ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17
17
1አኪጦፌልም አቤሴሎምን፦ አሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ልምረጥና በዚህች ሌሊት ተነሥቼ ዳዊትን ላሳድድ። 2ደክሞና እጅ ዝሎ ሳለ እወድቅበታለህ፥ አስፈራውማለሁ፥ ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ ይሸሻል፥ ንጉሡንም ብቻውን እመታዋለሁ፥ 3ሙሽራ ወደ ባልዋ እንደምትመለስ ሕዝቡን ሁሉ ወደ አንተ እመልሰዋለሁ፥ ሕዝቡ ሁሉ ደኅና ይሆናል፥ የምትፈልገው አንድ ሰው ብቻ ነው። 4ነገሩም አቤሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች ሁሉ ደስ አሰኘ።
5አቤሴሎምም፦ አርካዊውን ኩሲን ጥሩ፥ ደግሞም እርሱ የሚለውን እንስማ አለ። 6ኩሲም ወደ አቤሴሎም በመጣ ጊዜ አቤሴሎም፦ አኪጦፌል ያለው ይህ ነው፥ ነገሩን እናደርገው ዘንድ ይገባልን? ባይሆን ግን አንተ ንገረን ብሎ ተናገረው። 7ኩሲም አቤሴሎምን፦ አኪጦፌል በዚህ ጊዜ የመከራት ምክር መልካም አይደለችም አለው። 8ኩሲ ደግሞ አለ፦ ግልገሎችዋ በዱር በተነጠቁ ጊዜ ድብ መራራ እንደ ሆነች በልባቸው መራሮች እጅግም ኃያላን መሆናቸውን አባትህንና ሰዎቹን ታውቃለህ፥ አባትህ አርበኛ ነው፥ ከሕዝብም ጋር አያድርም። 9አሁንም ምናልባት በአንድ ጉድጓድ ወይም በማናቸውም ስፍራ ተሸሽጎ ይሆናል፥ በመጀመሪያም ከእነርሱ አያሌዎች ቢወድቁ፥ የሚሰማው ሁሉ፦ አቤሴሎምን የተከተለው ሕዝብ ተመታ ይላል። 10እስራኤልም ሁሉ አባትህ ኃያል እንደ ሆነ፥ ከእርሱም ጋር ያሉት ሰዎች ጽኑዓን እንደ ሆኑ ያውቃልና ጽኑዕ ልቡም እንደ አንበሳ ልብ የሆነው ፈጽሞ ይቀልጣል። 11ነገር ግን የምመክርህ ይህ ነው፥ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያለ እስራኤል ሁሉ በብዛቱ እንደ ባሕር አሸዋ ሆኖ ወደ አንተ ይሰብሰብ፥ አንተም በመካከላቸው ወደ ሰልፍ ውጣ። 12እርሱንም ወደምናገኝበት ወደ አንድ ስፍራ እንደርስበታለን፥ ጠልም በምድር ላይ እንደሚወድቅ እንወርድበታለን፥ እርሱና ከእርሱም ጋር ያሉ ሰዎች ሁሉ አንድ ስንኳ አናስቀርም። 13ወደ ከተማም ቢገባ እስራኤል ሁሉ ወደዚያች ከተማ ገመድ ይወስዳል፥ እኛም አንድ ድንጋይ እንኳ እስከማይገኝባት ድረስ ወደ ወንዙ ውስጥ እንስባታለን። 14አቤሴሎምና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ፦ የአርካዊው የኩሲ ምክር ከአኪጦፌል ምክር ይሻላል አሉ። እግዚአብሔርም በአቤሴሎም ላይ ክፉ ያመጣ ዘንድ እግዚአብሔር መልካሚቱን የአኪጦፌልን ምክር እንዲበትን አዘዘ። 15ኩሲም ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር፦ አኪጦፌል ለአቤሴሎምና ለእስራኤል ሽማግሌዎች እንዲህና እንዲህ መክሮአል፥ እኔ ግን እንዲህና እንዲህ መክሬአለሁ። 16አሁን እንግዲህ ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ እንዳይዋጡ፥ ፈጥናችሁ፦ ሳትዘገይ ተሻገር እንጂ በዚህች ሌሊት በምድረ በዳ መሻገሪያ አትደር ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት አላቸው። 17ዮናታንና አኪማአስ ተገልጠው ወደ ከተማ ይገቡ ዘንድ አልቻሉም ነበርና በዓይንሮጌል ተቀምጠው ነበር፥ አንዲትም ባሪያ ሄዳ ትነግራቸው ነበር፥ እነርሱም ሄደው ለንጉሡ ለዳዊት ይነግሩት ነበር። 18አንድ ብላቴናም አይቶ ለአቤሴሎም ነገረው፥ እነርሱ ግን ፈጥነው ሄዱ፥ ወደ ብራቂምም ወደ አንድ ሰው ቤት መጡ፥ በግቢውም ውስጥ ጉድጓድ ነበረ፥ ወደዚያም ውስጥ ወረዱ። 19ሴቲቱም በጉድጓዱ አፍ ላይ ዳውጃ ዘረጋችበት፥ የተከካ እህልም በላዩ አሰጣችበት፥ ነገሩም እንዲህ ተሰወረ። 20የአቤሴሎም ባሪያዎች ወደ ሴቲቱ ወደ ቤት መጥተው፦ አኪማአስና ዮናታን የት አሉ? አሉ፥ ሴቲቱም፦ ፈፋውን ተሻግረው ሄዱ አለቻቸው። እነርሱም ፈልገው ባላገኙአቸው ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። 21ከሄዱም በኋላ እነርሱ ከጉድጓዱ ወጥተው ሄዱ፥ ለንጉሡም ለዳዊት ነገሩት፥ ዳዊትንም፦ አኪጦፌል በእናንተ ላይ እንዲህ መክሮአልና ተነሡ፥ ፈጥናችሁም ውኃውን ተሻገሩ አሉት። 22ዳዊትና ከእርሱም ጋር የነበሩት ሁሉ ተነሥተው ዮርዳኖስን ተሻገሩ፥ እስኪነጋም ድረስ ዮርዳኖስን ሳይሻገር አንድ ሰው እንኳ አልቀረም። 23አኪጦፌልም ምክሩን እንዳልተከተሉ ባየ ጊዜ አህያውን ጫነ፥ ተነሥቶም ወደ ቤቱ ወደ ከተማው ሄደ፥ ቤቱንም አደራጅቶ በገዛ እጁ ታንቆ ሞተ፥ በአባቱም መቃብር ተቀበረ።
24ዳዊትም ወደ መሃናይም መጣ፥ አቤሴሎምም ከእርሱም ጋር የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ዮርዳኖስን ተሻገሩ። 25አቤሴሎምም በጭፍራው ላይ በኢዮአብ ስፍራ አሜሳይን ሾመ፥ አሜሳይም የይስማኤላዊ ሰው የዬቴር ልጅ ነበረ፥ እርሱም የኢዮአብን እናት የጽሩያን እኅት የናዖስን ልጅ አቢግያን አግብቶ ነበር። 26እስራኤልና አቤሴሎምም በገለዓድ ምድር ሰፈሩ።
27ዳዊትም ወደ መሃናይም በመጣ ጊዜ በአሞን ልጆች አገር በረባት የነበረ የናዖስ ልጅ ኡኤስቢ፥ የሎዶባርም ሰው የዓሚኤል ልጅ ማኪር፥ የሮግሊምም ሰው ገለዓዳዊው ቤርዜሊ፦ 28ሕዝቡ በምድረ በዳ ተርቦአል፥ ደክሞአል፥ ተጠምቶአል ብለው ምንጣፍ፥ ዳካ፥ የሸክላም ዕቃ፥ ይበሉም ዘንድ 29ስንዴ፥ ገብስ ዱቄት፥ የተጠበሰ እሸት፥ ባቄላ፥ ምስር፥ የተቆላ ሽንብራ፥ ማር፥ ቅቤ፥ በጎች፥ የላምም እርጎ ለዳዊትና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ አመጡላቸው።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ