አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 1

1
ንጉሥ ዳዊት በሽምግልና ዕድሜው
1ንጉሡ ዳዊትም ሸመገለ፤ ዕድሜውም በዛ፤ ልብስም ደረቡለት፤ ነገር ግን አይሞቀውም ነበር። 2ባሪያዎቹም “ለጌታችን ለንጉሡ ድንግል ትፈለግለት፤ በንጉሡም ፊት ቆማ ታገልግለው፤ በጌታችንም በንጉሡ ብብት ተኝታ ታሙቀው፤” አሉት። 3በእስራኤልም አገር ሁሉ የተዋበች ቆንጆ ፈለጉ፤ ሱነማይቱን አቢሳንም አገኙ፤ ወደ ንጉሡም ይዘዋት መጡ። 4ቆንጆይቱም እጅግ ውብ ነበረች፤ ንጉሡንም ትረዳውና ታገለግለው ነበር፤ ንጉሡ ግን አያውቃትም ነበር።
አዶንያስ ለመንገሥ የነበረው ፍላጎት
5የአጊትም ልጅ አዶንያስ “ንጉሥ እሆናለሁ፤” ብሎ ተነሣ፤ ሠረገሎችንና ፈረሰኞችን በፊቱም የሚሮጡ አምሳ ሰዎች አዘጋጀ። 6አባቱም ከቶ በሕይወቱ ሳለ “እንዲህ ለምን ታደርጋለህ?” ብሎ አልተቆጣውም ነበር፤ እርሱ ደግሞ እጅግ ያማረ ሰው ነበረ፤ ከአቤሴሎምም በኋላ ተወልዶ ነበር። 7ሴራውም ከጽሩያ ልጅ ከኢዮአብና ከካህኑ ከአብያታር ጋር ነበረ፤ እነርሱም አዶንያስን ተከትለው ይረዱት ነበር። 8ነገር ግን ካህኑ ሳዶቅና የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነቢዩም ናታን ሳሚም ሬሲም የዳዊትም ኀያላን ከአዶንያስ ጋር አልነበሩም። 9አዶንያስም በጎችንና በሬዎችን ፍሪዳዎችንም በዓይንሮጌል አጠገብ ባለችው በዞሔሌት ድንጋይ ዘንድ ሠዋ፤ የንጉሡንም ልጆች ወንድሞቹን ሁሉ፥ የንጉሡንም ባሪያዎች፥ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠራ። 10ነገር ግን ነቢዩን ናታንን፥ በናያስንም፥ ኀያላኑንም፥ ወንድሙንም ሰሎሞንን አልጠራም።
የሰሎሞን መንገሥ
11ናታንም የሰሎሞንን እናት ቤርሳቤህን እንዲህ ብሎ ተናገራት “ጌታችን ዳዊት ሳያውቅ የአጊት ልጅ አዶንያስ እንደ ነገሠ አልሰማሽምን? 12አሁንም ነዪ፤ የልጅሽን የሰሎሞንን ነፍስና የአንቺን ነፍስ እንድታድኝ እመክርሻለሁ። 13ሄደሽ ወደ ንጉሡ ወደ ዳዊት ግቢና ‘ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! ለእኔ ለባሪያህ ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፤ በዙፋኔም ይቀመጣል፤ ብለህ አልማልህልኝምን? ስለ ምንስ አዶንያስ ይነግሣል?’ በዪው። 14እነሆ፥ አንቺ በዚያ ለንጉሥ ስትነግሪ እኔ ከአንቺ በኋላ እገባለሁ፤ ቃልሽንም አጸናለሁ።”
15ቤርሳቤህም ወደ ንጉሡ ወደ እልፍኝ ገባች፤ ንጉሡም እጅግ ሸምግሎ ነበር፤ ሱነማይቱም አቢሳ ታገለግለው ነበር። 16ቤርሳቤህም አጎንብሳ ለንጉሡ እጅ ነሣች፤ ንጉሡም “ምን ትፈልጊያለሽ?” አለ። 17እርስዋም አለችው “ጌታዬ ሆይ! አንተ ለባሪያህ ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፤ በዙፋኔም ይቀመጣል፤’ ብለህ በአምላክህ በእግዚአብሔር ምለህልኛል፤ 18አሁንም፥ እነሆ፥ አዶንያስ መንገሡ ነው፤ አንተም ጌታዬ ንጉሥ ይህን አታውቅም፤ 19እርሱም ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፤ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ ካሁኑንም አብያታርን፥ የሠራዊቱንም አለቃ ኢዮአብን ጠርቶአል፤ ባሪያህን ስሎሞንን ግን አልጠራውም። 20አሁንም፥ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሥ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን ትነግራቸው ዘንድ የእስራኤል ሁሉ ዐይን ይመለከትሃል። 21ይህ ባይሆን፥ ጌታዬ ከአባቶችህ ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ እኔና ልጄ ሰሎሞን እንደ ኀጢአተኞች እንቈጠራለን።”
22እነሆም፥ ለንጉሡ ስትናገር ነቢዩ ናታን ገባ። 23ለንጉሡም “እነሆ፥ ነቢዩ ናታን መጥቶአል፤” ብለው ነገሩት፤ እርሱም ወደ ንጉሡ ፊት በገባ ጊዜ በግምባሩ በምድር ላይ ተደፍቶ ለንጉሡ እጅ ነሣ። 24ናታንም አለ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! አንተ ‘ከእኔ በኋላ አዶንያስ ይነግሣል፤ በዙፋኔም ላይ ይቀመጣል፤’ ብለሃልን? 25እርሱ ዛሬ ወርዶ ብዙ በሬዎችንና ፍሪዳዎችን በጎችንም ሠውቶአል፤ የንጉሡንም ልጆች ሁሉ፥ የሠራዊትንም አለቃ ኢዮአብን፥ ካህኑንም አብያታርን ጠርቶአል፤ እነሆም፥ በፊቱ እየበሉና እየጠጡ ‘አዶንያስ ሺህ ዓመት ይንገሥ!’ ይላሉ። 26ነገር ግን እኔን ባሪያህን፥ ካህኑንም ሳዶቅን፥ የዮዳሄንም ልጅ በናያስን፥ ባሪያህንም ሰሎሞንን አልጠራም። 27በውኑ ይህ ነገር ከጌታዬ ከንጉሡ የተደረገ ነውን? ለባሪያህም ከአንተ በኋላ በጌታዬ በንጉሡ ዙፋን ላይ የሚቀመጠውን አልነገርህምን?”
28ንጉሡም ዳዊት “ቤርሳቤህን ጥሩልኝ፤” ብሎ መለሰ። ወደ ንጉሡም ገባች፤ በንጉሡም ፊት ቆመች። 29ንጉሡም “ነፍሴን ከመከራ ሁሉ ያዳነኝ ሕያው እግዚአብሔርን! 30በእውነት ‘ልጅሽ ሰሎሞን ከእኔ በኋላ ይነግሣል፤ በእኔም ፋንታ በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል፤’ ብዬ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር እንደ ማልሁልሽ፥ እንዲሁ ዛሬ በእውነት አደርጋለሁ፤” ብሎ ማለ። 31ቤርሳቤህም በግምባርዋ በምድር ላይ ተደፍታ ለንጉሡ እጅ ነሣችና “ጌታዬ ንጉሥ ዳዊት ለዘላለም በሕይወት ይኑር!” አለች።
32ንጉሡም ዳዊት “ካህኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ጥሩልኝ፤” አለ። ወደ ንጉሡም ፊት ገቡ። 33ንጉሡም አላቸው “የጌታችሁን ባሪያዎች ይዛችሁ ሂዱ፤ ልጄንም ሰሎሞንን በበቅሎዬ ላይ አስቀምጡት፤ ወደ ግዮንም አውርዱት፤ 34በዚያም ካህኑ ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርገው ይቅቡት፤ ቀንደ መለከትም ነፍታችሁ ‘ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ!’ በሉ። 35በኋላውም ተከትላችሁ ውጡ፤ እርሱም መጥቶ በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ፤ በእኔም ፋንታ ይንገሥ፤ በእስራኤልና በይሁዳም ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዣለሁ።” 36የዮዳሄም ልጅ በናያስ መልሶ ለንጉሡ አለ “ያበጅ! ያድርግ! የጌታዬም የንጉሥ አምላክ ይህን ይናገር! 37እግዚአብሔር ከጌታዬ ከንጉሥ ጋር እንደ ነበረ እንዲሁ ከሰሎሞን ጋር ይሁን! ዙፋኑንም ከጌታዬ ከንጉሡ ዳዊት ዙፋን የበለጠ ያድርግ!”
38ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን የዮዳሄም ልጅ በናያስ ከሊታውያንና ፈሊታውያንም ወረዱ፤ ሰሎሞንንም በንጉሡ በዳዊት በቅሎ ላይ አስቀምጠው ወደ ግዮን አመጡት። 39ካህኑም ሳዶቅ ከድንኳኑ የቅብዓቱን ቀንድ ወስዶ ሰሎሞንን ቀባ፤ ቀንደ መለከትም ነፉ፤ ሕዝቡም ሁሉ “ሰሎሞን ሺህ ዓመት ይንገሥ!” አሉ። 40ሕዝቡም ሁሉ እርሱን ተከትለው ወጡ፤ ሕዝቡም ዘፈን ይዘፍኑ ነበር፤ በታላቅም ደስታ ደስ አላቸው፤ ከጩኸታቸውም የተነሣ ምድር ተናወጠች።
41አዶንያስና እርሱም የጠራቸው ሁሉ መብሉና መጠጡ ተፈጽሞ ሳለ ሰሙ፤ ኢዮአብም የቀንደ መለከት ጽምጽ በሰማ ጊዜ “ይህ በከተማ ውስጥ ያለ የሽብር ድምጽ ምንድር ነው?” አለ። 42እርሱም ይህን ሲናገር የካህኑ የአብያታር ልጅ ዮናታን መጣ፤ አዶንያስም “አንተ መልካም ሰው ነህና፥ መልካም ታወራልናለህና ግባ፤” አለ። 43ዮናታንም ለአዶንያስ እንዲህ ብሎ መለሰ “በእውነት ጌታችን ንጉሥ ዳዊት ሰሎሞንን አነገሠው። 44ንጉሡም ከእርሱ ጋር ካሁኑን ሳዶቅንና ነቢዩን ናታንን የዮዳሄንም ልጅ በናያስን ከሊታውያንንና ፈሊታውያንንም ሰደደ፤ በንጉሡም በቅሎ ላይ አስቀመጡት። 45ካህኑም ሳዶቅና ነቢዩ ናታን በግዮን ንጉሥ አድርገው ቀቡት፤ ከዚያም ደስ ብሎአቸው ወጡ፤ ከተማይቱም አስተጋባች፤ የሰማችሁትም ድምጽ ይህ ነው። 46ደግሞም ሰሎሞን በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦአል። 47የንጉሡም ባሪያዎች ገብተው ‘እግዚአብሔር የሰሎሞንን ስም ከስምህ ዙፋኑንም ከዙፋንህ የበለጠ ያድርግ!’ ብለው ጌታችንን ንጉሡን ዳዊትን ባረኩ፤ ንጉሡም በአልጋው ላይ ሆኖ ሰገደ። 48ንጉሡም ደግሞ ‘ዐይኔ እያየ ዛሬ በዙፋኔ ላይ የሚቀመጠውን የሰጠኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን!’ አለ።”
49አዶንያስም የጠራቸው ሁሉ ፈሩ፤ ተነሥተውም እያንዳንዳቸው በየመንገዳቸው ሄዱ። 50አዶንያስም ሰሎሞንን ፈራ፤ ተነሥቶም ሄደ፤ የመሠዊያውንም ቀንድ ያዘ። 51ለሰሎሞንም “እነሆ፥ አዶንያስ ንጉሡን ሰሎሞንን ፈርቶ ‘ንጉሡ ሰሎሞን ባሪያውን በሰይፍ እንዳይገድለኝ ዛሬ ይማልልኝ፤’ ብሎ የመሠዊያውን ቀን ይዞአል፤” አሉት። 52ሰሎሞንም “እርሱ አካሄዱን ያሳመረ እንደ ሆነ ከእርሱ አንዲት ጠጕር እንኳ በምድር ላይ አትወድቅም፤ ነገር ግን ክፋት የተገኘበት እንደ ሆነ ይሞታል፤” አለ። 53ንጉሡ ሰሎሞንም ላከ፤ ከመሠዊያውም አወረዱት፤ መጥቶም ለንጉሡ ለሰሎሞን እጅ ነሣ፤ ሰሎሞንም “ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ