መጽሐፈ ጥበብ 4
4
1ከበጎነት ጋር አለመውለድ ፍጹም ሥራ ነው፤ በእግአብሔር ዘንድ፥ በሰውም ዘንድ የታወቀች ስለ ሆነች ስም አጠራሯ ሕይወት ነውና። 2በዚህ ዓለም ሳለችም ያከብሯታል፤ ካለፈችም በኋላ ፈጽመው ይወድዷታል፤ በዚህም ዓለም የገድል ድልን እግኝታ፥ የማያልፍ አክሊልንም ተቀዳጅታ ትኖራለች።
3የክፉዎች ሰዎች ልጆች ብዛት አይረባም፤ የከንቱ ተክልም ሥሯ አይታወቅም፤ ጽኑ አኗኗርም አታደርግም። 4ለጊዜውም በቅርንጫፎችዋ ላይ ቅጠል ቢወጣ ሳያድግ ነፋስ ያነዋውጠዋል፤ በነፋሱም ኀይል ይነቀላል። 5ቅርንጫፎችዋም ሳያድጉ ይሰበራሉ፥ ፍሬያቸውም ለመብል የማይሆን ከንቱ ጨርቋ ነው፤ ጊዜው አይደለምና፥ ለመብላትም አይገባምና። 6ከክፉዎች ሰዎች መኝታ የሚወለዱ ልጆችም በተመረመሩ ጊዜ ለእናትና አባታቸው ክፋት ምስክሮች ናቸው። 7ጻድቅ ሰው ግን ለመሞት በደረሰ ጊዜ በዕረፍት ይኖራል።
8የሽምግልና ክብር በዕድሜ ብዛት አይደለም፤ በዓመታትም ቍጥር የሚቈጠር አይደለም። 9ሽበትስ የሰው ዕውቀቱ ነው፤ የሽምግልናም አክሊሏ ያለ ነውር መኖር ነው። 10እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሰው በእርሱ ዘንድ የሚወደድ ይሆናል፤ በኀጢአተኞችም መካከል ሲኖር ይለያል። 11ክፋትም ዕውቀቱን ሳትለውጥበት፥ ይህም ባይሆን ሐሰት ሰውነቱን ሳታስትበት ተነጥቆ ይሄዳል። 12የክፋት ቅንዐት በጎ ሥራዎችን ያጠፋልና፥ የፈቃድ ነዘህላልነትም የዋህ ልቡናን ይለውጣልና። 13በጥቂት ዘመንም ቢሞት ረዥም ዓመታትን ጨርሷል። 14ነፍሱ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝታዋለችና፤ ስለዚህም ከክፉዎች መካከል ተለይቶ በችኮላ ሄደ። 15ልዩ የሆኑ ሰዎች ግን ይህን አይተው ልብ አላደረጉትም፤ የዚህንም ትርጓሜ በልባቸው አላሳደሩትም። የእግዚአብሔር ጸጋው ለጻድቃኑ ነውና የይቅርታው ጕብኝትም ለመረጣቸው ሰዎች ነውና።
የቅዱሳን ድል አድራጊነትና የኃጥኣን ፍርድ
16ጻድቅ ሰው ከሞተ በኋላ በሕይወት ባሉ ክፉዎች ላይ ይፈርዳል። ጐልማሳ ሰውም ፈጥኖ በሚሞትበት ጊዜ የዐመፃ ሽምግልና ዕድሜአቸው በበዛ በክፉዎች ሰዎች ላይ ይፈርዳል። 17ጠቢብ የሆነ የጻድቁን ሞት አይተው እግዚአብሔር ስለ እርሱ ምን እንደ መከረ፥ ወደ እርሱም ለምን እንደ ሰበሰበው አያስተውሉምና። 18እርሱንም አይተው በእርሱ ይጠቃቀሳሉ፤ እግዚአብሔር ግን በእነርሱ ይሥቃል። 19ከዚህም በኋላ ለጐስቋላ ሞት ይሆናሉ፤ ለዘለዓለምም ሙታን ለሚሰደቡበት ስድብ ይሆናሉ። ይቈርጣቸዋልና፥ ይሰነጥቃቸዋልምና፥ ቃልም ሳይኖራቸው በፊታቸው የወደቁ ሆነው ይገኛሉ። ከመሠረታቸውም ያነዋውጣቸዋል፤ ለዘለዓለሙ እንደ ተፈታች ምድር ይሆናሉ፥ የተጨነቁም ይሆናሉ፤ መታሰቢያቸውም ይጠፋል። 20በፍርሃትም ሆነው በኀጢኣታቸው ለመወቀስ ይቀርባሉ፤ ኀጢኣታቸውም በፊታቸው ተገልጦ ይዘልፋቸዋል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 4: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ