መጽሐፈ ሲራክ 4
4
ለድሆችና ለችግረኞች መደረግ ስለሚገባው
1ልጄ ሆይ፥ ድሃውን የሚኖርበትን አትከልክለው፤
ከሚለምንህም ዐይኖችህን አትመልስ።
2የተራበች ሰውነትን አታሳዝን፥
ያዘነ ሰውንም አታበሳጭ።
3ያዘነ ልቡናን አታስደንግጥ፤
የሚለምንህንም አትለፈው።
4በሚያገለግልህም ቤተ ሰብህ ላይ አትቈጣ፤
ከድሃም ፊትህን አትመልስ።
5ከሚለምንህም ዐይንህን አትመልስ፤
ይረግምህም ዘንድ ለሰው ምክንያት አትስጠው፤
6በልቡናው አዝኖ ቢረግምህ
ፈጣሪው ጸሎቱን ይሰማዋልና።
7በብዙ ሰዎች ዘንድ እንድትወደድ ሁን፤
በዳኞች ዘንድ አገልግል፤ ራስህንም ከፍ ከፍ አታድርግ።
8ድሃውን በጆሮህ አድምጠው፤
በየዋህነትም በጎ ቃልን መልስለት።
9የተበደለውንም ሰው ከሚበድለው ሰው እጅ አድነው፤
ለእርሱም መፍረድን ቸል አትበል።
10አባቱ ለሞተበት ልጅ እንደ አባት ሁነው፤
ለእናቱም እንደ ባሏ ቁምላት፤
እንደ ልዑልም ልጆች ትሆናለህ፥
ከእናትህም ይልቅ ይወድሃል።
ጥበብ ከፍ ከፍ እንደምታደርግ
11ጥበብስ ልጆችዋን ከፍ ከፍ አደረገቻቸው፤
የሚፈልጓትንም ትቀበላቸዋለች።
12እርሷን የወደደ ሕይወቱን ወደደ፤
ወደ እርሷም የሚገሠግሥ ሰው በደስታ ይሞላል።
13አጥንቶ የሚይዛት ሰውም ክብርን ይወርሳል፥
እርስዋም ያደረችበትን እግዚአብሔር ይባርካል።
14እርስዋንም የሚያገለግሉ ቅዱሱን ያገለግላሉ፤
የሚወዱኣትንም እግዚአብሔር ይወዳቸዋል።
15እርስዋን የሚሰማትም አሕዛብን ይገዛል፤
እርስዋንም የሚያደምጣት ሰው ተዘልሎ ይኖራል።
16ካመንኻት ታገኛታለህ፤
በዘመንህም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች።
17ከእርሱ ጋር ትሄድ ዘንድ ትቀድማለች፤
ፈጽማም ታስፈራዋለች፥
ሰውነቱን እስክታስገዛና በተግሣጽዋ እስክትፈትነው ድረስ፥
ትገርፈዋለች ታስተምረዋለችም።
18ከዚህ በኋላ ዳግመኛ ተቀብላ ደስ ታሰኘዋለች፤
ምሥጢርዋንም ትገልጥለታለች።
19ከእርሷ ወጥቶ ቢስት ግን ትለየዋለች።
በጠላቱም እጅ ትጥለዋለች።
20ጊዜውን ጠብቅ፥
ከክፉ ነገርም ተጠንቀቅ፤
ስለ ነፍስህ በማፈር አታድላ።
21በማፈር ኀጢአትን የሚሠራ አለና፤
በማፈርም ጽድቅን#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ይከብራል” ይላል። የሚሠራ ሞገስንም የሚያገኝ አለና።
22ጕዳት በራስህ ስለሚደርስብህ የሰው ፊት አይተህ አታድላ፥
ሰውነትህን እንዳትጥል አትፈር።
23የሚናገርን ሰው መናገሩን አትከልክለው፤
ከቃሉ የተነሣ ጥበቡ ይታወቃልና፥
ትምህርቱም ከአንደበቱ ንግግር የተነሣ ይታወቃልና።
24ጽድቅን አትቃወም።
ስለ በደልኸውም በደል ንስሓ ግባ።
25ኀጢአትህንም መናገር አትፈር፥
የውኃ ሙላትን አትደፋፈር።
26ለሰነፍ ሰው ራስህን አታዋርድ፤
ለታላቅ ሰው ፊትም አታድላ።
27ፈጣሪህ እግዚአብሔር ስለ አንተ ይከራከርልሃልና
ለሞት እስክትደርስ ስለ እውነት ተከራከር።
28በአፍህ አውታታ አትሁን፤
ሥራህንም ቸል አትበል።
29በቤትህ እንደ አንበሳ አስፈሪ አትሁን፤
ቤተ ሰብህንም አታስደንግጥ፤
30ለመበደር እጅህን አትዘርጋ።
በመክፈልም ጊዜ እጅህን ለመሰብሰብ አትመለስ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 4: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ