የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 1

1
1እንዲህም ሆነ፥ ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት አማሌቃውያንን ከመግደል ተመልሶ በጺቅላግ ሁለት ቀን ያህል ተቀመጠ። 2በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ ከሳኦል ሰፈር አንድ ሰው ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ መጣ፥ ወደ ዳዊትም በመጣ ጊዜ በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ። 3ዳዊትም፦ ከወዴት መጣህ? አለው፥ እርሱም፦ ከእስራኤል ሰፈር ኮብልዬ መጣሁ አለው። 4ዳዊትም፦ ነገሩ እንደ ምን ሆነ? እስኪ ንገረኝ አለው። እርሱም መልሶ፦ ሕዝቡ ከሰልፉ ሸሽቶአል፥ ከሕዝቡ ብዙው ወደቁ ሞቱም፥ ሳኦልና ልጁም ዮናታን ደግሞ ሞተዋል አለ። 5ዳዊትም ወሬኛውን ጕልማሳ፦ ሳኦልና ልጁ ዮናታን እንደ ሞቱ በምን ታውቃለህ? አለው። 6ወሬኛውም ጕልማሳ አለ፦ በድንገት ወደ ጊልቦዓ ተራራ መጣሁ፥ እነሆም፥ ሳኦል ጦሩን ተመርኩዞ ቆሞ ነበር፥ ሰረገሎችና ፈረሰኞችም ተከትለው ደረሱበት። 7ወደ ኋላውም ዘወር አለና እኔን አይቶ ጠራኝ፥ እኔም፦ እነሆኝ አልሁ። 8እርሱም፦ አንተ ማን ነህ? አለኝ፥ እኔም፦ አማሌቃዊ ነኝ ብዬ መለስሁለት። 9እርሱም፦ ሰውነቴ ዝሎአልና፥ ደግሞ እስከ አሁን ድረስ ነፍሴ ገና ፈጽማ ሕያው ናትና በላዬ ቆመህ ግደለኝ አለኝ። 10እኔም ከወደቀ በኋላ አለ መዳኑን አይቼ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፥ በራሱም ላይ የነበረውን ዘውድ በክንዱም የነበረውን ቢተዋ ወሰድሁ፥ ወደዚህም ወደ ጌታዬ አመጣሁት። 11ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ይዘው ቀደዱ። 12በሰይፍም ወድቀዋልና ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን ለእግዚአብሔርም ሕዝብ ለእስራኤልም ወገን እንባ እያፈሰሱ አለቀሱ፥ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ። 13ዳዊትም ወሬኛውን ጕልማሳ፦ አንተ ከወዴት ነህ? አለው፥ እርሱም፦ እኔ የመጻተኛው የአማሌቃዊው ልጅ ነኝ ብሎ መለሰለት። 14ዳዊትም፦ እግዚአብሔር የቀባውን ለመግደል እጅህን ስትዘረጋ ለምን አልፈራህም? አለው። 15ዳዊትም ከጕልማሶቹ አንዱን ጠርቶ፦ ወደ እርሱ ቅረብና ውደቅበት አለው። እርሱም መታው፥ ሞተም። 16ዳዊትም፦ እግዚአብሔር የቀባውን እኔ ገድያለሁ ብሎ አፍህ በላይህ መስክሮአልና ደምህ በራስህ ላይ ይሁን አለው።
17ዳዊትም ስለ ሳኦልና ሰለ ልጁ ስለ ዮናታን ይህን የኅዘን ቅኔ ተቀኘ፥ 18የይሁዳንም ልጆች ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። እነሆ፥ ይህ በያሻር መጽሐፍ ተጽፎአል። 19የእስራኤል ክብር በኮረብቶች ላይ ተወግቶ ሞተ፥ ኃያላን እንዴት ወደቁ! 20የፍልስጥኤማውያን ቈነጃጅት ደስ እንዳይላቸው፥ የቆላፋንም ቈነጃጅት እልል እንዳይሉ፥ በጌት ውስጥ አታውሩ፥ በአስቀሎናም አደባባይ የምስራች አትበሉ። 21እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፥ የሳኦል ጋሻ በዘይት እንዳልተቀባ፥ የኃያላን ጋሻ በዚያ ወድቆአልና ዝናብና ጠል አይውረድባችሁ፥ ቍርባንንም የሚያበቅል እርሻ አይሁንባችሁ። 22ከሞቱት ደምና ከኃያላን ስብ የዮናታን ቀስት አልተመለሰችም፥ የሳኦልም ሰይፍ በከንቱ አልተመለሰም። 23ሳኦልና ዮናታን የተዋደዱና የተስማሙ ነበሩ፥ በሕይወታቸውና በሞታቸው አልተለያዩም፥ ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ፥ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ። 24የእስራኤል ቈነጃጅት ሆይ፥ ቀይ ሐርና ጥሩ ግምጃ ያለብሳችሁ ለነበረ፥ በወርቀዘቦም ላስጌጣችሁ ለሳኦል አልቅሱለት። 25ኃያላንም በሰልፍ ውስጥ እንዴት ወደቁ! ዮናታንም በኮረብቶችህ ላይ ወድቆአል። 26ወንድሜ ዮናታን ሆይ፥ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ፥ በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበር፥ ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ። 27ኃያላን እንዴት ወደቁ! የሰልፍም ዕቃ እንዴት ጠፋ!

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ