መዝሙረ ዳዊት 77
77
የአሳፍ ትምህርት።
1ሕዝቤ ሆይ፥ ሕጌን አድምጡ፥
ጆሮአችሁንም ወደ አፌ ቃል አዘንብሉ።
2አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤
ከቀድሞ ጀምሮ ያለውንም ምሳሌ እናገራለሁ።
3የሰማነውንና ያየነውን፥#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ያወቅነውን” ይላል።
አባቶቻችንም የነገሩንን፥
ለሚመጣ ትውልድ ከልጆቻቸው አልሰወሩም።
4የእግዚአብሔርን ምስጋና ተናገሩ፥
ኀይሉንና ያደረገውንም ተአምራት።
5ለያዕቆብ ያቆመውን ምስክር፥
ለእስራኤልም የሠራውን ሕግ፥
ለአባቶቻችን ያዘዘውን
ለልጆቻቸው ይነግሩ ዘንድ፥
6የሚመጣ ትውልድ የሚወለዱም ልጆች ያውቁ ዘንድ፥
ተነሥተውም ለልጆቻቸው ይነግራሉ።
7ተስፋቸውን በእግዚአብሔር እንዲያደርጉ፥
የእግዚአብሔርንም ሥራ እንዳይረሱ፥
ትእዛዙንም እንዲፈልጉ፤#ዕብ. “እንዲጠብቁ” ይላል።
8እንደ አባቶቻቸው እንዳይሆኑ፥
ጠማማና የምታስመርር ትውልድ፥
ልብዋን ያላቀናች ትውልድ፥
መንፈስዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነች።
9የኤፍሬም ልጆች ቀስታቸውን ገትረው ይወጉ ነበር።
በሰልፍ ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ።
10የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁምና፥
በሕጉም ለመሄድ እንቢ አሉ፤
11ረድኤቱንና ያሳያቸውን ተአምራቱን ረሱ፥
12በግብጽ ሀገርና በጣኔዎስ በረሃ
በአባቶቻቸው ፊት የሠራውን ተአምራት።
13ባሕርን ከፍሎ አሳለፋቸው፤
ውኆችን እንደ ረዋት ውኃ#ዕብ. “እንደ ክምር” ይላል። አቆመ።
14ቀን በደመና መራቸው፥
ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን።
15ዓለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፤
ከብዙ ጥልቅ እንደሚገኝ ያህል አጠጣቸው።
16ውኃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ።
ውኃንም ከዓለት አፈለቀ፥
17ነገር ግን እርሱን መበደልን እንደገና ደገሙ፥
ልዑልንም በምድረ በዳ አስመረሩት።
18ለነፍሳቸው መብልን ይፈልጉ ዘንድ፥
እግዚአብሔርን በልባቸው ፈተኑት።
19እግዚአብሔርን እንዲህ ብለው አሙት፦
“እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድን ያሰናዳ ዘንድ
20ዓለቱን ይመታ ዘንድ ውኃንም ያፈስ ዘንድ ይችላልን?
እንጀራን መስጠትና ለሕዝቡስ ማዕድን መሥራት ይችላልን?”
21እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፤
በያዕቆብም ላይ እሳት ነደደ፥
መቅሠፍትም በእስራኤል ላይ ወጣ፤
22በእግዚአብሔር አላመኑምና፥
በማዳኑም አልተማመኑምና።
23ደመናውንም ከላይ አዘዘ፥
የሰማይንም ደጆች ከፈተ፤
24ይበሉም ዘንድ መናን አዘነበላቸው፥
የሰማይንም እንጀራ ሰጣቸው።
25የመላእክትንም እንጀራ የሰው ልጆች በሉ።
የሚበቃቸው ስንቅንም ላከላቸው።
26ከሰማይ ዐዜባዊ ነፋስን አስነሣ፥
በኀይሉም መስዓዊ ነፋስን አመጣ፤
27ሥጋን እንደ አፈር፥
የሚበርሩትንም ወፎች እንደ ባሕር አሸዋ አዘነበላቸው፤
28በሰፈራቸው መካከል፥
በድንኳናቸውም ዙሪያ ወደቀ።
29በሉ፥ እጅግም ጠገቡ፤
ለምኞታቸውም ሰጣቸው።
30ከወደዱትም አላሳጣቸውም፤
መብላቸውም ገና በአፋቸው ሳለ፥
31የእግዚአብሔር መቅሠፍት በላያቸው መጣ፥
ከእነርሱም ብዙዎቹን ገደለ፤
የእስራኤልንም ምርጦች አሰናከለ።
32ከዚህም ሁሉ ጋር እንደ ገና እርሱን በደሉ፥
ተአምራቱንም አላመኑም፤
33ቀኖቻቸውም በከንቱ አለቁ፥
ዓመቶቻቸውም በችኮላ አለፉ።
34በገደላቸውም ጊዜ ወዲያው ፈለጉት፤
ተመለሱ፥ ወደ እግዚአብሔርም ገሠገሡ፤
35ረዳታቸውም እግዚአብሔር፥
መድኀኒታቸውም ልዑል እግዚአብሔር እንደ ሆነ ዐሰቡ።
36በአፋቸው ብቻ ወደዱት፤
በአንደበታቸውም ዋሹበት፤
37ልባቸውም ከእርሱ ጋር አልቀናም፥
በቃል ኪዳኑም አልተማመኑትም።
38እርሱ ግን መሐሪ ነው፥
ኀጢአታቸውንም ሁሉ ይቅር አላቸው፥ አላጠፋቸውምም፤
ቍጣውንም መመለስ አበዛ፥
መዓቱንም ሁሉ አላቃጠለም።
39ሥጋም እንደ ሆኑ ዐሰበ።
መንፈስ ከወጣ በኋላ አይመለስም
40በምድረ በዳ ምን ያህል አስቈጡት፥
በበረሃም አሳዘኑት።
41ተመለሱ፥ እግዚአብሔርንም ፈተኑት፥
የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት።
42እነርሱም እጁን አላሰቡም፥
ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን፥
43በግብፅ ያደረገውን ተአምራቱን፥
በጣኔዎስም በረሃ ያደረገውን ድንቁን።
44ወንዞቻቸውንም ወደ ደም ለወጠ፥
ምንጮቻቸውንም ደግሞ እንዳይጠጡ።
45ዝንቦችንም በላያቸው ሰደደባቸው፥ በሉአቸውም፤
ጓጕንቸሮችን ሰደደ፥ አረከሳቸውም።#ዕብ. “አጠፋቸው” ይላል።
46ፍሬያቸውን ለኩብኩባ፥
ሥራቸውንም ለአንበጣ ሰጠ።
47ወይናቸውንም በበረዶ፥
በለሳቸውንም በውርጭ አጠፋ።
48እንስሶቻቸውን ለበረዶ፥
ሀብታቸውንም ለእሳት ሰጠ።
49የመዓቱን መቅሠፍት በላያቸው ሰደደ፤
መቅሠፍትን፥ መዓትንም መከራንም
በክፉዎች መላእክት ሰደደ።
50ለቍጣው መንገድን ጠረገ፤
ነፍሳቸውንም ከሞት አላዳናትም፥
እንስሶቻቸውንም በሞት ውስጥ ዘጋ፤
51በኵሮቻቸውንም ሁሉ በግብፅ ምድር፥
የድካማቸውንም መጀመሪያ በቤቶቻቸው ውስጥ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “በካም ድንኳኖች” ይላል። ገደለ።
52ሕዝቡን ግን እንደ በጎች አሰማራቸው፥
እንደ መንጋም ወደ ምድረ በዳ አወጣቸው።
53በተስፋም መራቸው አልፈሩምም፥
ጠላቶቻቸውንም ባሕር ደፈናቸው።
54ወደ መቅደሱም ተራራ ወሰዳቸው፥
ቀኙ ወደ ፈጠረችው ተራራ፤
55ከፊታቸውም አሕዛብን አባረረ፥
ርስቱንም በገመድ አካፈላቸው፥
የእስራኤልንም ወገኖች በቤታቸው አኖረ።
56ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔርን ፈተኑት፥
አሳዘኑትም፥ ምስክሩንም አልጠበቁም፤
57ተመለሱም፥ እንደ አባቶቻቸውም ከዱ፤
እንደ ጠማማ ቀስትም ሆኑ፤
58በኮረብቶቻቸውም አስቈጡት፥
በተቀረጹ ምስሎቻቸውም አስቀኑት።
59እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ።
እስራኤልንም እጅግ ናቃቸው፤
60የሴሎምንም ድንኳን ተዋት፥
በሰዎች መካከል ያደረባትን ድንኳኑን።
61ኀይላቸውን ለምርኮ፥
ጌጣቸውንም#ዕብ. “ክብሩን” ይላል። በጠላት እጅ ሰጠ።
62ሕዝቡንም በጦር ውስጥ ዘጋቸው፥
ርስቱንም ቸል አላቸው።
63ጐልማሶቻቸውን እሳት በላቻቸው፥
ቈነጃጅቶቻቸውም አላለቀሱም።
64ካህኖቻቸውም በሰይፍ ወደቁ፥
ባልቴቶቻቸውም አላለቀሱላቸውም።
65እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፥
የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኀያልም ሰው፤
66ጠላቶቹንም በኋላው ገደለ፤
የዘለዓለምንም ኀሣር ሰጣቸው።
67የዮሴፍንም ድንኳን ተዋት፥
የኤፍሬምንም ወገን አልመረጠውም፤
68የይሁዳን ወገን ግን መረጠ፥
የወደደውን የጽዮንን ተራራ።
69መቅደሱን እንደ አርአያም#ግእዝ “በአርያም” ይላል። ሠራ፥
ለዘለዓለምም በምድር ውስጥ መሠረታት።
70ባሪያው ዳዊትንም መረጠው፥
ከበጎቹም መንጋ ውስጥ ወሰደው፤
71ከሚያጠቡ በጎችም በኋላ፥#ግእዝ “እምድረ ሐራሳት” ይላል።
ባሪያውን ያዕቆብን ርስቱን እስራኤልንም ይጠብቅ ዘንድ ወሰደው።
72በልቡ ቅንነት ጠበቃቸው፥
በእጁም ጥበብ መራቸው።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 77: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ