በሰማይ ለዘለዓለም ይኖራል።
90እውነትህ ለልጅ ልጅ ናት፤
ምድርን መሠረትሃት፥ እርስዋም ትኖራለች።
91ሁሉን ገዝተሃልና
ቀኑ በትእዛዝህ ይኖራል።
92ሕግህ ትምህርቴ ባይሆን፥
ቀድሞ በጕስቍልናዬ በጠፋሁ ነበር።
93በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና
ፍርድህን ለዘለዓለም አልረሳም።
94እኔ የአንተ ነኝ፥ ፍርድህን ፈልጌአለሁና አድነኝ።
95ኃጥኣን ያጠፉኝ ዘንድ ጠበቁኝ፤
ምስክርህን አስተውያለሁና።
96የሥራውን ሁሉ ፍጻሜ አየሁ፤
ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው።
ሜም።
97አቤቱ፥ ሕግህን እንደምን እጅግ ወደድሁ!
ቀኑን ሁሉ እርሱ ትምህርቴ ነው።
98ለዘለዓለም ለእኔ ነውና
ትእዛዝህ ከጠላቶቼ ይልቅ አስተዋይ አደረገኝ።
99ትእዛዝህ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ምስክርህ” ይላል። ትምህርቴ ነውና
ካስተማሩኝ ሁሉ ይልቅ አስተዋልሁ።
100ትእዛዝህን ፈልጌአለሁና
ከሽማግሌዎች ይልቅ አስተዋልሁ።
101ቃልህን እጠብቅ ዘንድ
ከክፉ መንገድ ሁሉ እግሬን ከለከልሁ።
102አንተ አስተምረኸኛልና ከፍርድህ አልራቅሁም።
103ቃልህ ለጕሮሮዬ ጣፋጭ ነው፤
ከማርና ከወለላ ይልቅ ለአፌ ጣፈጠኝ።
104ከትእዛዝህ የተነሣ አስተዋልሁ፤
ስለዚህ የዐመፃን መንገድ ጠላሁ።
ኖን።
105ሕግህ ለእግሬ መብራት፥
ለመንገዴም ብርሃን ነው።
106የጽድቅህን ፍርድ እጠብቅ ዘንድ ማልሁ፥ አጸናሁም።
107እጅግ መከራ ተቀበልሁ፥
አቤቱ፥ እንደ ቃልህ ሕያው አድርገኝ።
108አቤቱ፥ ከአፌ የሚወጣውን ቃል ውደድ፥
ፍርድህንም አስተምረኝ።
109ነፍሴ ሁልጊዜ በእጅህ ውስጥ ናት፤
ሕግህን ግን አልረሳሁም።
110ኃጥኣን ወጥመድን ዘረጉብኝ፤
ከትእዛዝህ ግን አልሳትሁም።
111የልቤ ደስታ ነውና
ምስክርህን ለዘለዓለም ወረስሁ።
112ለዘለዓለም ያለ ነቀፋ
ትእዛዝህን አደርግ ዘንድ ልቤን መለስሁ።
ሳምኬት።
113ዐመፀኞችን ጠላሁ፥ ሕግህን ግን ወደድሁ።
114አንተ ረዳቴና መጠጊያዬ ነህ፥
በቃልህም ተማመንሁ።
115እናንተ ዐመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ፥
የአምላኬንም ትእዛዝ ልፈልግ።
116እንደ ቃልህ ተቀበለኝ፥ ሕያውም እሆናለሁ፤
ከተስፋዬም አታሳፍረኝ።
117ርዳኝም፥ አድነኝም፥
ሁልጊዜም ፍርድህን አነብባለሁ።
118ምኞታቸው ዐመፃ ነውና
ከሥርዐትህ የሚርቁትን ሁሉ አጐሳቈልሃቸው።
119የምድር ኃጥኣን ሁሉ ወንጀለኞች#ዕብ. “እንደ ርኵሰት አጠፋሃቸው” ይላል። ናቸው፤
ስለዚህ ምስክርህን ወደድሁ።
120መፈራትህን በሥጋዬ ውስጥ አስማማ፤
ከፍርድህ የተነሣ ፈርቻለሁና።
ዔ።
121ፍርድንና ጽድቅን ሠራህ፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሠራሁ” ይላል።
ለሚያስጨንቁኝ አሳልፈህ አትስጠኝ።
122ባሪያህን በመልካም ጠብቀው፤
ትዕቢተኞችም አይጋፉኝ።
123ዐይኖቼ ለማዳንህ፥
ለጽድቅህም ቃል ፈዘዙ።
124ለባሪያህ እንደ ምሕረትህ አድርግ፥
ፍርድህንም አስተምረኝ።
125እኔ ባሪያህ ነኝ፤ እንዳስተውል አድርገኝ፥
ምስክርህንም አውቃለሁ።
126ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ አለው፥
ሕግህንም ሻሩት።
127ስለዚህ ከወርቅና ከዕንቍ ይልቅ ትእዛዝህን ወደድሁ።
128ስለዚህ ወደ ትእዛዝህ ሁሉ አቀናሁ፥
የዐመፃንም መንገድ ሁሉ ጠላሁ።
ፌ።
129ምስክርህ ድንቅ ነው፤
ስለዚህ ነፍሴ ፈለገችው።
130የቃልህ ነገር ያበራል፥
ሕፃናትንም አስተዋዮች ያደርጋል።
131አፌን ከፈትሁ፥ ልቡናዬንም አሰፋሁ፤
ትእዛዝህን ወድጃለሁና።
132ስምህን ለሚወድዱ እንደምታደርገው ፍርድ፥
ወደ እኔ ተመልከት፥ ይቅርም በለኝ።
133መንገዴንና አካሄዴን እንደ ቃልህ አቅና፤
ኀጢአትም ሁሉ ድል አይንሳኝ።
134ከሰው ቅሚያ አድነኝ፤
ትእዛዝህንም እጠብቃለሁ ።
135በባሪያህ ላይ ፊትህን አብራ፥
ፍርድህንም አስተምረኝ።
136ሕግህን አልጠበቅሁምና
የውኃ ፈሳሽ ከዐይኖች ፈሰሰ።
ጻዴ።
137አቤቱ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፥
ፍርድህም ቅን ነው።
138ምስክርህን በጽድቅ አዘዝህ፥
እጅግም ቅን ነው።
139ጠላቶቼ ትእዛዝህን ረስተዋልና
የቤትህ ቅንዓት አቀለጠኝ።
140ቃልህ እጅግ የጋለ#ዕብ. “የነጠረ” ይላል። ነው፥
ባሪያህ ግን ወደደው።
141እኔ ታናሽና የተናቅሁ ነኝ፥
ሕግህን ግን አልረሳሁም።
142ጽድቅህም የዘለዓለም ጽድቅ ነው፥
ቃልህም የታመነ ነው።
143መከራና ችግር አገኙኝ፤
ትእዛዝህ ግን ትምህርቴ ነው።
144ምስክርህ ለዘለዓለም እውነት ነው፤
እንዳስተውል አድርገኝ፥ በሕይወትም አኑረኝ።
ቆፍ።
145በፍጹም ልቤ ጮኽሁ፥ አቤቱ ስማኝ፤
ፍርድህንም ፈለግሁ።
146ወደ አንተ ጮኽሁ፥ ስማኝ#“ስማኝ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። አድነኝም።
ምስክርህንም ልጠብቅ።
147ወደ ተራሮች ደረስሁ፥ ጮኽሁም።
ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና።
148ዐይኖቼ ለመማለድ ደረሱ፥
ቃልህን እናገር ዘንድ።#“ቃልህን እናገር ዘንድ” የሚለው በዕብ. የለም።
149አቤቱ፥ እንደ ይቅርታህ ቃሌን ስማ፤
እንደ ፍርድህ ሕያው አድርገኝ።
150በዐመፃ የከበቡኝ ቀረቡ፥
ከሕግህ ግን ራቁ።
151አቤቱ አንተ ቅርብ ነህ፥
መንገዶችህም ሁሉ የቀኑ ናቸው።
152ለዘለዓለም እንደ መሠረትሃቸው
ከቀድሞ ጀምሮ ምስክሮችህን ዐወቅሁ።
ሬስ።
153ሕግህን አልረሳሁምና
ችግሬን ተመልከት፥ አድነኝም።
154ፍርዴን ፍረድ አድነኝም፤
ስለ ቃልህም ሕያው አድርገኝ።
155ሕይወት ከኃጥኣን የራቀ ነው፥
ፍርድህን አልፈለጉምና።
156አቤቱ፥ ይቅርታህ እጅግ የበዛ ነው፤
እንደ ፍርድህም ሕያው አድርገኝ።
157የከበቡኝና ያስጨነቁኝ ብዙዎች ናቸው፤
ከምስክርህ ግን ፈቀቅ አላልሁም።
158ቃልህን አልጠበቁምና
ሰነፎችን አይቼ አዘንሁ።
159ትእዛዝህን እንደ ወደድሁ ተመልከት፤
አቤቱ፥ በይቅርታህ ሕያው አድርገኝ።
160የቃልህ መጀመሪያ እውነት ነው፥
ፍርድህም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እውነተኛ ፍርድህም ...” ይላል። ሁሉ ለዘለዓለም እውነት ነው።
ሣን።
161አለቆች በከንቱ አሳደዱኝ፤
ከቃልህ የተነሣ ግን ልቤ ደንገጠብኝ።
162ብዙ ምርኮ እንዳገኘ በቃልህ ደስ አለኝ።
163ዐመፃን ጠላሁ ተጸየፍሁም፤
ሕግህን ግን ወደድሁ።
164ስለ እውነት ፍርድህ ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ።
165ስምህን ለሚወድዱ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሕግህን ለሚወዱ” ይላል። ብዙ ሰላም ነው፥
ዕንቅፋት የለባቸውም።
166አቤቱ፥ ማዳንህን ተስፋ አደረግሁ፥
ትእዛዛትህንም ጠበቅሁ።
167ነፍሴ ምስክርህን ጠበቀች፥
እጅግም ወደደችው።
168አቤቱ፥ መንገዶችህ ሁሉ በፊትህ ናቸውና።
ትእዛዝህንና ምስክርህን ጠበቅሁ።
ታው።
169አቤቱ፥ ልመናዬ ወደ አንተ ትቅረብ፤
እንደ ቃልህም አስተዋይ አድርገኝ።
170አቤቱ፥ ምልጃዬ ወደ ፊትህ ትድረስ፤
እንደ ቃልህም አድነኝ።
171ፍርድህን አስተምረኸኛልና
ከንፈሮች ምስጋናህን ይናገራሉ።
172ትእዛዛትህ ሁሉ ጽድቅ ናቸውና፥
አንደበቴ ቃልህን ተናገረ።
173ትእዛዛትህን ወድጃለሁና
ቀኝህ የሚያድነኝ ይሁን።
174አቤቱ፥ ማዳንህን ናፈቅሁ፤
ሕግህም ትምህርቴ ነው።
175ነፍሴ ትኑርልኝ ላመስግንህም፥
ፍርድህም ይርዳኝ።
176እንደ ጠፋ በግ ተዘነጋሁ፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ተበዘበዝሁ” ይላል።
ትእዛዛትህን አልረሳሁምና ባሪያህን ፈልገው።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 118: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ