የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 6

6
1የእግዚአብሔር ታቦት በፍልስጥኤማውያን አገር ሰባት ወር ተቀመጠ። 2ፍልስጥኤማውያንም ካህናትንና ምዋርተኞችን ጠርተው፥ በእግዚአብሔር ታቦት ላይ ምን እናድርግ? ወደ ስፍራውስ በምን እንስደደው? አስታውቁን አሉ። 3እነርሱም፦ የእስራኤልን አምላክ ታቦት ብትሰድዱ የበደል መሥዋዕት መልሱለት እንጂ ባዶውን አትስደዱት፥ የዚያን ጊዜም ትፈወሳላችሁ፥ እጁም ከእናንተ አለመራቁ ስለ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ አሉ። 4እነርሱም፦ ስለ በደል መሥዋዕት የምንመልስለት ምንድር ነው? አሉ። እነርሱም እንዲህ አሉ፦ እናንተንና አለቆቻችሁን ያገኘች መቅሠፍት አንዲት ናትና እንደ ፍልስጥኤማውያን አለቆች ቁጥር አምስት የወርቅ እባጮች አምስትም የወርቅ አይጦች አቅርቡ። 5የእባጫችሁንም ምሳሌ ምድራችሁንም የሚያጠፋአትን የአይጦችን ምሳሌ አድርጋችሁ ለእስራኤል አምላክ ክብርን ስጡ፥ እጁን ከእናንተና ከአማልክቶቻችሁ ከምድራችሁም ምናልባት ያቀልል ይሆናል። 6ግብጻውያንና ፈርዖንም ልባቸውን እንዳጸኑ ልባችሁን ለምን ታጸናላችሁ? እግዚአብሔር ኃይሉን ካደረገባቸው በኋላ ያወጡአቸው አይደሉምን? እነርሱም አልሄዱምን? 7አሁንም ወስዳችሁ አንዲት ሰረገላ ሥሩ፥ የሚያጠቡም፥ ቀን በር ያልተጫነባቸውን ሁለት ላሞች በሰረገላ ጥመዱአቸው፥ እንቦሶቻቸውንም ለይታችሁ ወደ ቤት መልሱአቸው። 8የእግዚአብሔርንም ታቦት ወስዳችሁ በሰረገላው ላይ አኑሩት፥ ስለ በደልም መሥዋዕት ያቀረባችሁትን የወርቁን ዕቃ በሣጥን ውስጥ አድርጋችሁ በታቦቱ አጠገብ አኑሩት፥ ይሄድም ዘንድ ስደዱት። 9ተመልከቱም፥ በድንበሩም መንገድ ወደ ቤትሳሚስ ቢወጣ ይህን እጅግ ክፉ ነገር ያደረገብን እግዚአብሔር ነው፥ አለዚያም እንዲያው መጥቶብናል እንጂ የመታን የእርሱ እጅ እንዳልሆነ እናውቃለን።
10ሰዎቹም እንዲሁ አደረጉ፥ የሚያጠቡትን ሁለቱን ላሞች ወሰዱ፥ በሰረገላም ጠመዱአቸው፥ እንቦሳቻቸውንም በቤት ዘጉባቸው፥ 11የእግዚአብሔርንም ታቦት፥ የወርቁ አይጦችና የእባጮቻቸው ምሳሌ ያሉበትንም ሣጥን በሰረገላው ላይ ጫኑ። 12ላሞችም ወደ ቤትሳሚስ ወደሚወስደው መንገድ አቅንተው እምቧ እያሉ በጎዳናው ላይ ሄዱ፥ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላሉም፥ የፍልስጥኤማውያንም አለቆች እስከ ቤትሳሚስ ዳርቻ ድረስ በኋላ በኋላቸው ይሄዱ ነበር። 13የቤትሳሚስ ሰዎችም በሸለቆው ውስጥ ስንዴ ያጭዱ ነበር፥ ዓይናቸውንም ከፍ አድርገው ታቦቱን አዩ፥ በማየታቸውም ደስ አላቸው። 14ሰረገላውም ወደ ቤትሳሚሳዊው ወደ ኢያሱ እርሻ መጣ፥ ታላቅም ድንጋይ በነበረበት በዚያ ቆመ፥ የሰረገላውንም እንጨት ፈልጠው ላሞቹን ለእግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ። 15ሌዋውያንም የእግዚአብሔርን ታቦት፥ ከእርሱ ጋር የነበረውንም የወርቅ ዕቃ ያለበትን ሣጥን አወረዱ፥ በታላቁም ድንጋይ ላይ አኖሩት፥ በዚያም ቀን የቤትሳሚስ ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረቡ፥ መሥዋዕትንም ሠዉ። 16ፍልስጥኤማውያንም አምስቱ አለቆች ባዩት ጊዜ በዚያው ቀን ወደ አስቀሎና ተመለሱ።
17ፍልስጥኤማውያን ስለ በደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀረቡአቸው የወርቅ እባጮች እነዚህ ናቸው፥ አንዲቱ ለአዛጦን፥ አንዲቱም ለጋዛ፥ አንዲቱም ለአስቀሎና፥ አንዲቱ ለጌት፥ 18አንዲቱ ለአቃሮን የወርቁም አይጦች ቁጥር ለአምስቱ የፍልስጥኤማውያን አለቆች እንደ ነበሩት ከተሞች ሁሉ ቁጥር እንዲሁ ነበረ፥ እነርሱም እስከ ታላቁ ድንጋይ የሚደርሱ ከተሞችና መንደሮች ናቸው። በዚህም ድንጋይ ላይ የእግዚአብሔርን ታቦት አስቀመጡ፥ ድንጋዩም እስከ ዛሬ ድረስ በቤትሳሚሳዊው በኢያሱ እርሻ አለ።
19ወደ እግዚአብሔርም ታቦት ውስጥ ተመልክተዋልና የቤትሳሚስን ሰዎች መታ፥ በሕዝቡም ከአምስት ሺህ ሰው ሰባ ሰዎችን መታ፥ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ ግዳይ ስለ መታ ሕዝቡ አለቀሰ። 20የቤትሳሚስም ሰዎች፦ በዚህ በቅዱስ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ማን ይችላል? ከእኛስ ወጥቶ ወደ ማን ይሄዳል? አሉ። 21በቂርያትይዓሪምም ወደ ተቀመጡት ሰዎች መልክተኞች ልከው፦ ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት መልሰዋል፥ ወርዳችሁም ወደ እናንተ አውጡት አሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ