መጽሐፈ ጥበብ 2
2
ስለ ክፉ አሳብ
1የቀና ነገርን ሳያስቡ ራሳቸው እንዲህ አሉ፥ ሕይወታችን ጥቂት ነው፥ የሚያሳዝንም ነው-። ለሰውም ሞት መድኀኒት የለውም፥ ከመቃብርም የተመለሰ የታወቀ የለምና። 2እኛ በከንቱ ተፈጥረናልና ከዚህም በኋላ እንዳልተፈጠርን እንሆናለን፤ በአፍንጫችን ያለ ትንፋሻችን እንደ ጢስ ነውና። በልቡናችንም እንቅስቃሴ የብልጭልጭታ ቃል አለና። 3ከሞተ በኋላ ሥጋችን ትቢያ ይሆናል፤ መንፈሳችንም እንደ ጉም ተን ይበተናልና። 4ስማችንም በጊዜ ይዘነጋል፤ ሥራችንንም የሚያስበው ማንም የለም፤ ሕይወታችንም እንደ ደመና ፍለጋ ያልፋል፤ እንደ ጉምም ይበተናል፤ በፀሐይ ጨረር እንደ ተበተነ፥ በሙቀቱም እንደ ቀለጠ ውርጭ ይሆናል።
5ሕይወታችንም እንደ ጥላ ያልፋልና፥ ይህ የተወሰነ ነገር ስለሆነ ለሞታችን መከልከል የለውም፤ ማንም አይመልሰውምና። 6ኑ ባለው መልካም ነገር ደስታን እናድርግ፤ በጐልማሳነታችንም ወራት ሳለን በመትጋት በሰውነታችን ደስ የሚያሰኘውን እናድርግ። 7ዋጋው ብዙ የሆነ ወይን እንጠጣ፤ የሚሸት ሽቱንም እንቀባ፤ የመፀው አበባም አይለፈን። 8ቡቃያችን ሳይጠወልግ ጽጌረዳን እንቀዳጅ፤ ከትዕቢታችን አበባ የማይሳተፍ ማንም አይኑር። 9ከእኛ መካከል ደስታችን የማይገባው ሰው አይኑር፤ እርሱ ዕድላችን፥ ርስታችንም ነውና በየቦታው ለደስታችን ምልክት እንተው።
10ጻድቁን ድሃ እንቀማ፤ ለባልቴቲቱም አንራራ፤ ዕድሜው ብዙ ከሆነ ከሽማግሌም ሽበት የተነሣ አንፈር። 11ኀይላችን የጽድቅ ሕግ ይሁነን፤ ደካማ ሕሊና የተናቀ ይባላልና።
12ኑ፤ ጻድቁን እንግደለው፤ በእኛ ጭንቅና ጽኑዕ ሆኖብናልና፥ ሥራችንንም ይቃወማልና፤ ሕግ በማጣታችንም ያሽሟጥጠናልና፥ የትምህርታችንንም በደል ይሰብካልና። 13“እግዚአብሔርንም ማወቅ በእኔ አለ” ይላል፤ ራሱንም የእግዚአብሔር ልጅ ያደርጋል። 14ሕሊናችንንም የሚዘልፍ ሆኖብናል። 15በመልኩም በእኛ ጭንቅ ሆኖብናል፤ አኗኗሩም ከሌላ ጋር አይመሳሰልም፤ መንገዱም ልዩ ነው። 16በእርሱ ዘንድም የተናቅን ሆነናል፤ ከርኵሰትም እንደሚርቅ ከመንገዳችን ይርቃል። የጻድቃንን መጨረሻ ያመሰግናል፤ እግዚአብሔርም አባቱ እንደ ሆነ ይመካል።
17ነገሩም ቀዋሚ እንደ ሆነ እንይ፥ ከመልኩም የተነሣ የሚሆነውን እንመርምር።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ፍጻሜው ምን እንደ ሆነ እንመልከት” ይላል። 18የእግዚአብሔርስ እውነተኛ ልጅ ከሆነ ያድነው፤ ከሚቃወሙትም እጅ ይታደገው። 19ቅንነቱንም እናውቅ ዘንድ በስድብና በመከራ እንመርምረው። ትዕግሥቱንም በክፉ እንፈትነው። 20እንደ ቃሉ ረዳት ይሆነው እንደ ሆነ የከፋና የተዋረደ ሞትን እንፍረድበት።
ክፋት ልብን እንደሚያሳውር
21ይህን ነገር አሰቡ፤ በዚህም ሳቱ፤ ክፋታቸው የልብ ዕውሮች አድርጋቸዋለችና። 22የእግዚአብሔርን ምሥጢር አላወቁም፤ የጻድቁንም ዋጋ ተስፋ አላደረጉም፤ ነውር የሌለባቸውን የንጹሐት ነፍሳትንም ብዙ ክብር አላወቁም።
23እግዚአብሔር ሰውን ያለ ሞት ፈጥሮታልና፥ በራሱም አምሳል ፈጥሮታልና። 24ነገር ግን በዲያብሎስ ቅንዐት ሞት መጣ፥ ወደዚህ ዓለምም ገባ። 25ከእርሱም ድርሻ የሆኑት ሞትን ሞከሩት።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 2: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ