የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትን​ቢተ ዘካ​ር​ያስ 12

12
1ስለ እስራኤል የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ሸክም ይህ ነው። ሰማያትን የዘረጋ፥ ምድርንም የመሠረተ፥ የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 2እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን በዙሪያዋ ላሉት ለአሕዛብ ሁሉ የመንገድገድ ዋንጫ አደርጋታለሁ፣ ደግሞም ኢየሩሳሌም ስትከበብ በይሁዳ ላይ እንዲሁ ይሆናል። 3በዚያም ቀን ኢየሩሳሌምን ለአሕዛብ ሁሉ ከባድ ድንጋይ አደርጋታለሁ፣ የሚሸከሙአት ሁሉ እጅግ ይቈስላሉ፣ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በላይዋ ላይ ይከማቻሉ። 4በዚያ ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ፈረስን ሁሉ በድንጋጤ፥ ተቀማጭንም በእብድነት እመታለሁ፣ ዓይኖቼንም በይሁዳ ላይ እከፍታለሁ፥ የአሕዛብንም ፈረሶች ሁሉ በዕውርነት እመታለሁ። 5የይሁዳም አለቆች በልባቸው፦ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ በአምላካቸው በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ብርታት አለ ይላሉ። 6በዚያ ቀን የይሁዳን አለቆች በእንጨት መካከል እንዳለ ትንታግ፥ በነዶችም መካከል እንዳለ እንደ ፋና ነበልባል አደርጋቸዋለሁ፣ በቀኝና በግራ በዙሪያ ያሉትን አሕዛብ ሁሉ ይበላሉ፣ ከዚያም ወዲያ ኢየሩሳሌም በስፍራዋ በኢየሩሳሌም ትኖራለች። 7እግዚአብሔርም የዳዊት ቤት ክብርና የኢየሩሳሌም ሰዎች ክብር በይሁዳ ክብር ላይ እንዳይታበይ የይሁዳን ድንኳኖች አስቀድሞ ያድናል። 8በዚያ ቀን እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩት ይመክትላቸዋል፣ በዚያም ቀን ከእነርሱ መካከል ደካማው እንደ ዳዊት ይሆናል፣ የዳዊትም ቤት በፊታቸው እንደ እግዚአብሔር መልአክ እንደ አምላክ ይሆናል። 9በዚያም ቀን በኢየሩሳሌም ላይ የሚመጡትን አሕዛብ ሁሉ ለማጥፋት እጋደላለሁ።
10በዳዊትም ቤት ላይ፥ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ላይ፥ የሞገስንና የልመናን መንፈስ አፈስሳለሁ፣ ወደ እርሱም ወደ ወጉት ይመለከታሉ፣ ሰውም ለአንድያ ልጁ እንደሚያለቅስ ያለቅሱለታል፥ ሰውም ለበኵር ልጁ እንደሚያዝን በመራራ ኅዘን ያዝኑለታል። 11በዚያ ቀን በመጊዶን ሜዳ እንደ ነበረው እንደ ሐዳድሪሞን ልቅሶ ታላቅ ልቅሶ በኢየሩሳሌም ይሆናል። 12ምድሪቱም ታለቅሳለች፣ እያንዳንዱ ወገን ለብቻው፥ የዳዊት ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ የናታን ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ 13የሌዊ ቤት ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ የሰሜኢ ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው፣ 14የቀሩት ወገኖች ሁሉ እያንዳንዱ ወገን ለብቻው፥ ሴቶቻቸውም ለብቻቸው ያለቅሳሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ