መዝሙረ ዳዊት 18
18
ለመዘምራን አለቃ የዳዊት መዝሙር።
1ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥
የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል።
2ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፥
ሌሊትም ለሌሊት ጥበብን#ዕብ. “ዕውቀትን” ይላል። ትናገራለች።
3ቃላቸው ያልተሰማበት ነገር የለም፥ መናገርም የለም፥
4ቃላቸው ወደ ምድር ሁሉ ወጣ።
ነገራቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ደረሰ።
5በፀሐይ ውስጥ ድንኳኑን አደረገ፥
እርሱም እንደ ሙሽራ ከእልፍኙ ይወጣል፤
በመንገዱ እንደሚራመድ አርበኛ ደስ ይለዋል።
6አወጣጡ ከሰማያት ዳርቻ ነው፥
መግቢያውም እስከ ዓለም ዳርቻ ነው፤
ከትኩሳቱም የሚሰወር የለም።
7የእግዚአብሔር ሕግ ንጹሕ ነው፤ ነፍስንም ይመልሳል፤
የእግዚአብሔር ምስክር የታመነ ነው፤ ሕፃናትንም ጠቢባን ያደርጋል።
8የእግዚአብሔር ሥርዐት ቅን ነው፥ ልብንም ደስ ያሰኛል፤
የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፥ ዐይኖችንም ያበራል።
9እግዚአብሔርን መፍራት ንጹሕ ነው፥ ለዘለዓለምም ይኖራል፤
የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ቅንነት በአንድነት ነው።
10ከወርቅና ከክቡር ዕንቍ ይልቅ ይወደዳል፤
ከማርና ከማር ወለላም ይልቅ ይጣፍጣል።
11ባሪያህ ደግሞ ይጠብቀዋል፤
በመጠበቁም ብዙ ዋጋ ይቀበላል።
12ስሕተትን ማን ያስተውላታል?
ከተሰወረ ኀጢአቴ አንጻኝ።
13ከልዩ ሰው ባሪያህን አድነው።
ካልገዙኝ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥
ከታላቁም ኀጢአቴ እነጻለሁ።
14የአንደበቴ ቃል ያማረ ይሁን፤
የልቤ ዐሳብም ሁልጊዜ በፊቴ#ግሪክ ሰባ. ሊ. እና ዕብ. “በፊትህ” ይላል። ነው
አቤቱ ረድኤቴ መድኀኒቴም።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 18: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ