2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10
10
1እኔም ራሴ ጳውሎስ፥ በእናንተ ዘንድ ፊት ለፊት ሳለሁ ትሑት የሆንሁ፥ ከእናንተ ግን ብርቅ የምደፍራችሁ፥ በክርስቶስ የዋህነትና ገርነት እመክራችኋለሁ፤ 2በዓለማዊ ልማድ እንደምንመላለስ በሚቆጥሩን በአንዳንዶች ላይ አምኜ ልደፍር አስባለሁ፥ በዚያ እምነት ግን ከእናንተ ጋር ሆኜ እንዳልደፍር እለምንችኋለሁ። 3በሰው ልማድ ምንም እንኳ የምንመላለስ ብንሆን፥ እንደ ሰው ልማድ አንዋጋም፤ 4የጦር ዕቃችን ሥጋዊ አይደለምና፥ ምሽግን ለመስበር ግን በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ነው፤ 5የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥ 6መታዘዛችሁም በተፈጸመች ጊዜ አለመታዘዝን ሁሉ ልንበቀል ተዘጋጅተናል።
7በፊታችሁ ያለውን ተመልከቱ። ማንም የክርስቶስ መሆኑን ተረድቶ ቢሆን፥ ይህን እንደ ገና በራሱ ይቁጠረው፤ እርሱ የክርስቶስ እንደ ሆነ እኛ ደግሞ እንዲሁ ነን። 8ጌታ እናንተን ለማነጽ እንጂ እናንተን ለማፍረስ ያይደለ በሰጠው በሥልጣናችን ከፊት ይልቅ ብመካ እንኳ አላፍርም። 9በመልእክቶቼ የማስደነግጣችሁ አይምሰላችሁ። 10መልእክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፥ ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው ይላሉና። 11እንዲሁ የሚል ይህን ይቁጠረው፤ በሩቅ ሳለን በመልእክታችን በኩል በቃል እንዳለን፥ በፊቱ ደግሞ ሳለን በሥራ እንዲሁ ነን። 12ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም።
13እኛ ግን እግዚአብሔር እንደ ወሰነልን እስከ እናንተ እንኳ እንደሚደርስ እንደ ክፍላችን ልክ እንጂ ያለ ልክ አንመካም። 14ወደ እናንተ እንደማንደርስ አድርገን ከመጠን አናልፍምና፥ የክርስቶስን ወንጌል በመስበክ እስከ እናንተ እንኳ ደርሰናልና፤ 15-16በሌሎች ድካም ያለ ልክ አንመካም፥ ነገር ግን እምነታችሁ ሲያድግ ከእናንተ ወዲያ ባለው አገር እስክንሰብክ ሥራችንን እየጨመርን፥ በክፍላችን በእናንተ ዘንድ እንድንከብር ተስፋ እናደርጋለን፤ በሌላው ክፍል ስለ ተዘጋጀው ነገር አንመካም። 17-18የሚመካ ግን በጌታ ይመካ፤ እግዚአብሔር የሚያመሰግነው እንጂ ራሱን የሚያመሰግን እርሱ ተፈትኖ የሚወጣ አይደለምና።
Currently Selected:
2 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ