ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7
7
1እንዲህም ሆነ፥ ንጉሡ በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ባሳረፈው ጊዜ፥ 2ንጉሡ ነቢዩን ናታንን፦ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬአለሁ፥ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በመጋረጆች ውስጥ እንደ ተቀመጠ እይ አለው። 3ናታንም ንጉሡን፦ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ሂድ፥ በልብህም ያለውን ሁሉ አድርግ አለው። 4በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው፦ 5ሂድ፥ ለባሪዬ ለዳዊት ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 6የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት አልተቀመጥሁምና አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም። 7ከእስራኤል ልጆች ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ፦ ስለ ምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን? 8አሁንም ዳዊትን ባሪያዬን እንዲህ በለው፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ፥ 9በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፥ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆቹ ስም ታላቅ ስም አደርግልሃለሁ። 10ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ 11እተክለውማለሁ፥ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋላ አይናወጥም፥ እንደ ቀድሞው ዘመንና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፈራጆች እንዳስነሣሁበት ጊዜ ግፈኞች ተመልሰው አያስጨንቁትም፥ ከጠላቶችህም አሳርፍሃለሁ። እግዚአብሔርም ደግሞ፦ ቤት እሠራልሃለሁ ብሎ ይነግርሃል። 12ዕድሜህም በተፈጸመ ጊዜ ከአባቶችህም ጋር ባንቀላፋህ ጊዜ፥ ከወገብህ የሚወጣውን ዘርህን ከአንተ በኋላ አስነሣለሁ፥ መንግሥቱንም አጸናለሁ። 13እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፥ የመንግሥቱንም ዙፋን ለዘላለም አጸናለሁ። 14እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፥ ክፉ ነገርም ቢያደርግ፥ ሰው በሚቀጣበት በትርና በሰው ልጆች መቀጫ እገሥጸዋለሁ፥ 15ከፊቴም ከጣልሁት ከሳኦል እንዳራቅሁ ምሕረቴን ከእርሱ አላርቅም። 16ቤትህና መንግሥትህም በፊቴ ለዘላለም ይጠነክራል፥ ዙፋንህም ለዘላለም ይጸናል። 17እንደዚህ ቃል ሁሉ እንደዚህም ራእይ ሁሉ ናታን ለዳዊት ነገረው።
18ንጉሡ ዳዊትም ገባ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፦ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ እስከዚህ ያደረስኸኝ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድር ነው? 19ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ በፊትህ ጥቂት ነበረ፥ ስለ ባሪያህም ቤት ደግሞ ለሩቅ ዘመን ተናገርህ፥ ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ ይህ የሰው ሕግ ነው። 20ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ባሪያህን ታውቃለህና ዳዊትስ ይናገርህ ዘንድ የሚጨምረው ምንድን ነው? 21ለባሪያህም ታስታውቀው ዘንድ ስለ ቃልህ ምክንያትና እንደ ልብህ አሳብ ይህን ታላቅ ነገር ሁሉ አደረግህ። 22ስለዚህም፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እንደ አንተ ያለ የለምና፥ በጆሮአችንም እንደ ሰማን ሁሉ ከአንተ በቀር አምላክ የለምና አንተ ታላቅ ነህ። 23ለእርሱ ለራሱ እንዲሆን ሕዝብን ይቤዥ ዘንድ ለእርሱ ለራሱም ስም ያደርግ ዘንድ፥ በአሕዛብና በአምላኮቻቸውም ፊት ከግብጽ በተቤዠው ሕዝብ ፊት ተአምራትንና ድንቅን ያደርግ ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ሄደለት እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ያለ በምድር ላይ ምን ሕዝብ አለ? 24ሕዝብህንም እስራኤልን ለዘላለም ሕዝብ አድርገህ አጽንተኸዋል፥ አንተም፥ አቤቱ፥ አምላክ ሆነሃቸዋል። 25አቤቱ አምላክ ሆይ፥ አሁንም ለባሪያህና ለቤቱ የተናገርኸውን ለዘላለም አጽናው፥ እንደ ተናገርህም አድርግ። 26የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው ይባል ዘንድ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሁን፥ የባሪያህም የዳዊት ቤት በፊትህ የጸና ይሁን። 27አቤቱ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ አንተ፦ እኔ ቤት እሠራልሃለሁ ብለህ ለባሪያህ ገልጠሃልና ስለዚህ ባሪያህ ይህችን ጸሎት ወደ አንተ ይጸልይ ዘንድ በልቡ ደፈረ። 28ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አሁንም አንተ አምላክ ነህ፥ ቃልህም እውነት ነው፥ ይህንም መልካም ነገር ለባሪያህ ተናግረሃል። 29ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ ተናግረሃልና አሁን እንግዲህ ለዘላለም በፊትህ ይሆን ዘንድ የባሪያህን ቤት፥ እባክህ፥ ባርክ፥ በበረከትህም የባሪያህ ቤት ለዘላለም ይባረክ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ