መጽሐፈ ሲራክ 1
1
የጥበብ መንገዶች
1የጥበብ ሁሉ መገኛዋ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፥ ለዘለዓለምም ከእርሱ ጋር ናት።
2የባሕር አሸዋን፥ የዝናም ጠብታን፥ የዘለዓለምነት ቀኖችንስ ማን ቈጠረ?
3የሰማይን ምጥቀት፥ የምድርን ስፋት፥ የባሕርን ጥልቀት፥ ጥበብንም ማን መርምሮ አገኛቸው?
4ጥበብ ከሁሉ አስቀድሞ ተፈጠረች።
5የጥበብ መታሰቧ ከጥንት ጀምሮ ነው።#በግሪክኛው “የጥበብ መታሰቧ ከጥንት ጀምሮ ነው” የሚለው በምዕ. 1 ቍ. 4 ውስጥ ነው ግሪክኛው ቍ. 5 የለውም አንዳንድ ዘሮች ቍ. 5 ላይ “የጥበብ ምንጭ የልዑል እግዚአብሔር ቃል ነው መንገዶችዋም የእግዚአብሔር የዘለዓለም ትእዛዛት ናቸው” የሚል ይጽፋሉ።
6የጥበብ ሥርዋ ለማን ተገለጠ?
7ምክሯንስ ማን ዐወቀ?#በአንዳንድ ዘሮች ምዕ. 1 ቍ. 7 ላይ “የጥበብ ዕውቀት ለማን ተገለጠች የልምዷንስ ብልጽግና ማን ዐወቀ” ይላል።
8ጥበበኛ አንድ ነው፥ እጅግም የሚያስፈራ ነው፤
እርሱም በዙፋኑ ላይ ጸንቶ ይኖራል።
9እርሱ እግዚአብሔር ሠራት፤ አያት፥ ሰፈራትም።
በሥራውም ሁሉ ላይ አሳደራት፤
10እርስዋም እንደ እርሱ ስጦታ ከሥጋዊ ሁሉ ጋር ናት፥
ለሚወዱትም ሁሉ እርስዋን ሰጣቸው።
11እግዚአብሔርን መፍራት ክብር ነው፥
የሚያስመካም ነው፥ ደስታም ነው፥ የደስታ ዘውድም ነው።
12እግዚአብሔርን መፍራት የልብ ደስታ ነው፤
ሐሤትንም ይሰጣል፤ ደስም ያሰኛል፥ የሕይወትንም ዘመን ያረዝማል።
13እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ፍጻሜው ያምራል፤
በሚሞትበትም ቀን ይከብራል።
14የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤
በእናታቸው ማኅፀን ከምእመናን ጋር ተፈጠረች።
15ከሰዎችም ጋር የዓለምን መሠረት ፈጠረች፤
ከዘራቸውም ጋር ልትኖር ታመነች።
16ጥበብን መጥገብ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥
በፍሬዋም ታጠግባቸዋለች።
17በቤቶችዋም ደስታ መልትዋል፥
በቦታዎችዋም ፍሬ አለ።#ግሪክኛው “እርስዋ ቤቶቻቸውን ሁሉ በደስታ ትሞላለች፥ ጎታዎቻቸውንም በምርት ትሞላለች” ይላል።
18የጥበብ ዘውድዋ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤
ሰላምን ያመጣታል፥ ይፈውሳል፥ ያድናልም።
19ፈጣሪዋ አያት፥ ሰፈራትም፥
የምክርንና የዕውቀትን የጥበብንም ምንጭ አፈሰሰ፥
የሚያጸኗትንም ሰዎች አገነናቸው፥ አከበራቸውም።
20የጥበብ ሥር እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥
ቅርንጫፍዋም የሕይወትን ዘመን ያረዝማል።
ከኀጢአት ለመራቅ ራስን መቈጣጠር
21በተቈጣ ጊዜ መከራ ይመጣበታልና
ቍጡና ዐመፀኛ ሰው መጽደቅ አይችልም።
22ጊዜዋን እስክታሳልፍ ድረስ ቍጣን ታገሣት፤
ኋላም ደስ ታሰኝሃለች።
23ጊዜውን እስክታገኝ ድረስ ነገርህን ሰውር፤
ብዙ ሰዎችም ጥበብህን ይናገራሉ።
24በጥበብ መዛግብት የምሳሌ ትምህርት አለ።
ኀጢአተኛ እግዚአብሔርን የሚፈራውን ይጸየፈዋል።
25ጥበብን ከወደድሃት ትእዛዞቹን ጠብቅ፤
እግዚአብሔርም እርስዋን ይሰጥሃል።
26ጥበብም፥ ዕውቀትም፥ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤
ፈቃዱም ሃይማኖትና የዋሀት ነው።
27እግዚአብሔርን መፍራትን አትዘንጋ።
28እየተጠራጠርህ እግዚአብሔርን በሁለት ልብ አታገልግለው።
29በሰው አፍ አትውደቅ፥#ግሪኩ “በሰው ፊት ግብዝ አትሁን” ይላል።
ከንፈሮችህንም ጠብቅ።
30እንዳቷረድ ሰውነትህም እንዳትወድቅ ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤
እግዚአብሔርም የሰወርኸውን ይገልጥብሃል።
እግዚአብሔርን በመፍራት አልመጣህምና፥ በልብህም ሽንገላ ሞልትዋልና
በብዙዎች ሰዎች መካከል ይጥልሃል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 1: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ